ጉባኤ ከበብ ቤተ ክርስቲያን

Written by :   Categories :   The Church Religious or Spiritual
    Download Formats:

Chapter 1
ለአዲስ የወይን ጠጅ አዲስ አቁማዳ ያስፈልጋል

" አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ " (ሉቃስ 5፡38)።

ጌታ በሕይወቴ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሲያከናውን በነበረውን በዚህ ትንሽ መጽሐፍ ውስጥ ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ። ይህም ለእኔ እጅግ ውድ የሆነ ዘላለማዊነትም ስላለውም መስዋእትን ያካተተ አኗኗር ነው።

በእውነት የክርስቶስን ትምህርት እና ሕይወት ለመረዳት ፍላጎት ካለን ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው ውድ የሆኑ ነገሮችን ትተን በብዙ መስኮች መሥዋዕቶች መክፈል ይኖርብላል። ይህን ስናደርግ ጌታ ሊያስተምረን የሚፈልጋቸው ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ይታያሉ። ይህም ሲሆን እግዚአብሔር ለህይወታችን ያለውን አጠቃላይ እቅድ እንፈፅማለን።

በአዲስ ኪዳን ላይ የተመሠረተች ቤተ ክርስቲያንን ማቋቋም ለእኔ እግዚአብሔር በጣም ውድ አድርጎልኛል።
ሆኖም ይህን ለማከናወን ያለው መንገድ በጣም ፣ በጣም ጠባብ ነው።፡

አስፈላጊው ብቸኛ ነገር

አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ውስጥ መቀመጥ እንዳለበት ኢየሱስ ተናግሯል። አዲሱ የወይን ጠጅ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ሊሰጠን የፈለገው የእሱ ሕይወት ነው። አዲሱም አቁማዳ የእሱ ሕይወት እንዲገለጽበት፣ በእኛ አማካይነት ለማቋቋም የሚፈልገው የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስትያን ነው።

ይህንን አዲስ ኪዳናዊ ሕይወት ለመኖር ከልብ ከፈለግን እግዚአብሔር በየጊዜው እንዳሳየን ይህንን እንደ ሽንኩርት ንብርብሮች ያሉትን ብዙ የራስ ወዳድነት ደረጃዎችን አንድ በአንድ ማስወገድ እንዳለብን እንገነዘባለን። በአዲስ ኪዳን ላይ የተመሠረተ ቤተ ክርስቲያን ስናቋቋምም ሁኔታው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው።

አሮጌው የወይን ጠጅ አቁማዳ ይሚመሰለው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ሳይሆን በሰው ሰራሽ የተለምዶ ሥርዓቶች ላይ የተገነባ ቤተ ክርስቲያንን ነው ። ይህን የመሳሰሉትን ንብርብሮች በየጊዜው ጌታ ሲያሳየን ነቅለን መጣል አለብን። የሚያሳዝነው ነገር ፣ አዲስ ኪዳናዊ ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት የሚሹ ብዙ ክርስቲያኖች የተወሰነ ደረጃ ላይ ደርስው ያደጉባቸውን አንዳንድ ግልፅ የሆኑ የሰው እና ሃይማኖታዊ ወጎችን ብቻ አስወግደው ገና ብዙ የሚነሱ የአሮጌው የወይን አቁማዳ ንብርብሮች ሳይነኩ እድገታቸውን ያቆማሉ። ነገር ግን ጌታ የሚፈለግብን አሮጌውን የወይን ጠጅ አቁማዳ እንዳለ አስወግደን አዲሱን ወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ እንድናደርግ ነው።

ቤተ ክርስቲያንን እንደ ክርስቶስ አካል አድርጎ ማቋቋም ላይ አዲስ ወይን ጠጅ እና አዲስ አቁማዳ ምን ማለት እንደ ሆነ በተግባር ሳይሆን በንድፈ-ሀሳብ ለብዙ አመታት አውቅ ነበር። ይህም የሆነው በዚህ አርዕስት ላይ ከሌሎች በላይ ቡዙ ስብከቶችን ስለ ሰማሁ ያጠራቀምኩት የራስ እውቀት ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ አባቴ እሁድ እሁድ ስለ አዲስ ኪዳን ሲያስተምሩ አዳምጥ ነበር። ከሰኞ እስከ ቅዳሜም ቤት ውስጥ አዳምጣቸው ነበር። ሆኖም ይህ ሁሉ የራስ እውቀት ብቻ ነበር። ከብዙ አመታት በኋላ ግን እነዚህ እውነቶች ወደ ልቤ ወረዱ። በዚህን ጊዜ ጌታን ማገልገል የምችለው በዚህ መንገድ ብቻ መሆኑን ተገነዘብኩ።

አሁን በሕይወቴ ውስጥ ለእኔ ብቸኛው አካል ኢየሱስ ነው። ከሌሎች ጋር ያለኝ ግንኙነቶች ሁሉ ከኢየሱስ ጋር ካለኝ ግንኙነት የሚመነጩ ናቸው። ስለዚህ አሁን ለጌታ ያለኝ ዋና አገልግሎት ቤተክርስትያንን እንደ ክርስቶስ አካል አድርጎ ማቋቋም ነው።

ጌታችን ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ እያንዳንዱን ቀን የመስቀልን መንገድ ለምን መረጠ? ይህንን ያደረገው መጽሓፍ ቅዱስ እንደሚለው "በፊቱም ስላለው ደስታ " (ዕብራዊያን 12፡2) ነበር። በፊቱ የነበረው ደስታ ምንድን ንበር?

በዮሐንስ 14 ውስጥ ፣ ኢየሱስ ወደ መስቀሉ ከመሄዱ በፊት ከደቀመዛሙርቱ ሊለያይ ሲል የነገራቸውን በዮሐንስ 14 ላይ እናያለን። በመጨረሻው እራት ላይ የነበረውን ኢየሱስ ከደቀ መዝሙሮቹ ሊለያይ ሲል የተናገራቸውን የመጨረሻ ቃላት ሐዋርያው ​​ዮሐንስ ለእኛ ለመንገር አምስት ምዕራፎች ወስዶ በዝርዝር መጻፉን በጣም አደንቃለሁ። ዮሐንስ 14፡31 ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን "ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ" አላቸው። ኢየሱስ ወደ ስቅለቱ እያመራ ነበር። ይህን ከማለቱ በፊት እንዲህ አላቸው" ነገር ግን አብን እንድወድ ዓለም ሊያውቅ፥ አብም እንዳዘዘኝ፥ እንዲሁ አደርጋለሁ። " (ዮሐንስ 14፡31)።
ይህ ለኢየሱስ ደስታው ነበር - ማለትም ለዘለዓለም እንደነበረው ሁልጊዜ ለአባቱ መታዘዝ እና ከአባቱ ጋር ኅብረትን መፍጠር ማለት ነው። ከሁሉም አስቀድሞ ኢየሱስ ወደ መስቀሉ የሄደው አባቱን ስለሚያፈቅር፣ ለአባቱ ታዛዥ ስለሆነ እና ለእኛ ስላለው ፍቅር ነው።

የክርስቶስን ቤተክርስቲያን መገንባት የምንችልበት ብቸኛው መንገድም እንደዚሁ ስለሆነ ይህንን ነጥብ ማጉላት እፈልጋለሁ። ኃጢአትን ለማሸነፍ እና የጌታን ሥራ ለማከናወን ያለን ፍላጎት ሁሉ የሚመነጨው ለአብ ስላለን ፍቅር የተነሳ ለትእዛዛቱ ታማኞች ስንሆን እና ለሌሎች ፍቅር ሲኖረን ነው። ቤተክርስቲያንን ለመመሥረት ከፈለግን ለሰዎች ርህራሄ ያስፈልገናል። ሆኖም ከርህራሄው በፊት ግን ትእዛዛቱን እንድንከተል የሚያስችለን ለሰማያዊው አባታችን ከፍተኛ ፍቅር እንዲኖረን ያስፈልጋል።

የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያንን ለመመሥረት እነዚህ ሁለት መስፈርቶች አስፈላጊ ናቸው - አብን ማፍቀር እና ሌሎችንም ማፍቀር። እነዚህ በሁለቱ የመስቀሉ ጣውላዎች ሊመሰሉ ይችላሉ - አቀባዊው ጣውላ እና አግድም ጣውላ። ያላችሁ አንደኛው ጣውላ (አቀባዊው ወይም አግዳሚው) ብቻ ከሆነ መስቀል የላችሁም ማለት ነው።

በመስቀሉ በጣም የሚያምር፤ በየቀኑ እንዴት መስቀሉን መሸከም እንዳለብን የሚያመለክት፤ የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያብራራ ሁኔታን እናያለን።

በሚቀጥሉት ምዕራፎች ውስጥ የሁለቱ የመስቀል ጣውላዎች በሕይወታችን መኖር ምን ማለት እንደሆነ እና እንዴት እነዚህ ሁለቱ ጣውላዎች የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያንን ለመመሥረት እንድሚያገለግሉ ለማሳያት እወዳለሁ።

Chapter 2
የመስቀሉ አቀባዊው ጣውላ

የመስቀሉ አቀባዊ ጣውላ ለእግዚአብሔር አባታችን ያለንን ፍቅር የሚያሳይ ነው፤ ይህም በቀደምትነት መታየት አለበት። ኢየሱስ የተሰቀለበትን መስቀል ሲሠሩ የጀመሩት በአቀባዊ ሳንቃ ነበር። ይህ ሳንቃ በግምት የአግዳሚውን ሳንቃ ሁለት እጥፍ ይሆን ነበር።

የዚህም ምሳሌያዊ ትርጉም ከሰማያዊ አባታችን ጋር ያለን ቀጥተኛ ግንኙነት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ነው። ይህ ከሁሉም በቅድሚያ መኖር አለበት። ይህ ከሆነ በኋላ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ይከተላል።

የኢየሱስን ምሳሌ መከተል 

ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ከመሄዱ በፊት በምድራዊ ሕይወቱ ሁሉ ውስጣዊ መስቀሉን ተሸክሞ ነበር። ይህን የውስጣዊ መስቀል በምድር በኖረባቸው ከ12000 ቀናት በላይ ተሸክሞ ነበር የኖረው። ለእኛ እንዲህ ይላል " በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ" (ሉቃስ 9፡23)። በምድር ላይ ለእያንድንዷ 12000 ቀናት የኖረበት መሠረታዊ ሥርዓት ይህ ነበር፤ "ህይወቴ የሚወሰነው በመጀመሪያ ደረጃ ለአባቴ ባለኝ ፍቅር፣ ለትእዛዛቱ ታዛዥ መሆን እና ለሌሎች ባለኝ ፍቅር ነው"።


ለዚህም ነው ኢየሱስ ለምድራዊ ወላጆቹ በመገዛት ለ 30 ዓመታት በቤቱ ውስጥ ሊቆይ የቻለው። ለሰላሳ ዓመታት በየቀኑ ፍጽምና ለሌላቸው ለዮሴፍ እና ለማሪያም ታዛዥ ለመሆን ምን ያህል ያለመታዘዝ እና ያለመበሳጨት ፈተናዎችን ማሸነፍ ነበረበት። በደስተኝነት ታዛዥ ሆኖ የኖረው " በፊቱም ስላለው ደስታ" ነበር። ማለትም "እናትና አባትህን አክብር" የሚለውን የአባቱን ተዛዝ በመከተሉ ከአባቱ ጋር ለሚኖረው ደስታ ነበር።

መስቀሉን የመሸከም እና በሁሉም ነገር አባቱን የመታዘዝ ዝንባሌው እስከ ምድራዊ ሕይወቱ ማለቂያ ድረስ ቀጠለ። ለ 33 ዓመት ተኩል ያህል የመጀመሪያው የክርስቶስ አካል ኢየሱስ ነበረ። ዛሬ እኛ የእርሱ መንፈሳዊ አካላ አባላት ስለሆንን፣ እኛም እንደዚሁ ማድረግ አለብን።

የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የአማኞች ብቻ ሳይሆን የደቀ መዛሙርት ቤተክርስቲያን መሆን አለበት። ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው የግሉን ሕይወት በመካድ በየቀኑ መስቀሉን የሚሸከም ነው (ሉቃስ 9፡23)። ስለዚህ አዲሱን የወይን ጠጅ (የኢየሱስን ሕይወት) በአዲስ አቁማዳ (የአዲስ ኪዳን ቤተክርስትያን) ውስጥ ከፈለግን በየቀኑ ራሳችንን ክደን መስቀሉን ተሸክመን ኢየሱስን መከተል አለብን። ይህን ስናደርግ ብቻ ነው እንደ ክርስቶስ አካል የሆነ ቤተክርስትያን መመሥረት የምንችለው።

የተደበቀ የአማኝ ሕይወት

ቤተክርስቲያንን ለመመሥረት ፣ ከጌታችን ጋር አቀባዊ ግንኙነት በጣም አስፈላጊ ነው። ከጌታ ጋር ያለን ይህ ግንኙነት ምስጢራዊ እና በግል ሕይወታችን ውስጥ የሚታይ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች በሰይጣን ተታልለው እግዚአብሔርን ማምለካቸውን በውጭ በሚያደርጓቸው ሥርአቶች ይወስናሉ። ነገር ግን እውነተኛ አምልኮ 100% የውስጥ ነው። በተደበቀው ሕይወታቸን ነው።

አዲስ ኪዳን በመጀመሪያ ደረጃ በውስጣዊ ዝንባሌዎች ፤ በ ሀሳቦች እና በዓላማዎች ላይ ያተኮረ ነው።

በተራራው ስብከት ኢየሱስ ስለ ድብቅ ሕይወት ትናግሯል። በብሉይ ኪዳን ጊዜ እንደነበረው ከማመንዘር መራቅ ብቻ ሳይሆን በአዲስ ኪዳን ይህን ዓይነት አስተሳሰብ መጥላት አለብን። በብሉይ ኪዳን ጊዜ አስፈላጊ ሆኖ ይታይ የነበረው ምን ያህል እንደ ሰጣችሁ፤ ምን ያህል እንደ ጸለያችሁ አና ምን ያህል እንደ ጾማችሁ ነበር። አሁን ግን ኢየሱስ እንደተናገረው መስጠትም፤ መጸለይም ወይም መጾም ማንም ሰው ሳያውቅ በሚስጢር መሆን አለበት። ይህ የአዲስ ኪዳን አዲስ የወይን ጠጅ ነው።

ለክርስቶስ ያለንን ውስጣዊ አምልኮ በሚስጢር የመያዝ አስፈላጊቱን ካላስተዋልን፤ የአዲስ ኪዳን መሠረታዊ መርህ አልገባንም ማለት ነው። ለክርስቶስ ያለን መሰጠት ሁልጊዜ በሚስጢር መሆን አለብት።

"ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና" (ቆላስያስ 3፡3)። ይህ አስደሳች አኗኗር ነው። ለክርስቶስ መሰጠታችንን ከሌሎች ደብቀን በያዝን መጠን የጌታን ሚስጢሮች እያወቅን እንሄዳለን። ከሙሽራችን ጋር ሌሎች የማይውቁት የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረን ያስፈልጋል። ጥሩ ትዳር የሚሆነው ባል እና ሚስት ሌሎች በሌሉበት ሁለቱ ብቻ እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር ማንም ሳያውቅ ሲደስቱ ነው። እንደዚህ የመሰጠት መንፈስ ካላቸው ሙሽሮች ጋር ነው ዛሬ ኢየሱስ ቤተክርስያንን የሚመሠርተው።

አቀባዊው ጣውላ (አብን ማፍቀር እና ለክርስቶስ በፍጹምነት መሰጠት) ከተመሠረተ በኋላ፤ አግዳሚው ጣዎላ (ለሌሎች ያለን ፍቅር) ይደረጋል። ይህ ሲሆን በደስታ ይምንሰቀልበት መስቀል ተዘጋጅቷል ማለት ነው።


Chapter 3
የመስቀሉ አግድም ጣውላ

አግዳሚውን ጣውላ በአየር ላይ ለማንጠልጠል ብትሞክሩ አይሠራም፤ ይወድቃል። ነገር ግን በአቀባዊው ጣውላ ላይ በሚስማር ብታያይዙት ጠንክሮ ይቀመጣል፤ መስቀል ይሆናል። ሆኖም አስቀድሞ አቀባዊው ጣውላ መመሥረት አለበት።

የምናቋቁማቸው ቤተክርስቲያኖች በአዲስ ኪዳን ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው። ይህን ማድረግ የሚችሉ " ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም ... የላከኝን ፈቃድ" ነው የማደርገው የሚል አቋም ያላቸው ብቻ ናችው። የሚያሳዝነው ግን አብዛኞቹ ክርስቲያኖች እንደዚህ ዓይነት አመለካከት የላቸውም። የራሴም ሕይወት አንድ ጊዜ እንዲሁ ነበር። የፈለግሁትን እያደረግሁ ራሴን አማኝ ነኝ እል ነበር። ከእኔ 'የቤተክርስቲያን' አስተሳሰብ ጋር ከሚስማማ ቤተክርስቲያን ውስጥ መሳተፍ እፈልግ ነበር። በሁሉም ረገድ እንደ እኔ ካሉ ሰዎች ጋር ኅብረት መፍጠርን እፈልግ ነበር። ጊዜዬን ከምወዳቸው ሰዎች ጋር ብቻ ነበር ያማሳልፈው። ከማያስደስቱኝ ወንድሞች እርቅ ነበር። ይህ በመስቀሉ መንገድ መጓዝ አልነበረም። የዚህን ዓይነት አስተሳሰብ ከያዝን የክርስቶስን አካል በጭራሽ መገንባት አንችልም። እጅግ በጣም ጥሩ የሃይማኖት ትምህርት እየተቀበሉ ከመስቀሉ መንገድ ውጭ መጓዝ ይቻላል።


ኢየሱስ "እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ" (ዮሃንስ 13፡35) እንዳለው እርስ በርሳችን መዋደዳችን የደቀ መዛሙርትነታችን ማረጋገጫ ነው ብዬ ለብዙ ዓመታት አስብ ነበር። በተገኘሁበት ቤተክርስቲያን ያሉትን ወንድሞች እና እህቶች መውደድ ደቀ መዝሙር መሆኔን የሚያረጋግጥ ይመስለኝ ነበር።

ነገር ግን ይህን ጥቅስ በደንብ ብታስተውሉ ጥቅሱ የሚናገረው ለሌሎች (አማኝ ላልሆኑ ሰዎች) እርስ በርስ መዋደዳችን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆናችን ማስረጃነት ነው። ይህ የመስቀሉ አግዳሚ ጣውላ ነው።

ነገር ግን ቀደም ሲል ኢየሱስ የሱ ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያስፈልገው ፈቃዳችንን እና ራሳችንን መካድ እንደሆነ ተናግሯል (ሉቃስ 9፡23)። በመጀመሪያ በልባችሁ እና በውስጣዊ አኗኗራችሁ ደቀ መዝሙር መሆናችሁን እግዚአብሔር ማየት ይፈልጋል። በየቀኑ ራሳችሁን እየከዳችሁ ስትኖሩ "ሉቃስ 9፡23 ላይ እንደተገለጹት ክርስቲያኖች" መሆናችሁን እግዚአብሔር ያያል። በእርግጥም እንደነዚህ ዓይነት ብቻ ናቸው ክርስቲያን የሚባሉት። "ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ" (የሐዋሪያት ሥራ 11፡26)።

ከዚህ በኋላ፤ ሌሎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትን መውደዳችሁ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመሆናችሁ ማረጋገጫ ነው።

ሆኖም ማስተዋል ያለባችሁ በመጀመሪያ ላይ አቀባዊው ጣውላ መኖር እንዳለበት ነው። ማለትም እግዚአሔር ለእሱ ያላችሁን ፍቅር ሲያውቅ ነው። ስለዚህ በቤት ከርስቲያናችሁ ያሉትን ሰዎች ስለምንወድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ነን ብላችሁ ራሳችሁን አታታሉ! ለሌሎች ሰዎች ያላችሁ ሰብአዊ ፍቅር የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትነትን ያሳያል ብላችሁ ትታላሉ ይሆናል። ከሌሎች አማኞች ጋር እሁድ እሁድ አብራችሁ መሆናችሁ ደቀ መዛሙርትነታችሁን አያረጋግጥም። ደቀ መዛሙርትነታችሁን ማረጋገጥ የምትችሉት ከስኞ አስከ ቅዳሜ ከለሎች አማኞች ጋር በማትገናኙበት ጊዜ እንዴት ራሳችሁን ክዳችሁ ኢየሱስን በብርቱ ስትወዱ ነው። ማለትም የየቀኑ አኗኗራችሁ በኢየሱስ ፊት ሲሆን ነው።

እውነተኛ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከሁሉም አስቀድሞ ከሙሽራው ጋር ኅብረትን ስለሚሻ አንዱ ቀን ከሌላው ቀን አይበላለጥበትም። ከሌሎች ደቀ መዛሙርት ጋር ያለው ኅብረት የሚመነጨው ከጌታ ጋር ካለው ኅብረት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ደቀ መዝሙር በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በሚቀላቀሉ ወይም በሚተዉ አማኞች የተነሳ በጭራሽ አይረበሽም።
እውነተኛው ቤተክርስቲያን ሊገነባ የሚችለው በሕይወታቸው ውስጥ ወሳኙ ኢየሱስ ብቻ በሆነላቸው ደቀ መዛሙርት ብቻ ነው።

አስቀድሜ እንዳልኩት አንዱ ጣውላ አቅባዊው ሆነ አግዳሚው ብቻውን መስቀል አይሆንም። የሚያሳዝነው ፣ አብዛኛዎቹ አማኞች እና አብዛኛዎቹ ቤተ ክርስቲያናት ከእነዚህ ሁለት ምድቦች በአንዱ ውስጥ ይወድቃሉ፤ አቅባዊው ጣውላ ብቻ ወይም አግዳሚው ጣውላ ላይ ብቻ ያተኩራሉ።

ሶስት ዓይነት የክርስቲያኖች ስብሰባ ዐይቻለሁ።

1. ጉባኤ

2. ክበብ

3. ለአካባቢው የእውነተኛው ቤተ ክርስቲያን መግለጫ

ከሦስቱ ውስጥ የመጨረሻው ለአዲሱ የወይን ጠጅ የሚሆን አዲሱ የወይን ቆዳ ነው።

Chapter 4
ጉባኤው

ጉባኤው የአቅባዊ ጣዎላዎች መሰባሰቢያ ነው። ይህን የሚመስሉ ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ነበርኩ። ጥሩ በሚባል ጉባኤ ውስጥ የህዝቡ ፍላጎት ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው የግል መንፈሳዊ አካሄድ ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና በትምህርታዊ ንፅህና ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ግን ሁሉም የተለያየ መጠን ያላቸው የግለሰብ ጣውላዎች ናቸው (ለጌታ ስለመሰጠት የተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያሉ ናቸው)። ከሌሎች ጋር ኅብረት አይፈጥሩም፤ እነሱን የነካ የመሰላቸውን ሰው ያስወግዳሉ። ለብዙ ዐመታት እኔም የጉባኤ አባል ነበርኩ። ብዙ ጥሩ የሆኑ ስብከቶችን ስለሰማሁ ከእግዚአብሔር ጋር ያለኝ የግል አካሄድ መልካም ነው ብዬ አምን ነበር። ነገር ግን ዮሃንስ እንዳለው "ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?" (ዮሃንስ 4፡20)። ለዚህ ጥቅስ የጉባኤ ተካፋዮች ብዙም ትኩረት አይሰጡትም።

እዚህ ላይ ዮሃንስ የሚለው ፤ አቅባዊ ጣውላ ስላላችሁ መስቀል ያላችሁ ይመስላችኋል። ምንም እንኳን ውጫዊ ቅድስና ብታሳዩም ጉባኤው ውስጥ ካሉት ሌሎች አማኞች ጋር ኅብረት የላችሁም።


" ጉባኤ " የብሉይ ኪዳን ዘይቤ ነው

በጉባኤው ዘይቤ ወንድሞች እና እህቶች ምንም እንኳን ጓደኞች ቢሆኑም እርስ በእርስ የመንፈሳዊ ኅብረትን ስለማይፈጥሩ ብቸኞች ናቸው። እርስ በእርሳቸው በፍቅር ለመገንባባት አብረው ጊዜ አያሳልፉም። በብሉይ ኪዳን ጊዜ እስራኤል ውስጥ እንዲህ ነው የነበረው።

