የፈሪሳውያን 50 ምልክቶች

Written by :   Zac Poonen Categories :   Religious or Spiritual
    Download Formats:

Chapter
መግቢያ በወንጌል እንደምናነበው እየሱስ ሰዎችን ስለ ሦሥት እርሾዎች አስጠንቅቋል፣

1፟ የሄሮድስ እርሾ (ማርቆስ 8፣15)

2 የሰዱቃዊያን እርሾ (ማቲዎስ 16፣6)

3 የፈሪሳዊያን እርሾ (ማቴዎስ 6፣6)

እነዚህ ሦሥት አይነት ክርስቲያኖችን ያሳያሉ ።

የሄሮድ እርሾ ዓለማዊነት ነበረ። በማርቆስ 6፣20 እንደምናየው ሄሮድ የዮሃንስ መጥመቁን ስብከት ማዳመጥ ይወድ ነበር። ሆኖም ከሁለት ጥቅሶች በኋላ እንደምናየው ሰሎሜ ስትደንስ ማየትንም ይወድ ነበር (በግምት ሰውነቷ በደምብ ሳይሸፈን ወሲባዊነትን የሚያነሳሳ ዳንስ ነበር የምትደንሰው)። ዛሬ እንደዚህ ዓይንት ክርስቲያኖች አሉ። እነዚህም ክርስቲያኖች እሁድ እሁድ ጥዋት ጥሩ ስብከትን ቢወዱም ከሰዓት በኋላ እርኩስ ሲኒማ ያያሉ። ከሚያሰለቸው የፈሪሳዊያን ስብከት ይልቅ የመጥምቁ ዮሃንስ ስብከት ኃይለኛ እና ሥልጣን ያለው ስለነበረ ነው ሄሮድ የወደደው። ስለዚሀም ኃይለኛ እና ጥሩ ስብከትን የሚወድ ሁሉ መንፈሳዊ ነው ማለት አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ዓለማዊ የሆኑ ክርስቲያኖች እንደ ፈሪሳዊያን አይመጻደቁም። ዓለማዊ የሆኑ መዝናኛዎችን ይወዳሉ፣ መውደዳቸውንም አይደብቁም።

የሰዱቃዊያን እርሾ የሃሰት ትምሕርት ነበር። በእምነታቸው ነፃ አሳቢዎች ነበሩ። በመላእክት፣ በተአምራት፣ በትንሣኤ እና፣ በመንፈሳዊ ቃል አያምኑም ነበር። ዛሬም የዚህ አይነት እምነት ያላቸው ክርስቲያኖች አሉ። እነዚህም ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ተአምራትን ማድረግ እንዳቆመ እና የተለያዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችም በአሁኑ ጊዜ እንደሌሉ ነው የሚያምኑት።

የፈሪሳዊያን እርሾ መሠረቱ ግብዝነት ነበረ። ትምሕርታቸው በመጸሓፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነበር በተጨማሪም በውጭ ለሰው በሚያሳዩት ኑሮአቸው የጻድቃን ኑሮ ነበራቸው። በነዚህ ሁለት ነገሮች ላይ እየሱስም መስክሮላቸዋል (ማቴዎስ 23፡3 እና 5)። አሥራት ይከፍሉ ነበር፣ በየጊዜው ይጾሙና ይጸልዩ ነበር፣ በተጨማሪም በውጭ ለሰው የሚታዩትን ትእዛዛት ሁሉ ከመጠበቅም በላይ የወንጌል መልእክተኞችም ሆነው ይሠሩ ነበር። ዛሬ እነዚህን ሁሉ የሚያደርጉና እንደ ፈሪሳዊያን የሚኖሩ ክርስቲያኖች አሉ።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ከሦስቱም ዓይነት እርሾዎች አሉባቸው።

ከላይ የተገለጹትን ሁኔታዎች ስናይ የእየሱስ ትልቁ አለመግባባት ከሄሮድ እና ከሰዱቃዊያን ተከታዮች ጋር ይመስላል። ነገር ግን ግጭቱ ከነዚህ ጋር አልነበረም። ትልቅ ግጭት የነበረው ቅድስናን እና በመጸሓፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምሕርት ከሚያስተምሩት ፈሪሳዊያን ጋር ነበር። እነዚሁ ፈሪሳዊያን ነበሩ ከሌሎች ሁሉ የበለጠ እየሱስን ለመስቀል የጓጓት።

ዛሬም ቢሆን በክርስትና ውስጥ አደገኛ የሆኑት ከሰዱቃዊያን እና ከሄሮድ ተከታዮች ይልቅ ፈሪሳዊያን ናቸው። የሄሮድ ተከታይ ወደ ገሃነም ሊያመራ ይችላል ሆኖም አለማዊነቱ ለሁሉም ግልጽ ስለሆነ ሌሎችን አያሳስትም። ነፃ አሳቢ የሆኑት ሰዱቃዊያን በተአምር እና በትንሣኤ ስለማያምኑ ብዙዎች መንፈሳዊነታቸውን ይጠራጠራሉ፣ ስለዚህም በነሱ አይታለሉም።

በዛሬው ክርስትና በጣም አደገኛ የሆነው (በእየሱስ ጊዜ እንደነበረው) ትምሕርቱ ትክክል የሆነውና 'ቅድስናን' የሚሰብከው ፈሪሳዊ ነው። ይህም 'ቅድስና' ሕግ እና ትእዛዛትን በማጥበቅ ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ የሚገኝ 'ጽድቅነት' በሮሜ 14፡17 የተጠቀሰውን "የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ" አያካትትም። እንዲህ አይነት ሰው ክርስቲያኖችን ወደ ሃሰት ቅድስና ስለሚመራ አደገኛ ነው።

ስለዚህ የፈሪሳዊያንን ገፀ-ባህሪያትን ማውቅ አስፈላጊ ነው። ከላይ ከገልጽኩት በላይ ስለ ሄሮድ ተከታዮች እና ስለ ሰዱቃዊያን ገፀ-ባህሪያት ብዙም አልተጻፈም። ነገር ግን ስለ ፈሪሳዊያን በወንጌል ውስጥ ብዙ ተጽፏል። ይህም የሆነው እግዚአብሔር ገፀ-ባህሪያቸውን እንድናጠና ስለፈለገ ነው።

አክራሪ እና በመጸሓፍ ቅዱስ ላይ ብቻ የተመሠረተ ትምሕርት ኖሮአቸው ጽድቅናን የሚሹ አማኞች ሳያውቁት ፈሪሳዊ የመሆን አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል። ይህ ሁኔታ ብዙዎቻችንን ስለሚመለከት በጥልቅ እና በትህትና እናጥናው።

በወንጌል ውስጥ ቢያንስ ሃምሳ የሚሆኑ የፈሪሳዊያን ገፀ-ባህሪያትን አግኝቻለሁ። ከሃምሳዎቹ ገፀ-ባህሪያት ውስጥ አንድ እንኳን የፈረሳዊ ባህሪ ቢኖረን እና አርባ ዘጠኙ ባይመለከቱንም ፈሪሳዊ ነን ማለት ነው። እዚህ መጽሓፍ ላይ የተዘዘሩት የፈሪሳዊያን ባህሪያት ሁሉንም የሚያካትቱ አይደሉም። እያንዳንዳቸሁ ስለ ሕይውታችሁ በጥልቅ ብታስተውሉ በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተካትቱ ገፀ-ባህሪያትን ልታግኙ ትችላላችሁ።

የፈሪሳዊያን መንፈስ ከክርስቶስ መንፈስ ጋር በጣም ተቃራኒ ስለሆነ ፈሪሳዊነት በጣም አሳሳቢ ነው። በጣም ጥቂት እንኳን የገሃነም መንፈስ እንዳይኖርብን እንደምንሻ ሁሉ በጣም ጥቂት የፈሪሳዊ መንፈስ እንዳይኖርብን መሻት አለብን።