በእንደዚህ ዓይነት ሥርዓት ውስጥ አንደኛቸው "በጣም ትልቅ መንፈሳዊ" መሆን ስለሚችሉ ባል እና ሚስት እንኳን ኅብረት ላይኖራቸው ይችላል! ለምሳሌ ሚስት ከመጠን በላይ ልጆችን የመያዝ የሥራ ሸክም በዝቶባት ሳለ ባል ሚስቱን ከመርዳት ይልቅ "የጸጥታ ጊዜ" ኖሮት የእግዚአብሔር ቃል ያሰላስላል! እንዲህ ዓይነት ሰው የጉባኤ አስተሳሰብ ያለው ነው።

እንደዚህ አይነት ሰው በእውነቱ ክርስቲያን መሆኑም ያጠራጥራል። ይህ ሰው መጽሓፍ ቅዱስ ስለሚያነብ ፤ ስለሚጸልይ አና ለቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ስለሚሰጥ መንፈሳዊ ነኝ ፤ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነኝ ብሎ ሊያስብ ይችላል። ነገር ግን ይህ ሰው እንዲህ ካሰበ ራሱን ነው የሚያታልለው።

በውጭ በሚታዩ "ክርስቲያናዊ" እንቅስቃሴዎች ስለነበሩኝ እኔም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነኝ ብዬ በማሰብ ብዙ ክርስቲያኖችን እንደሚያደርገው በሰይጣን እኔም ተታልዬ ነበር።

ይህ የብሉይ ኪዳን ሃይማኖት ነው - የቤተ ክርስቲያን "ጉባኤ' የብሉይ ኪዳን ቃል ነው።

ሙሴ ለእስራኤላዊያን ሕግ ሲሰጣቸው ጉባኤ ነበሩ። አንድላይ ሲሰበሰቡ እንዴት ማምለክ እንዳለባቸው እግዚአብሔር ዝርዝር መመሪያዎችን በሰጣቸው ጊዜ የተለያዩ ግለሰቦች ስብሰባ ነበር። የተቀደሰ ሕይወት እንዲኖሩ እግዚአብሔር የጋበዛቸው ግለሰቦች ነበሩ።

በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እንደ ሙሴ ያሉ "ብቸኛ መሪዎች" እና እንደ ኤልያስ ያሉ "ብቸኛ ነቢያት" ነበሯቸው። ግን ሁለት መሪዎች ወይም ነቢያት አብረው ሲሠሩ ወይም እርስ በእርስ ኅብረት ሲገነቡ እና ተባብረው የእግዚአብሔርን ሥራ ባንድነት ሲሠሩ አናይም። የዚህ ዓይነት ኅብረት ሊገነባ የሚቻለው በአዲስ ኪዳን ብቻ ነው። ይህም "አዲስ ወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ" የሚለው መርህ ነው።

ብሉይ ኪዳን ጊዜ እስራኤላዊያን ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው ሕይወት ብቻ ነበር የሚንከባከቡት። ምንም እንኳን አንዳንዶቹ ቅዱሳን ቢሆኑም ከሌሎች ጋር ኅብረት አይመሠርቱም ነበር። በብሉይ ኪዳን ጊዜ የአማኞች ኅብረት አልነበረም። አንዳንዶቹ ለእግዚአብሔር መሥራት ቢፈልጉም ብቸኞች ነበሩ። በብሉይ ኪዳን አንድ ላይ ሆነው የአማኞች ኅብረትን ማቋቋም ስለልተቻለ እንደ አንድ አካል ሆነው መሥራት አይችሉም ነበር። ሲሰበሰቡ ጉባኤ ነበሩ።

አዲስ ወይን ጠጅ እና አዲስ አቁማዳ

አሁን ግን አዲስ ኪዳን በጌታ ተመስርቷል። ዳግም ስንወለድ የኢየሱስን ሕይወት - አዲሱን የወይን ጠጅ እንቀበላለን። ይህ ሕይወት በብቸኝነት (በዱሮው የወይን ጠጅ አቁማዳ) አይኖርም። ይህንን የክርስቶስን ሕይወት ወደ ራስ ወዳድ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ለማስማማት ከሞከርን ኢየሱስ እንዳለው የዱሮው የወይን ጠጅ አቁማዳ ይፈነዳል። ራስ ወዳድ የሆነ አኗኗር ማለት ከሌሎች አማኞች ጋር የአማኞችን ኅብረት ሳንፈጥር ሁልጊዜ ሰለራሳችን እና ስለ ቤተሰቦቻችን ብቻ እያሰብን መኖር ማለት ነው። እግዚአብሔር በቅዱስ መንፈሱ (በአዲሱ ወይን) ሞልቶን በአዲሱ የወይን ቆዳ (በክርስቶስ አካል) ውስጥ እንድንፈስ ይፈልጋል።

እግዚአብሔር ለእኔ ያደረገውን ስመለከት ሁላችንም እዚህ ሕይወት ውስጥ ለመግባት እንደምንችል እገነዘባለሁ። የ"ጉባኤ" ተሳታፊ ክርስቲያን በነበርኩበት ጊዜ እግዚአብሔር ምህረት አደረገልኝ፤ በሕይወቴ ውስጥ ሁሉም ነገር ተናወጦ እንዳልሆነ ሆነ። ከዚያም እግዚአብሔር አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ውስጥ አደረገልኝ። "የመናወጡ" መልካም ውጤት የአሮጌውን አቁማዳ መስወገድ ነው!

እግዚአብሔር የዱሮውን አቁማዳዬን ማፈንዳቱ መልካም ነበር፤ በዚያን ጊዜ ነው እምነቴ በምድራዊ እንጂ በሰማያዊ ነገሮች ላይ እንዳልሆነ ያስተዋልኩት። እምነቴ በሰዎች የተለምዶ ወጎች ላይ እና ቤተክርስቲያን ስለመመሥረት የነበረኝ አስተሳሰብ ደግሞ በራሴ ሀሳቦች ላይ የተመሠረቱ ነበሩ።

እግዚአብሔርን ማምለክ ብዙውን ጊዜ ለብዙ ክርስቲያኖች ውጫዊ ነገር ብቻ ነው ። በሁሉም የቤተክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ይሳተፋሉ ፣ ይጸልያሉ ፣ በአክብሮት ይቀመጣሉ ፣ በተጨማሪም ሁሉም 'ሃይማኖታዊ ቋንቋ' ይናገራሉ። እንደነዚህ ያሉት ውጫዊ ድርጊቶቻቸው መንፈሳዊ ነን ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። ግን ስለእለት ተዕለት ሕይወት ተግባራዊ ገጽታዎች ከእነሱ ጋር መወያየት አይቻልም ፣ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ውይይት "መንፈሳዊነት የጎደለው እና ዓለማዊ" አድርገው ስለሚወሰዱት! ስለ "ሃይማኖታዊ" ጉዳዮች ብቻ ማውራት ይወዳሉ። ስለ ተራ ፣ ስለዕለት ተዕለት ጉዳዮች እርስ በእርሳችን እንድንነጋገር የማይፈቅድ ሐሰተኛ ክርስትና ነው።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እና በዙሪያው ላሉት ሰዎች ሲናገር ሁልጊዜ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን እየጠቀሰላቸው አልነበረም።ያንን ያደረገው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ነው - ለምሳሌ ፣ ከሰይጣን ጋር ሲነጋገር ወይም ለፈሪሳውያን ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ። ግን አብዛኛውን ጊዜ ስለ ተራ ፣ ስለእለት ተእለት ጉዳዮች ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይነጋገር ነበር ። በጭራሽ በሐሰት መንፈሳዊነት እርምጃ አልወሰደም ወይም አልተናገረም ። በዚህ አዲሱ የወይን ጠጅ ምን እንደ ሆነ አሳይቶናል።

'ሃይማኖታዊ' ቋንቋን ሁልጊዜ መጠቀም ተመሳሳይ 'ሃይማኖታዊ' ቋንቋ ከሚናገሩ በዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር ቤተክርስቲያን እንገነባለን የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ይሰጠናል። እርስ በእርሳችን ጥቅሶችን መጥቀስ እና በስብሰባዎች ውስጥ ከእነዚያ ጥቅሶች ያገኘነውን ማካፈል እንችላለን - እናም ያ መንፈሳዊነት እንደሆነ መገመት እንችላለን። ግን ይህ የሚያመጣው መንፈሳዊ ሳይሆን ነፍሳዊ ሕይወትን ብቻ ነው።

የስንዴው እህል ወደ መሬት ውስጥ መውደቅ እና መሞት አለበት

ዛሬ ስላሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሚሰበሰቡባቸውን ሜጋ ቤተ ክርስቲያኖችን ብትመለከቱ። በውስጣቸው ፣ እርስ በእርሳቸው እውነተኛ አምላካዊ ኅብረት ያላቸው ሁለት ሰዎች እንኳን ላይኖሩ ይችላሉ። የሚያሰባስባቸው መንፈሳዊ ሳይሆን ሀይለኛ ነፍሳዊ ሙዚቃ እና አንደበተ ርቱዕ የሆነ ነፍሳዊ ስብከት ነው። ይህ የክርስቶስን አካል አያሳይም። እነዚህ በተናጥል ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ስለሚኖራቸው ግንኙነት የሚያስቡ አቅባዊ ጣውላዎች ናቸው። ይህ ራስን ማታለል ነው እንጂ አግዳሚ ጣውላ ስለሌለበት መስቀል አይሆንም።

ዮሃንስ 12፡24 ላይ ኢየሱስ "የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች" አለ። ለዘለዓለም የሚቆይ እውነተኛ ፍሬ ሊመጣ የሚችለው እንደ ስንዴው ፍሬ የራሳቸውን ትተው ለሚሰዉ ብቻ ነው። አሥር ሺ የእህል ፍሬዎች በወርቅ ብልቃጥ ውስጥ ተቀምጠው ለተመልካች አስደናቂ ሊሆኑ ይችላሉ። በሺ የሚቆጠሩ የዚህ ዓይነት ስንዴዎች በሜጋ-ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ጎን ለጎን ተቀምጠው ማየት ይቻላል። ያንን ባየሁ ጊዜ ይመስለኛል ፣ "ከእነዚያ እህሎች መካከል ሁለቱ እንኳን ራሳቸው ላይ ማተኮርን ተተው ኅብረት ለመፍጠር ፈቃደኞች ቢሆኑ ኖሮ እግዚአብሔር እዚያ በሚገኙ ቅሪቶች መካከል በአካባቢያቸው የክርስቶስን አካል በእውነት ማሳየት የሚችል ሥራ መጀመር ይቻል ነበር"።

በምድር ላይ ወድቆ ለመሞት ፈቃደኛ ያልሆኑ የስንዴ እህል የሆኑ ሰዎችን በቤተክርስቲያናችን ከመሰብሰብ እግዚአብሔር ያድነን። እግዚአብሔር የሚጀምረው መሬት ላይ ወድቆ ለመሞት ፈቃደኛ በሆነው በአንድ ስንዴ ነው። ከዚያም አንድ በአንድ እያለ በየጊዜው ቁጥራቸው ይጨምራል። ቤተክርስቲያን የተራበ ዓለምን መመገብ የሚችል የክርስቶስ አካል ሆና የተገነባችው በዚህ መንገድ ነው። ንገር ግን ለራሳቸው ብቻ የቆሙ የስንዴ እህሎች በዓለም ላይ ለተራቡት እና ለተቸገሩት መፍትሄ ይመስላሉ እንጂ መፍትሄ ሊሆኑ አይችሉም - ከእውነተኛ ዳቦ ይልቅ የዳቦ ሥዕሎች ናቸው። ኢየሱስ አንድ የስንዴ እህል መሬት ላይ ወድቆ ሲሞት (በእርግጠኝነት) ብዙ ፍሬ እንደሚያፈራ ተናግሯል።

አንድ የስንዴ ፍሬ በጣም ትንሽ ስለሆነ በጣቶቻችሁ መካከል ብትይዙት አይታይም። በየጊዜው በግል የሚትገናኙ ፤በሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባላት የተናቃችሁ እና ብዙም የማትታወቁ ግሩፖች ልትሆኑ ትችላላችሁ። ተስፋ አትቁረጡ። ሌሎች በዙሪያችሁ ያሉ ሌሎች ሜጋ-ቤተ ክርስቲያኖች ስለ ሥራቸው አስገራሚ ዘገባዎችን የሚሰጡ እና ከፍተኛ ደሞዝ የሚያገኙ እና የሚያማምር መኪናዎችን የሚነዱ ታዋቂ ፓስተሮች ሊኖራቸው ይችላል። የፈለጉትን ያድርጉ። አትቅኑባቸው። ጥሪያችን እንደ ስንዴዋ ዘር መሬት ውስጥ ወድቆ መሞት ነው። ጌታ ለዘላለም የሚኖር ፍሬ ከእኛ ያወጣል። ይህ የእርሱ የሰጠን ተስፋ ነው። ይህ እውነተኛው ቤተክርስቲያን የመገንባት ምስጢር ነው።

Chapter 5
ክበቡ

ክበብ የጉባኤ ተቃራኒ ነው።

ቀደም ብሎ እንዳየነው ጉባኤው የተለያዩ መጠን ያላቸው ጎን ለጎን የተደረድሩ አቅባዊ ጣውላዎችን ያካትታል። ለጌታ የመሰጠት መጠናቸው ላይ የአንዳንዶቹ ከፍ ያለ ሲሆን የሌሎቹ ደግሞ አነስተኛ ነው። ነገር ግን እርስ በእርሳቸው የአማኞች ኅብረት የላቸውም። ክበቡ ግን እርስ በእርሱ የሚተሳሰሩ ሰዎችን ያቀፈ ነው። ራሳቸውን ከሌላ ጉባኤዎች ጋር በማወዳደር "በመሃላቸን መልካም ግንኙነት ስላለ መንፈሳዊዎች ነን" ብለው ስለሚገምቱ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እርስ በእርሳቸው በጥሩ ሁኔታ ይነጋገራሉ እናም እርስ በርሳቸው ጥሩ ኅብረት እንዳላቸው ያስባሉ። እንግዲያው ሁሉም በአስተምህሮት አንድ ስለሆኑ ሁሉም መንፈሳዊ እንደሆኑ ይገምታሉ፣ ተመሳሳይ ልብስም ይለብሳሉ፣ ወዘተ። ነገር ግን አሁንም ሁሉም በጣም አንድ ዓይነት የሆኑ የእንጨት ጣውላዎች ናቸው!


ክበቡ "ኪዳን-አልባ" ሃይማኖት ነው

አንዳችን ከሌላው ጋር የሚኖረንን አግድም ግንኙነቶች አስፈላጊነት አውቀን እዚያ ላይ ስናተኩር የሚገጥመን ትልቁ አደጋ ክበብን መመሥረት ነው። ከእኛ ጋር እንዲቀላቀሉ የምንጋብዛቸው ሌሎች ሰዎች ሁሉም እኛን የሚመስሉ፣ እንደኛ የሚናገሩ እና እንደ እኛ ናቸው ብለን የምንገምታቸው ናቸው። ስለዚህ ተመሳሳይ የሆኑ ሰዎች ያሉበት ክበብ እንሆናለን - ወይም ፣ አንዳንዶች እንደሚሉት ፣ "ኩኪ-ቆራጩ ክርስቲያኖች"- ሁሉም አስተያየታቸው፣ አስተሳሰባቸው እና አኗኗራቸው ተመሳሳይ ነው።_ ህብረታቸው የሚመሠረተው አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ ቋንቋ በመናገራቸው ላይ ነው።

እውቀታቸው ከእኛ እውቀት ጋር ተመጣጣኝ ከሆነ ከሌላ ማህበረሰብ እና ሌላ ቋንቋ ካላቸው ሰዎች ጋር እንኳን መስማማት እንችል ይሆናል። ነገር ግን ሌላ ወንድም ቤተክርስቲያናችን በጣም ያልተማረ እና የእኛን አስተምህሮቶች ጠንቅቆ የማያውቅ ከሆነ እና ከእኛ ጋር መቀላቀል ከፈለገ ከእርሱ ጋር መስማማት ይከብደን ይሆናል። ስለዚህ አናቀርበውም፣ ከጊዜ በኋላ ጥሎ ይሄዳል። ይህም የሚሆነው እኛ በአእምሮአችን የቀረጽነው እና ለእኛ ተቀባይነት ያለው ሰው ስላልሆነ ነው። የእንደዚህ ዓይነቱ ክበብ የብሉይ ኪዳን ወይም የአዲስ ኪዳን ኅብረት አይደለም - ኪዳን አልባ ነው።

ጉባኤው በብሉይ ኪዳን ላይ የተመሠረተ ፣ ለእግዚአብሔር በውስን የተሰጠ እርስ በርስ የጋራ ኅብረት ያልነበረው ነበር። ይህን ተገንዝቦ እንደዚህ ላለመሆን ከነጭራሹ ቃል ኪዳን በሌለበት ሕይወት ውስጥ ልትገቡ ትችላላቸሁ። ብዙ ክርስቲያኖች እንደዚህ ናቸው። እነሱ እግዚአብሔር ከብሉይ ኪዳን እና ከህግ ነፃ እንዳወጣቸው ይሰማቸዋል እናም በመጨረሻም ቃልኪዳን አልባ ይሆናሉ። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች የጻፈውን ደብዳቤ ይወዳሉ ፣ "ከሕግ ነፃ" ስለመሆን ያለውን ትምህርት በተሳሳተ መንገድ ስለሚያዩ ምንም ዓይነት ቃል ኪዳን አይፈልጉም። ነገር ግን ያለ ኪዳን ከክርስቶስ ጋር ጋብቻ ሊኖር አይችልም።

እኔና ባለቤቴ ስንጋባ ቃል ኪዳን ገባን። ምንም እንኳን የትዳር አኗኗር ደንብ መጽሐፍ ባይኖርም ፣ አንዳንድ በፍቅር ላይ የተመሰረቱ ህጎች አሉ። ለምሳሌ-በእግዚአብሔር ቸርነት ሚስቴን በጭራሽ አላጭበረብርም። ይህም የሆነበት ምክንያት በጋብቻ መጽሐፍ ውስጥ "ከተጋባችሁ ብኋላ እንዲህ አድረጉ ወይም እንዲህ አታድርጉ" የሚል ትእዛዝ ስላለ አይደለም። እኔ ስለምወዳት ለባለቤቴ ታማኝ ነኝ። እሷን ስለወደድኳት እሷን የሚጎዳ ማንኛውንም ነገር ማድረግ በፍጹም አልፈልግም። እንደዚሁም ከክርስቶስ ጋር በትዳራችንም ውስጥ እርሱ በመጀመሪያ ስለወደደኝ እና እኔም በሙሉ ልቤ ስለወደድኩት አንዳንድ ሕጎች አሉ። ከእሱ ጋር ያለኝ ግንኙነት በፍቅር ላይ ነው እንጂ የሕግ መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ አይደለም።

ክበቡ ግን ብዙ ሕጎች አሉት። የክበቡ አባል መሆን ከፈለጋችሁ የተወሰኑ መስፈርቶችን ማሟላት አለባችሁ። እነዚህም መስፈርቶች ሰው ሠራሽ የሆኑ ከእግዚአብሄር ሕጎች ውጭ ናቸው።

ከእግዚአብሔር ኪዳን ሥር ካልሆናችሁ ከሌሎች ሰዎች ጋር ኅብረት የምትፈጥሩበትን የራሳችሁን ኪዳን ትፈጥራላችሁ። "መልካም ስታደርግልኝ እኔም መልካም አደርግልሃለሁ፤ በጥሩ ሁኔታ ከያዝከኝ እኔም በጥሩ ሁኔታ እይዘሃለሁ። ግን በጥሩ ሁኔታ እኔን መያዝ ስታቆም ግኑኘታችን ያበቃል።" ብዙ አማኞች ከሌሎች ጋር እንደዚህ ዓይነት ግንኙነት ነው አላቸው።

ሆኖም ክበቡ አንዳንድ ምድራዊ መብቶችን ይሰጣችኋል። "በቤተክርስቲያን ስብሰባዎች" ላይ መሳተፍ ትችላላችሁ ፣ ልጆቻችሁ እዚያ ካሉ ሌሎች ጥሩ ልጆች ጋር መገናኘት ይችላሉ ፣ የጋብቻ አገልግሎት ማግኘት ትችላላችሁ ከዚያም ጊዜው ሲደርስም መልካም የቀብር ሥነ ሥርዓትም ማግኘት ትችላልችሁ !!

የክበብ ሕይወት ወደ አደጋ ይመራል

አማኞች እርስ በእርሳቸው እንደዚህ ያለ ወዳጅነትን ሲመሠርቱ የአግድሚ ጣውላዎች መሰባሰብ ይሆናል። አንዳንዶቹ ለክርስቶስ ትንሽ መሰጠት ሊኖራቸው ይችላል ፣ ሆኖም አቅባዊ ጣዎላው በጣም ትንሽ ነው። በአብዛኛዎቹ ሁኔታዎች አቀባዊ ጣዎላ አይኖርም።

በባለቤታችሁ ወይም በሌሎች ሰዎች ተጎትታችሁ ነው ወደ "ቤተክርስቲያን" መሳተፍ የጀመራችሁት? ጥሩ ስብከቶችን ስለምትሰሙበት ወይም "የክበቡን ድባብ" ስለወደዳችሁ እና በሚያስፈልግ ጊዜ አባላት ስለሚደርሱላችው ነው የተቀላቀላችሁት?

የሰማችሁት ጥሩ ስብከት ስለገባችሁ ብቻ መንፈሳዊ ነን ብላችሁ በቀላሉ ራሳችሁን ማታለል ትችላላችሁ። በተጨማሪም በእናንተ "ቤተክርስቲያን" ውስጥ ያለው ትምህርት በሌሎች "ቤተ ክርስቲያኖች" ከሚገኘው የላቀ ነው ብላችሁ ስለምታስቡ ራሳችሁን መካብ እና ማስደሰት ትችላላችሁ። ሆኖም ለክርስቶስ መሰጠት ያለው አቅባዊው ጣውላ በሕይወታችሁ ላይኖር ይችላል። እንደዚያ ከሆነ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ስትቀርቡ በአጠቃላይ ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጭ መሆናችሁን ስትገነዘቡ አሳዛኝ አስገራሚ ሁኔታ ይሆናል!

በአየር ማረፊያዎች የደህንነት ፍተሻ ቦታ ላይ ተሳፋሪዎች ሻንጣቸውን የሚጭኑበት የማጓጓዥያ ቀበቶ አለ። እነዚህ ሻንጣዎች በደህንነት ፍተሻ ውስጥ አልፈው በመጨረሻም በሌላኛው በኩል ይወጣሉ። የክርስቶስ የፍርድ ወንበር በተወሰነ መልኩ ከዚህ ጋር አመሳስለዋለሁ። ነገር ግን በፍተሻ መሳሪያው ቦታ ትልቅ እሳት ይኖራል! እናም እግዚአብሔር የሕይወታችንን ድርጊቶች በሙሉ በዚህ እሳት መሃል ያሳልፋል። በሌላው በኩል የሚወጣው ነገር የሚወሰነው በምድር ሳለን የኖርነው ሕይወታችን ነው። በ1ኛ ቆሮንቶስ 3፡13-15 እንደተጻፈው የብዙ አማኞች ሥራ ሁሉ እንደ እንጨት፣ ጋለባ እና ጭድ ስለሆነ ሁሉም ይቃጠላል። በሌላው በኩል ምንም ነገር አይወጣም። ብዙዎች ጥሩ በሚባሉ ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ለዓመታት የተቀመጡ በዚያን ቀን መላ ምድራዊ ሕይወታቸውን እንዳባከኑ ይገነዘባሉ።


ለዓመታት በጥሩ "ቤተ ክርስቲያኖች" ተሳትፈው አስደናቂ ስብከቶችን የሰሙ (በ"ቤተክርስቲያናቸው" ወይም በኢንተርኔት) ለብዙዎች ጌታ እንዲህ ይላቸዋል፣ "ምድራዊ ሕይወታችሁ በከንቱ ነበር፣ ለእኔ የተሰጣችሁ ስላልነበራችሁ። እኔ መቼም 'አላውቃችሁም' እኔንም 'አታውቁም'፣ በጭራሽ ከእኔ ጋር አልተጓዛችሁም፣ መስቀሉንም ተሸክማችሁ አታውቁም'(ማቴዎስ 7 22-23)። ይህ እጅግ እጅግ የሚያሳዝን ይሆናል።

ደህንነት በጌታ ወይስ በቤተክርስቲያን?

በምድር ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለእኔ በጣም አስደሳች ስፍራ ናት። ይህን የምለው ከልቤ ነው። የቅዱሳን ኅብረት በጣም ጣፋጭ ነው። ይህም ሆኖ ከሰማያዊ አባቴ እና ከጌታ ከኢየሱስ ጋር ካለኝ ኅብረት ምንጊዜም አይበልጥብኝም። ከኢየሱስ እና ከአብ ጋር ያለኝ ኅብረት በምድራዊ ህይወቴ በሙሉ ሳይቋረጥ ለዘለአለም ይቀጥላል። ይህ የጸና ኅብረት በምድር ላይ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ኅብረት እንዲኖረኝ ያስችለኛል።

በክበቡ ውስጥ ያሉ ሰዎች ግን ደህንነታቸውን የሚያገኙት ከክበባቸው ነው እንጂ ከጌታ አይደለም። ጌታን የሚያገለግሉ ሰዎችን ስብከት ስላዳመጡ ደህንነት ያገኙ ይመስላቸዋል። በዚህ ዓመት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስብከቶችን አዳምጣችሁ ይሆናል። ንይህ ገር ግን ይህ እውነተኛ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር አያደርጋችሁም።


በክበቡ ውስጥ ያሉትም እንዲሁ በእንክብካቤ ካልተያዙ በቀላሉ ይከፋሉ። ከሰዎች ክብርን እና ሞገስን ይፈልጋሉ። በሰዎች መሃል በይፋ እና በጥሩ ዐይን መታየተን ይሻሉ። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የእርማት ቃል ቢሰጣቸው ወዲያውኑ ይበሳጫሉ ፣ በመጨረሻም ክበቡን ይተዋሉ! አንድ አምላካዊ ፣ ታላቅ ወንድም ሲገሥጸኝ ቅር ከተሰኘሁ የ"ክበብ" ክርስቲያን መሆኔን እንደሚያረጋግጥ ጌታ አሳይቶኛል። ሌሎች በዙሪያዬ ያሉ የክርስቶስን እውነተኛ ሕይወት እየተለማመዱ ሊሆን ይችላል። ግን ለዓመታት በመካከላቸው ተቀምጬ ጥሩ የክበብ አባል ብቻ እንደሆንኩ የምረዳው በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ስቀርብ ሊሆን ይችላል። በእርማትም ሆነ በተግሳጽ ከመከፋት እግዚአብሔር ያድነን።

እግዚአብሔር የሚወዱን እና ቃሉን በፍቅር የሚነግሩን ሽማግሌዎችን ሰጥቶናል። ልጆቻቸውን የሚወዱ አባቶች በትሩን እንደማይለቁ ሁሉ እነሱም እንዲሁ በትሩን አይለቁም። እንደነዚህ ያሉት ሽማግሌዎች የሰማዩ አባታችን እንደሚወደን ይወዱናል። እንግዲያው እንደዚህ አምላካዊ አረጋዊ ወንድሞች በሚነግሯችሁ ነገር ላይ ካመጻችሁ ወይም ከተከፋችሁ የክበብ አስተሳሰብ እንዳላችሁ እርግጠኛ ምልክት ነው።

የመጨረሻው ውጤት የመንፈሳዊ እድገት እጦት ይሆናል። በህይወታችሁ ውስጥ ምንም የመንፈሳዊ እድገት ከሌለ ወደኋላ እየተመለሳችሁ ነው ማለት ነው። በክርስቲያን የሕይወት ጉዞ ቋሚነት የለም። አንድ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ወንድም የተግሣጽ ቃል ሲነግረን ቅር ከተሰኘን በእርግጥ ወደ ኋላ የመመለስ ሁኔታ ላይ እንደሆንን ያሳያል - ምናልባት ወደ ገሃነም አያመራንም ይሆናል።

ለኛ ስላለው ፍቅር የተነሳ ስለሆነ የሰማያዊ አባታችንን ተግሣጽ እንድንወድ ዕብራውያን 12፡5-8 ይነግረናል። ጳውሎስ በ​​1ኛ ቆሮንቶስ 4፡15 እንደሚለው በቤተክርስቲያን ውስጥ የአባት ልብ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም እንዳትወድቁ እና ወደ ኋላ እንዳትቀሩ ያርሟችኋል። በዚህ እርማት የተነሳ ከተከፋችሁ የክበብ አስተሳሰብ እንዳላችሁ ያረጋግጣል። በመጨረሻ ወደ ጥፋት ይመራችኋል።

Chapter 6
እውነተኛው ቤተ ክርስቲያን

በአዲስ ኪዳን ውስጥ በብሉይ ኪዳን በጭራሽ የማይገኙ አዲስ የሆኑ በርካታ ቃላቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ "የአማኞች ኅብረት" ነው።

በበዓለ ሃምሳ ቀን ፣ ሶስት ሺህ ሰዎች በድጋሚ በታላቅ ተሃድሶ በተወለዱበት ጊዜ ለሚቀጥሉት አስር ቀናት የድንኳን ተክለው የተሃድሶ ስብሰባዎች አላደረጉም። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የሚያደርጉት ይህን ነው! ይልቁንም እግዚአብሔር እነዚያን ደቀ መዛሙርት "የተሃድሶውን ስብሰባ" እንዲዘጉ እና ሄደው ቤተክርስቲያንን እንዲገነቡ ነገራቸው።

በሐዋርያት ሥራ 2፡42 ላይ "ለኅብረት ራሳቸውን እንደሰጡ" እናነባለን። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚታየው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው! (ማስታወሻ፡ በመዝሙር 55፡14 ውስጥ "ኅብረት" ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል "ምክር" እንጂ "ኅብረት" ማለት አይደለም)


ከመስቀሉ የሚፈሰው ፍቅር

ይህን ኅብረት ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞሉ ወዲያውኑ ነበር ያገኙት። ዛሬ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ተሞላን ሲሉ "በልሳን ተናገርኩ" ወይም "ለታመመ ሰው ጸለይኩ እርሱም ተፈወሰ (የተፈወሰ ይመስለኛል!)" ፣ ወይም "እኔ አሁን አንደበተ ርቱዕ ሆኜ እሰብካለሁ" ወዘተ ነው የሚሉት።

ነገር ግን በበዓለ ሃምሳ ቀን በመንፈስ ቅዱስ በተሞሉበት ጊዜ እነዚያ አማኞች ከተሐድሶው ስብሰባ ወጥተው እርስ በእርሳቸው ኅብረት እንደመሠረቱ እናነባለን (የሐዋ 2፡42)። ይህ በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ዋናው ውጤት መሆን አለበት።

1ኛ ቆሮንቶስ 12፡13 "ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል" ይላል። እዚህ ላይ ቤተክርስቲያን የተገለጸችው እንደ ጉባኤ ወይም እንደ ክበብ ሳይሆን እንደ አካል ነው። "እናንተ የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም የአካል ብልቶች ናችሁ" (1ኛ ቆሮንቶስ 12 27)።

ይህ አካል የተገነባው በመስቀል ላይ ነው። ይህ የወይን አቁማዳ የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ነው።

ጉባኤው የብሉይ ኪዳን ፅንሰ-ሀሳብ ነው።

ክበቡ በጭራሽ ቃል ኪዳን የለውም።

እውነተኛው ቤተክርስቲያን ግን የተገነባችው በአዲሱ ኪዳን መሠረት ነው።

ቃል ኪዳን የሚለውን ቃል በአሁኑ ጊዜ ብዙ አንጠቀምም። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን በሚገነቡት መካከል ስምምነት እና ቁርጠኝነት ማለት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ለሙሽራው ቃል ገብተዋል ከዚያም እርስ በእርሳቸው ቃል ገብተዋል። እዚህ ላይ አቀባዊውን እና አግዳሚውን የመስቀል ጣውላዎች ታያላችሁ። በመጀመሪያ ጌታን ከልብ ይወዳሉ ፣ ከዚያ በኋላም እርስ በርሳቸው ይዋደዳሉ።

በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ "የጌታ ራት" ስንካፈል ከጌታ ጋር ኅብረት እንዳለን እና እንደ እሱ ለራስ መሞትን እንደምንፈልግ ነው የምናሳየው (1ኛ ቆሮንቶስ 11፡26-28)። በተጨማሪም እንደ አንድ አካል ብልቶች ልዩ ልዩ ብንሆንም እርስ በርሳችን ኅብረት እንዳለን እንገልፃለን (1ኛ ቆሮንቶስ 10፡16, 17) ለዚህም ነው ሁላችንም አንድ ዳቦ የምንካፈለው።

አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅር ሰዎች በተለምዶ እንደሚዋደዱት ማለትም - "እኔ እወዳችኋለሁ ፣ እናንተም ትውዱኛላችሁ፣ ስለዚህ እኛ ደስተኛ ቤተሰብ ነን!" ማለት አይደለም። ይህ ፍቅር የሚመነጨው ለጌታ ካለን ፍቅር ነው። እንደዚሁም ወንጌልን ላልሰሙ ማሰማት የሚገፋፋን ላልዳኑት ያለን ፍቅር ሳይሆን ዋና መነሻው ለጌታ ያለን ፍቅር ነው።

ይህ ለጌታ እና ለሎች ያለን ፍቅር ነው መንፈስ ቅዱስ በልባችን የሚያፈሰው (ሮሜ 5፡5)።

እውነተኛውን ቤተክርስቲያን መገንባት

አባቴ (ዛክ ፑነን) በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን መሃከል ያለውን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ልዩነት ይህን ምሳሌ ተጠቅመው ያስረዱ ነበር። በብሉይ ኪዳን ጊዜ የሰው ልብ ከዳን እንዳለው ጽዋ ነበር (ይህም በአይሁድ ቤተመቅደስ ውስጥ በጣም የተቀደሰውን ስፍራ ከጋረደው መጋረጃ ጋር ይማሰላል)። ጽዋው ስለተከደነ መንፈስ ቅዱስ በጸዋው ክዳን ላይ እና በጽዋው ውጭ ፈስሶ ከጽዋው ውጭ የበረከት ወንዞች ወደ ብዙ ሰዎች ፈሰሰዋል - በሙሴ ፣ በመጥምቁ ዮሐንስ ፣ ወዘተ እንዳደረገው።

በአዲሱ ኪዳን ግን የጸዋው ክዳን ተነስቷል (2ኛ ቆሮንቶስ 3፡12-18)። በቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረው መጋረጃ ኢየሱስ ሲሞት በመቀደዱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ መግባት ተቻለ። አሁን በአዲስ ኪዳን መንፈስ በሚፈስበት ጊዜ መጀመሪያ ጽዋው ይሞላል - በመጀመሪያ የአማኙን ልብ ያነፃል - ከዚያም በዮሐንስ 7፡37-39 ውስጥ ኢየሱስ እንዳብራራው ለብዙዎች በረከት "ከውስጥ ማንነቱ" ይወጣል። የአዲሱ ኪዳን ቤተክርስቲያን እንደዚህ ነው የተገነባችው።

መንፈስ ቅዱስን ብቻ ተጠቅመን የምንሰብክ ከሆነ ጉባኤ ወይም ክበብ ውስጥ ነን ማለት ነው። ነገር ግን አስቀድመን እግዚአብሔር ልባቸንን በፍቅሩ እንዲሞላን ካደረግን፤ እኛን ሞልቶ ከውስጣችን ለሌሎች ፈቅሩ እንዲፈስ ያደርጋል። ይህ ሲሆን ተመሳሳይ የኅብረት መንፈስ ካላቸው ጋር ቤተክርስቲያንን እንገነባለን። ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ያለን ፍቅር በልባችን ሞልቶ እያንዳንዳችን መስቀሉን ስናነሳ እውነተኛ የመንፈስ አንድነት ይገነባል።

በመሠረቱ እውነተኛው ቤተክርስቲያን በዋነኝነት የምትገነባው አንዳችን ከሌላችን ስንርቅ ነው። በእሁድ ስብሰባዎቻችን ላይ አንድ ላይ ስንሰባሰብ ብቻ አይደለም ቤተክርስቲያን የሚመሠረተው። በእርግጥ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ነው የሚመሠረተው። ሆኖም አንዳችን ከሌላው ስንርቅ በበለጠ ይመሠረታል። የኢየሱስ ቤተክርስቲያን አባል መሆናችን የሚያረጋገጠው በልዩ ልየ መንገዶች በምንፈተንበት ጊዜ ነው። ለምሳሌ - ሐቀኝነታችን ፣ ለመናደድ መሰጠታችን፣ ወይም ያየነውን መመኝታችን ፣ ወዘተ ሲፈተን ነው። በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ መስቀላችንን ከያዝን ፣ ለራሳችን የምንሞት ከሆነ፣ ለጌታ ያለንን አምልኮ የምንጠብቅ ከሆነ እና ኃጢአትን የምንቋቋም ከሆነ በብርሃን ውስጥ ነን ማለት ነው። ይህም ስለሆነ ከጌታ ጋር ኅብረት እናደርጋለን ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ ከሌሎች ጋር ስንገናኝ እርስ በርሳችን እውነተኛ ኅብረት ይኖረናል (1ኛ ዮሐ 1፡7)።

ቆላስይስ 2:2 ስለ ልባችን "በፍቅር መተባበር" ይናገራል። እራሴን በፍቅር ከሌሎች ጋር ማያያዝ አልችልም። ልባችንን አንድ ላይ ማስተባበርን የሚችለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው። ልቤን በእኔ አስተሳሰብ አንድ ችሎታ ለሌሎች መልካም በመሆን እና ስጦታዎችን በመስጠት ፣ ወይም አብሬ ጊዜ በማሳለፍ ፣ ወዘተ ልቤን ከሌሎች ጋር ለማጣመር ብሞክር የምመሠርተው ክበብ ነው እንጂ ቤተክርስቲያን አይሆንም። እግዚአብሔር "በቃ ለራስህ ብቸኛ ፍላጎት ሙት" ይላል። ይህንን ካደረግሁኝ መንፈስ ቅዱስ በማይታይ ፣ ከተፈጥሮ በላይ በሆነ መንገድ በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ካሉት እና 'ለብቸኛ ፍላጎታቸው ከሞቱት' ጋር ልቤን ያስተባብራል።

በዚህ ሁኔታ የተመሠረተ ኅብረት ይሆናል። ይህም የሚሆነው ተመሳሳይ አስተምህርቶችን ስለምናምን ወይም አንድ አይነት መዝሙሮችን ስለምንዘምር ሳይሆን ሁላችንም 'የግል/ብቸኛ ፍላጎታችን' ስለ ሞተ ነው። አሁን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ እርስበርስ ኅብረት እንገባለን።

የግል አና ብቸኛ ፍላጎቶቻችንን ሳንጥል የምንመሠርታችው ማንኛውም አንድነቶች ከሌሎች ጋር ወዳጅነትን ይፈጥራሉ እንጂ የክርስቲያኖች ኅብረት አይሆኑም። የአማኞች ኅብረት መንፈሳዊ ሲሆን ወዳጅነት ግን አለማዊ ነው።

በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ወዳጅነት አላቸው። የብዙ ዓለማዊ ክበብ አባላት እርስ በርሳቸው በጣም የጠበቀ ወዳጅነት ስላላቸው እርስ በእርሳቸው በጣም ይንከባከባሉ። ነገር ግን እውነተኛ ኅብረት በፍጹም ሊኖራቸው አይችልም። ይህም የሚሆንበት ምክንያት የአማኞች ኅብረት ሊኖር የሚችለው መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን ሲሰራ ብቻ ስለሆነ ነው። ማንኛውም የእግዚአብሔር ልጅ "በሰውነቱ ውስጥ የኢየሱስን መሞት ተሸክሞ" ሲታይ እግዚአብሔር ለዚህ ሰው የበልጠ "የኢየሱስን ሕይወት" ይሰጠዋል (2ኛ ቆሮንቶስ 4፡10,11)። ይህ "የኢየሱስ ሕይወት" በሁለት አማኞች መካከል እውነተኛ ኅብረትን የሚያመጣው። እንደዚህ ካሉ ሰዎች ጋር እግዚአብሔር የአዲስ የኪዳን ቤተክርስቲያን ይገነባል።

እነዚህን እውነቶች ማየት ስጀምር ጌታን "ጌታ ሆይ እውነተኛ ቤተክርስቲያንህን መገንባት የሚፈልጉ ሰዎች የት አሉ?" እያልኩ ጌታን መጠየቄን አቆምኩ። እግዚአብሔር እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን እንደሚያገኝ እና አንድ እንደሚያደርገን ተገነዘብኩ - ይህን ለማድረግ እኔ ራሴ በመጀመሪያ ዝቅተኛ ቦታ ወርጄ የራሴን ፍላጎት ለመተው ፈቃደኛ መሆን አለብኝ። ይህን ማድረግ ካልፈለግሁኝ ግን እግዚአብሔር ከእነዚህ አማኞች ጋር አንድ አያደርገግኝም።

በአካባቢያችን በሙሉ ልባቸው አማኝ የሆኑ ክርስቲያኖችን አማኞችን ለማግኘት መሞከር ከሣር ክምር ውስጥ አንድ መርፌ ለማግኘት እንደመሞከር ነው። በሣር ክምር ውስጥ ያሉትን ጥቃቅን መርፌዎች ስንፈልግ ብዙ ዓመታትን ልናሳልፍ እንችላለን ፤ እና ምናልባትም ከብዙ ጥረት በኋላ አንድ መርፌ ማግኘት እንችላለን። ጌታ ግን "እነዚያን መርፌዎች በመፈለግ ጊዜያችሁን አታባክኑ ያሉበትን እኔ አውቃለሁ እናንተ የግላችሁን ፍላጎት ትታችሁ ለራሳችሁ ሙቱ" ይላል ። ይህን ስታደርጉ በውስጣችሁ ያለው የኢየሱስ ሕይወት እነዚያን "መርፌዎች" (በሙሉ ልባቸው ደቀ መዛሙር የሆኑ) እንደማግኔት ይስባቸዋል (ዮሐ 1፡4, 12፡32)።

ሌሎች ጌታን ተከትለው መኖር እና የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ለመመሥረት የሚሹ ወደ እናንተ እና እናንተ ወደ ምታስተምሩት ወደ መስቀሉ መለእክት ይመጣሉ። ይህ የእግዚአብሔር መንገድ ነው ። እርሱ በሙሉ ልባቸው የሚያምኑትን ወደ እኛ ያመጣል። "አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣሉ" ሲል በዮሐንስ 6፡37 ላይ ኢየሱስ ተናግሯል።ለእኛም አብ እንዲሁ ያደርግልናል። አዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያንን የምንገነባው በዚህ መንገድ ነው።

ስለ ግል መስዋእትነት

በኤርምያስ 3፡14 ላይ ጌታ "አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤ እንደ ልቤም በግ ጠባቆችን እሰጣችኋለሁ" ይላል። ይህ አስደናቂ ተስፋ ነው። ወደ እውነተኛው ቤተክርስቲያን መምጣታችሁን የምታውቁት የእግዚአብሔርን ልብ የሚሹ እረኞችን ስታገኙ ነው። አላማቸው እናንተን ወደ እግዚአብሐር ለመምራት ስለሆነ እነደነዚህ ያሉ መሪዎችን አክብሩ፣ ሲያርሙዋችሁም አትከፉ።

ኤፌሶን 5:25 "ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ስለ ወደደ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ይናገራል። ያለ መስዋእትነት ቤተክርስቲያንን መገንባት አይቻልም። ኢየሱስ ከሰማይ ወደ ምድር ሲመጣ የከፈለው ታላቅ መስዋእትነት ነበር። ምቾትን መስዋእት አድርጎ በድህነት ውስጥ ኖረ። ከዚያም በላይ ደግሞ ራሱን ሰጠ።

ዋጋ ሳትከፍሉ አዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን እንመሠርታለን ብላችሁ አታስቡ። ቤተክርስቲያንን ለመመሥረት የሚትፈልጉ ነገር ግን ማንኛውንም የገንዘብ ወይም የግል ምቾትን መስዋእት ማድረግ የማትፈልጉ ከሆነ፣ የምትመሠርቱት ጉባኤ ወይም ክበብ ብቻ ነው። እውነተኛው ቤተክርስቲያን ያለ መስዋእትነት መመሥረት አይቻልም። ክርስቶስ ቤተርስቲያንን ለመመሥረት ራሱን እንደ ሰጠ። እኛም እኛ ከእሱ ጋር ተባብረን ለመመሥረት "ራስን ፍላጎት/ጥቅም" መተው አለብን።

በሰዎች አስተሳስብ የተናቀ እና ሌሎች ያጥላሉት ማንኛውም ሰው እራሱን በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለመሞላት ፈቃደኛ ከሆነ እና በመስቀሉ መንገድ የሚሄድ ከሆነ ጌታ ይህን ሰው ተጠቅሞ ቤተክርስቲያንን ለመመሥረት ይችላል።

በራሳችሁ ዓይን ትንሽ ከሆናችሁ እግዚአብሔር ዛሬ "አንተ ትንሽ ፣ ትንሽ ዋጋ ያለው የስንዴ እህል ነህ ፣ ሂድና መሬት ውስጥ ወድቀህ ሙት" ይላችኋል። ይህን ስታደርጉ እግዚአብሔር በእናንተ በኩል የሚያደርገውን ተአምር ታያላችሁ። እግዚአብሔር ለእናንተ እና እናንተን ተጥቅሞ ለወድፊት ሊያደርግ ያዘጋጀውን ዛሬ ለማየትም ሆነ ለማሰብ አትችሉም (1ኛ ቆሮንቶስ 2፡9)። ነገር ግን በዚህ መጽሐፍ በኩል ወደ እናንተ የሚመጣውን ጥሪ ለመስማት እግዚአብሔርን አጥብቃችሁ መውደድ አለባችሁ።

Chapter 7
ቤተክርስቲያንን መገንባት - ሰጪ መሆን

" እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም " ( ማቴዎስ 20:28).

ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የእርሱ "ቤተክርስቲያን" እጅግ በጣም ትንሽ ነበር። አሥራ ሁለት ሰዎች ነበሩት ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ይክደዋል። ከከሃዲው ሌላ የቀሩት ግን ኢየሱስን ለመከተል ሁሉንም ነገር የተዉ፣ እውነተኛ ደቀመዛሙርት ነበሩ። ስለዚህም በመንፈስ ቅዱስ ከተሞሉ በኋላ ዓለምን ለወጧት።

ከመቀየራቸው በፊት ግን ብዙውን ጊዜ እርስ በርሳቸው ይጨቃጨቁ ነበር። አንድ ጊዜ ኢየሱስ እንደሚሰቀል ሲነግራቸው ደቀ መዛሙርቱ - አንድ መሪ ​​ከቦታው ሲወጣ ማንኛውንም ምድራዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው እንደሚያደርገው ወዲያውኑ በሱ ምትክ ማን መሪ እንደሚሆን ክርክር ጀመሩ (ማርቆስ 9፡31-34)።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ እንደሚሰቀል እና በሦስተኛው ቀን ከሞት እንደሚነሳ ደግሞ ሲገራቸው (ማቴዎስ 20፡ 18-21) እንደገና ደቀ መዛሙርቱ ከያዕቆብ እና ከዮሀንስ ጀምሮ የክብር ቦታ ለመያዝ ያላቸውን ፍላጎት ገለፁ። የኢየሱስን መከበር ሲያዩ እነሱም በዚህ አማካይነት በሰዎች ፊት መከበርን ፈለጉ። ኢየሱስም እሱ የመጣው "ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት"(ቁ 28) እንዳልምጣ ነገራቸው።

እራሳቸውን "ክርስቲያን" ነን ብለው የሚጠሩትንም ጨምሮ በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት ሰዎች እንዳሉ ኢየሱስ አሳይቶናል። - እነዚህም "ወሳጆች" እና "ሰጪዎች" ናቸው። የዚህ ዓለም መንፈስ ያላቸው ክርስቲያኖች (የጉባኤ ክርስቲያኖች እና የክበብ ክርስቲያኖች) ሁል ጊዜም ከክርስትና ለራሳቸው ሊያገኙ የሚችሉትን የሚፈልጉ ናቸው። በሌላው በኩል የእውነተኛው ቤተክርስቲያን ሰዎች ግን ሰጪዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ሁል ጊዜ በመጀመሪያ ለእግዚአብሔር ቅጥሎም ለሌሎች የሚሰጡበትን መንገድ ይፈልጋሉ። ኢየሱስ እንደተናገረው ብዙ በረከት የሚያገኙት ሰጪዎች ናቸው (የሃዋሁሪያት ሥራ 20፡35)።

በዚህ ዓለም ሥራዓት መሠረት ደረጃችሁ እንደጨመረ መጠን ከሌሎች አገልግሎት ማግኘትን ትጠባበቃላችሁ። የዓለም አስተዳዳሪዎች ያለማቋረጥ የሚያገለግሏቸው ሰዎች አሏቸው። በሌላው በኩል ደግሞ በእግዚአብሐር መንግሥት ከፍ ስትሉ ሌሎችን የበለጠ ታገለግላላችሁ። ኢየሱስ ይህንን እውነት ማስተማር ብቻ ሳይሆን በሕይወቱ ኖሮት እንደነበር እናያለን።

በቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀባዮች ሁል ጊዜ ሌሎች ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉላቸው ይፈልጋሉ። ወሳጅ የሆኑ ሰዎች የሚፈልጓቸው ነገሮች ካልተሟሉ በመጨረሻ በሆነ ነገር ቅር ተሰኝተው ቤተክርስቲያኑን ለቀው ይወጣሉ። ሰጪ የሆኑ ሰዎች ግን በቤተክርስቲያናቸው ውስጥ የጎደለ ነገር ወይም የሚያስፈልግ ነገር ሲያዩ ኃላፊነታቸውን በመወጣት በእግዚአብሔር ጸጋ የጎደለውን ለማሟላት በታማኝነት እና በጽናት ይሠራሉ።

ለምሳሌ በቤተክርስቲያናችሁ ውስጥ በእናንተ እና በሌሎች መካከል ፍቅር ከሌለ እና "የፍቅር መስፈሪያችሁ" ባዶ የሆነ ሲመስላችሁ የዚህ ምክንያት የሌሎቹ ሰዎች ጥፋት እንጂ የእናንተ እንዳልሆነ አድርጋችሁ ልትመለከቱ ትችላላችሁ። ይህ የወሳጅ አስተሳሰብ ነው። በምትኩ "የሰጪ አስተሳሰብ" ቢኖራችሁ ይህንን የፍቅር ማነስ ወደ እግዚአብሔር አምጥታችሁ የፍቅር መስፈሪያችሁን እንዲሞላላችሁ ትጠይቁ ነበር። ይህን ስታደርጉ ፍቅር በሕይወታችሁ ውስጥ ሞልቶ እና ተትረፍርፎ በዙሪያችሁ ላሉት ጭምር ያፈሳል።

በ2ኛ ቆሮንቶስ 9፡6-8 እንደምናየው እግዚአብሔር ጸጋውን በብዛት በእኛ ላይ ለማፍሰስ ይፈልጋል። ይህን ጥቅስ ስናነብ ለራሳችን ብቻ በራስ ወዳድነት ብዙ ለማከማች ማሰብ ቀላል ነው። ነገር ግን ይህን ክፍል በጥንቃቄ ብታነቡት ለሌሎች መልካም የምታደርጉ ሰጭዎች እንድትሆኑ እግዚአብሔር የተትረፈረፈ ጸጋ እንደሰጣችሁ ታያላችሁ (የቁጥር 8 የመጨረሻውን ክፍል ተመልከቱ)።

ይህንን የፃፈው ጳውሎስ በኤፌሶን ቤተክርስቲያን ውስጥ ለሦስት ዓመታት ለፍቶ ሠርቶ ነበር። መጨረሻ ላይ ሲሰናበታቸው (የሐዋርያት ሥራ 20፡25-35) እዚያ በነበርበት ጊዜ ሁሉ በመካከላቸው ሰጪ ሆኖ እንደኖረ ሽማግሌዎቹን አስታወሳቸው። ለዚህም ነው በቤተክርስቲያኑ በገንዘብ የመደገፍ መብት ቢኖረውም ገንዘቡን ያልፈለገው። ጳውሎስ ለራሱ ኑሮ ብቻ ሳይሆን አብረውት ለነበሩትን ሰዎችም ጭምር ያሟላ ነበር። "ሰጪ" ስለመሆን "ከፍተኛ" አመለካከት ነበረው! ለዚያም ነበር እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን በመገንባት ረገድ በብዙ ሊጠቀምበት የቻለው።

ብዙ ሰዎች ሰጭ መሆን የማይፈልጉበት ምክንያት በማቴዎስ 20፡22-23 ላይ ኢየሱስ እንደገለጸው መስዋእትነትን ("የመከራ ጽዋ") የሚያካትት ስለሆነ ነው። ነገር ግን ቤተክርስቲያን የምትገነባው በመስዋእትነት ብቻ ነው። ስለዚህ በአካባቢያችን ያለ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ስንገነዘብ፣ እንደተጠሙ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ቀርበን ጥልቅ በሆነው ኃይሉ ውስጣችንን እንዲሞላን እንለምን። ከዚያ ውስጠኛው ስፍራ የሕይወት ውሃ ወንዞች ፈስሰው (ዮሐ. 7፡37-38) በዙሪያችን ያለው ደረቅ መሬት ይጠጣል ቤተክርስቲያንም ይመሰረታል።

Chapter 8
ቤተክርስቲያንን ስለ ማፍረስ - ከሳሽ መሆን

ሰነፍ [ ሴት ] በገዛ [ ቤቷን ] ታፈርሳለች ( ምሳሌ 14 1)

መጽሐፍ ቅዱስ ቤት ሊፈርስ ስለሚችልባቸው ሁለት መንገዶች እንዳሉ ይናገራል። አንደኛው ጠንካራ መሠረት ሳይኖረው በሰነፍ የተሠራ ቤት ስለሆነ ማዕበል ሲመታው ይፈራሳል (ማቴዎስ 7፡26-27)። ሌላው መንገድ በቤቱ ውስጥ በሚኖር ሰነፍ ሰው ቤቱ ፈርሶ እስኪወድቅ ድረስ አንድ በአንድ የቤቱን ጢቦች ያወልቃል (ምሳሌ 14፡1)።

በታሪክም ሆነ ዛሬም በዓለም ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን ሳስተውል ከውጭ ከሚመጡ ጥቃቶች ይልቅ ውስጥ ባሉ አባሎቻቸው ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እንዳፈረሱ አይቻለሁ። እንዲያውም ሰይጣን ቤተክርስቲያንን በውጭ ኃይሎች ባሳደደበት ጊዜ ውጤቱ ቤተክርስቲያን ንጹህናዋን እንድትጠብቅ ማደርግ ነበር። ስለዚህ ሰይጣን ክርስቲያኖች ራሳቸው ቤተክርስቲያንን ከውስጥ ስለሚያፈርሱ በጣም ረክቷል። እግዚአብሔር ከጉባኤዎችም ሆነ ከክበቦች አማኞችን ጠርቶ ቤተክርቲያን ቢመሠርትም፣ አባላቱ ከተባበሩት ስይጣን አሁን ቢሆን የሚሠራውን ሥራ ማፍረስ ይችላል።

መንፈሳዊ በሆነ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰይጣን ይህን ማድረግ ይችላልን? በእርግጥ ይችላል! መጀመሪያ ላይ በመንግሥተ ሰማይ በእግዚአብሔር ፊት ይህን አድርጓል (ከመላእክት ውስጥ አንድ ሦስተኛውን በአመፅ በተሳካ ሁኔታ ወሰዳቸው) (ራእይ 12፡4) ፣ እርኩሳን መናፍስት እንዲሆኑ አደረጋቸው። የአንደኛው ክፍለ ዘመን ቤተክርስቲያን እንዲሁ ብዙ ጊዜ በአረመኔ ተኩላዎች (የሐዋርያት ሥራ 20፡30) እና እንደ የናስ አንጥረኛው እስክንድሮስ (2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡14-15) እና ዲዮጥራፌስ (3ኛ ዮሐንስ 1፡9-10) የመሰሉ አጋጥሟታል።

የነዚህን ዓይነት ሁኔታዎችን ለማስወገድ ከፈልግን ቤተክርስቲያን የሚያፈርሱ ግጭቶች ምንጫችውን ለይተን ማወቅ አለብን። ያዕቆብ 3፡13-4፡1 ይህንን በግልፅ ያስረዳል። የእነዚህ ግጭቶች ምንጭ ራስን የማስደሰት ፍላጎት ነው (4: 1)። የዚህም ውጤት የመረረ ቅናት እና ሁሉን ለራስ ከፍተኛ ምኞት ይፈጠራል (3፡14) በመጨረሻም በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ሁከት እና የተለያዩ ክፋትን ያስከትላል (3፡16)። ለዚያም ነው በዕብራውያን 12፡15 ላይ ምሬት ገና ሲጀምር (ገና በልብ እና በሐሳብ ሳለ) እንዲታረም ማስጠንቀቂያ የተሰጠው። ይህ ካልሆነ እና ሥር ከያዘ ብዙዎችን ይበክላል።

በምሳሌ 14፡1 ላይ እንደምናየው ሁለት አማራጮች ብቻ እንዳሉን ልብ ማለት ያስፈልጋል - ቤተክርስቲያኗን በንቃት እንገነባታለን ወይም እናፈርሳታለን። ቤተክርስቲያንን በንቃት መገንባት የሚቻለው በፍቅር ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 8፡1)። ይህ ማለት በቤተክርስቲያን ውስጥ እርስ በርሳችን መዋደድ ብቻ ሳይሆን በኑሮአችንም ማሳየት ማለት ነው (1ኛ ዮሐ 3፡18)። በዚህ ነገር ላይ ከግብዝነት መጠበቅ ያስፈልጋል (ሮሜ 12፡9)። የፍቅራችን ጥራት የሚፈተነው አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ነው። በዚህን ጊዜ ኢየሱስ እንዳደረገው ለቤተክርስቲያን "የራስን ሕይወት" ትተን እውነተኛ ፍቅር እንዳለን ማስየት እንችላለን (ኤፌ 5፡25)። ይህ ማለት ደግሞ ኢየሱስ ለእኛ እንደሚያደረገው በቤተክርስቲያን ውስጥ በሌሎች ስም መማለድ ማለት ነው (ዕብራውያን 7፡25)።

ራእይ 12፡10 ሰይጣንን "የወንድሞች ከሳሽ" ነው ይለዋል። አማኞች ሌሎች የቤተክርስቲያን አባሎችን በመክሰስ ቤተክርስትያንን ሲያፈርሱ፣ ከከሳሹ ሰይጣን ጋር ተባብረዋል ማለት ነው። ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መርቶ በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተመቅደስ እንደገና እንዲገነቡ ጥሪ ያቀረበው ወጣት ነቢይ በሆነው በዘካርያስ ሕይወት ውስጥ የዚህን ምስል እናያለን። በዘካርያስ 3፡1-5 ላይ ሊቀ ካህናቱ ኢያሱ ቆሻሻ ልብሶችን ለብሶ ሰይጣን ከጎኑ ቆሞ ሲከሰው እናያለን።ጌታችን የኢያሱን የቆሸሹ ልብሶች ከማንሳቱ በፊት በመጀመሪያ ሰይጣንን ገሰጸ። ከዚያም የኢያሱን የቆሸሹ ልብሶች በሚያማምሩ አዳዲስ ልብሶች ቀየረለት። ለምንድን ነው ዘካሪያስ እዚያ የሆነው? እዚያ የሆነበት ምክንያት አቋሙ በከሳሹ ወገን ወይም በአማላጁ ወገን እንደሆነ ለማየት ፈተና ነበር። የእግዚአብሔርን ቤት መመሥረት ምን ማለት እንደሆነ ዘካርያስ ያሳየናል። ኢያሱ አዲስ እና ቆንጆ ልብሶችን እንደለበሰ የበለጠ ክብር ለማሳየት ዘካርያስ በኢያሱ ራስ ላይ ጥምጥም እንዲደረግለት ለመጠየቅ ወሰነ።

ዛሬም ቤተክርስቲያንን እግዚአብሔር የሚገኝባት ለማድረግ ተመሳሳይ ፈተናዎች ይገጥሙናል። በአንድ በኩል በሌሎች ላይ የሚነሱ ክሶችን በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ በመፍቀድ ከዚያም በቤተክርስቲያን ውስጥ በሌሎች ላይ ሐሜትን በማሰራጨት በመጨረሻም ቤተክርስቲያኗን በመከፋፈል የ "ማፍረስ" አገልግሎቱ አካል እንድንሆን ሰይጣን ይጋብዘናል....... .

በሌላው በኩል ደግሞ ፣ ኢየሱስ እርሱ እንደሚያደርገው ሁሉ ሌሎች የበለጠ እንዲከብሩ ምልጃን መርጦ የ "ማነጽ" አገልግሎቱ አካል እንድንሆን ይጋብዘናል (ዕብ 7፡25)። ኃጢአት ባለበት ቦታ እንኳን ግባችን ሁል ጊዜ "ወንድማችንን ለማዳን" መሆን አለበት (ማቴዎስ 18፡15)። ይህ እውነት የሚኖርባት ቤተክርስቲያን ኢየሱስ በመካከሏ ስለሚኖር በጨለማ ኃይሎች ላይ ሙሉ ስልጣን ይኖራታል (ማቴዎስ 18፡18-20)።

Chapter 9
ቤተክርስቲያንን ስለመንከባከብ - እረኛ መሆን

እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው (ማቴዎስ 9፡36)

በማቴዎስ 9፡37-38 በዓለም ውስጥ የተትረፈረፈ መከር እንዳለ እና የሚያጭዱ ሠራተኞች በጣም ጥቂት እንደሆኑ ኢየሱስ ተናገረ። ከዚያ ቀጥሎ ሠራተኞች ወደ መከር እርሻዎች እንዲላኩ ጸልዩ አለ። ብዙዎች ይህንን ጥቅስ ተጠቅመው ሰዎችን በስሜታዊነት ወደ አንዳንድ የወንጌል ስርጭት ሥራ በፍጥነት እንዲወጡ ያነሳሳሉ። ነገር ግን ቁጥር 36 - 38 ያለውን አንድጋር ስናነብ ኢየሱስ ስለ "ሠራተኞች" ሲናገር በትክክል ምን ማለቱ እንደሆነ እናያለን።

ኢየሱስ ሕዝቡን ሲመለከት ሰባኪዎች እና አስተማሪዎች እንዳልጎደሏቸው አየ (ብዙ ፈሪሳውያንና ጸሐፊዎች ስለነበሩ)፤ የስብሰባዎችም እጥረት አልነበርም (ሕዝቡ በሰንበት እንዲሁም በሌሎች ቀናት በምኩራብ ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር); ተአምራትም አልጎደላቸውም (እርሱ በመካከላቸው ብዙ ተአምራትን ያደርግ ነበር)። ሕዝቡ ያጣው እረኞችን ነበር።

ዛሬም ያለንበት ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። የምንኖረው ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ እና የተለያዩ ትምህርቶች በታተሙ መጽሃፎች፣ በኢንተርኔት፣ በስማርት ስልኮች፣ ወዘተ ላይ በቀላሉ ይገኛሉ። በተጨማሪም ቤተክርስቲያናት በሳምንት ውስጥ ብዙ አገልግሎት ይሰጣሉ። ዛሬም እግዚአብሔር በራሳቸው ላይ የሚያተኩረውን ልባቸውን ሰብሮ ለስላሳ የእረኛ ልብ እንዲተካላቸው የሚሹ መሪዎችን ይፈልጋል።

ቀደም ሲል በኤርምያስ 3፡4-15 ላይ የቤተክርስቲያኑን ("ጽዮን") ሁለት አስፈላጊ ባሕርያትን እግዚአብሔር አሳይቶናል፤ (1) ከተለያዩ ከተሞች እና ቤተሰቦች የተውጣጡ የተለያዩ ሰዎች ይሆናሉ (2) እንደልቡ የሆኑ እረኞችን ይሰጣቸዋል። "እንደ እግዚአብሔር ልብ እረኛ" ማለት ምን ማለት ነው?

እንዲህ ዓይነት እረኛ የክርስቶስ ርህራሄ ይኖረዋል። ይህም ሰዎች ማሳየት ከሚችሉት ርህራሄ በላይ ነው። ይህ ርህራሄ ሰይጣን ሰዎችን "ሲያስጨንቅና ሲጥል" (ማቴዎስ 9፡36 ህዳግ) ከማየት የተነሳ የሚመጣ መንፈሳዊ ስሜት ነው። ይህ ማለት ከአካላዊ ወይም ከስሜታዊ ደህንነት ይልቅ ለመንፈሳዊ ደህንነታቸው የበለጠ መንከባከብ እና በድፍረት እውነትን ለመናገር ፈቃደኛ መሆን ማለት ነው።

የዚህ ዓይነት እረኛ የራሱን ምቾት ላለማስቀደም ፈቃደኛ ይሆናል። ኢየሱስ በምድረ በነበረ ጊዜ አብ እንደመራው ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ማይሎች በእግር ተጉዞ ፣ ቤት ውስጥ ሳይሆን ውጭ ተኝቶ ፣ አንዳንድ ጊዜም ሳይበላ ውሎ፣ ወዘተ ሙሉ ሕይወቱን አሳለፈ። ሳያዳላ ታላላቅ ለሚባሉት የምኩራብ ባለሥልጣን (ማቴዎስ 9፡18-19) ሆነ የደም መፍሰስ ችግር የነበራትን ደሃ ሴት (ማቴዎስ 9፡20-22) ያለአዳልኦ እኩል ይንከባከብላቸው ነበር። ኢሳይያስ 53፡8 ላይ እንደሚለው ኢየሱስ "ስለ ራሱ ደህንነት ሳያስብ" ኖሮ ሞተ። እውነተኛ እረኞች በዚህ መንገድ ለመኖር የኢየሱስን አርአያ የሚከተሉ ናቸው።

እንዲህ ያለ እረኛ ሳያወላውል ለእውነት ይቆማል። አይሁዶች በግዞት ወደ ባቢሎን በተወሰዱ ጊዜ ገና ወጣት የነበርው ዳንኤል የእግዚአብሔርን መሥፈርቶች እንደማይጥስ በልቡ ወሰነ (ዳንኤል 1፡8)። ይህ የዳኒኤል ድፍረት ሦስቱ ጓደኞቹም በድፍረት እንዲቆሙ እደረጋቸው (ዳንኤል 1፡11)።

እንዲህ ያለ እረኛ ክመንፈስ ቅዱስ ጋር በመተባበር ሌሎች ደስታቸው እና እምነታቸው እንዲጠነክር ይረዳቸዋል። ጳውሎስ ይህንን በ2ኛ ቆሮንቶስ 1፡24 ላይ እንዲህ ብሎ ገልጾታል "ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፥ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና"( 2ኛ ቆሮንቶስ 1፡24 መልእክት)

እንዲህ ያለ እረኛ መንፈሳዊ ስልጣን ይኖረዋል። ይህ እግዚአብሔር ብቻ የሚመሰክረው ነገር ነው ፣ ስለሆነም "የዚህ ዓለም ገዢ" (ሰይጣን) ሲመጣ በህይወታችን ውስጥ ምንም ቦታ አይኖረውም (ዮሐ 14፡30) ነው ።

እንዲህ ያለ እረኛ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሙሉ ወንጌል ለመስበክ ግዳጅ ይኖረዋል። ብዙ ሰባኪዎች በታዋቂ ርዕሶች ላይ ማውራት ይወዳሉ ፣ የአድማጮቻቸውን ጆሮ ያስደስታሉ (2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡3-4)። እንደነዚህ ያሉ እረኞች አይደሉም። ጳውሎስ በበኩሉ ጥሪውን በቁም ነገር በመያዝ "የእግዚአብሔርን ዓላማ ሁሉ" ካላወጀ በእጆቹ ላይ የሰዎች ደም እንደሚኖር ተናገረ (የሐዋርያት ሥራ 20፡26-27) ።

የዚህ ዓይነት እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ይሰጣል። ይህ ማለት ምርጫዎቹን ፣ ፍላጎቱን ፣ ምቾቱን ወይም አጀንዳውን መተው ካስፈለገ ትቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ከበጎቹ ጋር ሳይፈራ ይቆያል ማለት ነው። ኢየሱስ ይህንን የእረኝነት ልብ ከቅጥረኞች ጋር በማነፃፀር ፣ ነገሮች በማይመቹበት ወይም ችግሮች ሲመጡ ስለ በጎቹ ግድ ስለሌለው በጎቹን ትቶ ይሄዳል (ዮሐ 10፡11-13)። ጳውሎስ የሥራ ባልደረቦቹን ሕይወት ሲመረምር ከጢሞቴዎስ በስተቀር ሁሉም የራሳቸውን ፍላጎት እንደሚሹ ተገነዘቦ ነበር። ጢሞቴዎስ ግን ለመንጋው ደህንነት ከልቡ የሚያስብ የእረኛ ልብ ነበረው (ፊልጵስዩስ 2፡19-21)።

ማን ለእኛ ይሄዳል ?

ከብዙ ዓመታት በፊት የተገዛሁላቸው፣ ነፍሴን የሚጠብቁ እና ስለሕይወቴ በደስታ መመስከር የሚችሉት እረኞች እነማን እንደሆኑ ጌታ ጠየቀኝ (ዕብራውያን 13፡17)። ምሳሌውን በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ማየት ቻልኩ። ኢየሲስ እግዚአብሔር ባስቀመጠው ቦታ ሁሉ ከሱ በላይ ሥልጣን ለነበራቸው በታማኝነት በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሠላሳ ዓመታት ውስጥ ታዛዥ ነበር። ስለዚህም እውነተኛ የመንፈሳዊ ሥልጣን ነበረው (ማቴዎስ 8፡8-9)። በዚህ መንፈሳዊ ስልጣን ፣ ቢገረፍም እና ቢደማም ፣ ኢየሱስ በድፍረት በጲላጦስ ፊት መቆም እንደሚችል አየሁ። ጲላጦስ ያለውን ኃይል በመናገር ኢየሱስን ለማስፈራራት ሲሞክር ኢየሱስ በዝግታ "ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ስልጣን ባልነበረህም" አለው (ዮሐ 19፡10)።

በእነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እውነቱን ለማየት የልቤ ዐይኖች እንደተከፈቱ ፣ እግዚአብሔር እንደነዚህ ያሉ እውነተኛ እረኞች ወዳሉበት ጽዮን ቤተክርስቲያን ለማግኘት እንዲመራኝ በውስጤ እሳት ተቀጣጠለ። ምንም ዓይነት ምድራዊ ዋጋ - ዘመድ ፣ ሥራ ፣ ወዘተ ቢያስከፍልም - የክርስቶስን አካል ለመገንባት በሙሉ ልቤ እራሴን ለመስጠት ወሰንኩ።

ለኢሳያስ እንደሆነው እግዚአብሔርም ከኃጢአት ሁሉ ካነፃኝና ከሰበረኝ በኋላ "ማንን እልካለሁ ማንስ ወደ እኛ ይሄድልናል?" ብሎ ጠየቀኝ (ኢሳይያስ 6: 8)። ከፊቴ የነበሩትን የሥራም ሆነ ሌሎች ሁኔታዎችን ትቼ በ2007 የወሰንኩትን ውሳኔ እስከዛሬ በጭራሽ አልተቆጨሁም።

ዛሬ ባቢሎን ከሚገኙት ከጉባኤ እና ከክበቦች ወጥታችሁ በመንፈሳዊው "ጽዮን" ውስጥ ቤተክርስቲያኑን እንድትመሠርቱ የእግዚአብሔርን ጥሪ ከሰማችሁ መልሳችሁ "እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ" እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።