አንደኛው ከእግዚአብሔር የተገኘ በረከት ምልክቱ መንፈስ ቅዱስ ራሳችንን እንድናይ የሚያበራልን ብርሃን ነው። ክርስትያንነት የጎደለው አኗኗራችንን በየጊዜው የበለጠ እያየን እና እያሻሻልን ካልተጓዝን የእግዚአብሔር በረከት አለን ማለት አንችልም። ብዙ የማያምኑ ሰዎች ሃብት እና ጤንነት ከአማኞችም በላይ ስላላችው የሃብት ብዛት እና መልካም ጤንነት የእግዚአብሔር በረከት ምልክቶች አይደሉም።

እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ከክርስቲያንነት የራቁ ሁኔታዎችን የሚያሳየን ራሳችንን ከነዚህ ነገሮች አጽድተን የሱን መለኮታዊነት እንድንካፈል ነው (2 ቆሮ 7፤1)። ይህም ሲሆን የግል ኑሮአችን፣ የቤተሰብ ኑሮአችን እና የቤተ ክርስቲያን ኑሮአችን ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ ይሄዳል። ከዚያም ከሕግ አክራሪነት ነጻ ወጥተን እንደ ንስር ከፍ ማለት እንችላለን። ነገር ግን በውስጣችን ያለውን የፈሪሳዊ መንፈስ ካላሸነፍን ምድራዊ ሆነን እንቀራለን።

እግዚአብሔር ቃሉን የሰጠን ራሳችን ያለንበትን ሁኔታ እንድንረዳ ነው እንጂ የሌሎችን ፈሪሳዊነት እንድናይበት አይደለም። ለእግዚአብሔር ሥራ ጠቃሚ መሆን የምንችለው የኛን ፈሪሳዊነት ተገንዝበን ረሳችንን ከዚህ ነጻ ስናደርግ ነው።

Chapter 1
ፈሪሳዊያን ከእግዚአብሔር ሰዎች ጋር ስለአላቸው ግንኙነት ታላቅ ክብር ይሰማቸዋል

" በልባችሁም አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ " (ማቴዎስ 3 9 )

ፈሪሳዊ የሆነ ሰው እሱ የእግዚአብሔር ሰው አለመሆኑን ስለሚያውቅ የእግዚአብሔር ሰው መሆኑ ከሚያታውቅለት ወንድም ጋር መወዳጀትን ይሻል። ይህንንም የሚያደርገው በዚህ ግንኙነቱ የእግዚአብሔር ሰው ለመሰኘት ነው። ዛሬ ብዙ ሥጋዊ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ሰው ነው ተብሎ የሚነገርለት ሰው የሚመራው ቤተ ክርስቲያን አባል በመሆናቸው ክብር የሚሰማቸው አሉ። በራሳቸው ምንም ቅድስና የላቸውም ነግር ግን በታወቀው መሪ ዝና ይመካሉ። ፈሪሳዊያን የእግዚአብሔር ከሆኑ ሰዎች ጋር በመዋላቸው እነሱም የእግዚአብሔር ሰዎች የሆኑ ይመስላቸዋል።

ምንም እንኳን የጥሩ ቤተ ክርስቲያን አባል ብትሆኑም ንስሃ ያልገባችሁለት ኃጢያት በሕይወታችሁ ካለ ወይም በሰው ላይ ቂም/ጥላቻ በልባችሁ ከያዛችሁ ወደ ገሃነም ትሄዳላችሁ። የጥሩ ቤተ ክርስቲያን አባላት ስለሆናችሁ ሓሜታችሁን እና የክፋት ንግግራችሁን እግዚአብሔር የሚቀበለው ከመሰላችሁ በጣም ተሳስታችኋል። የፍርድ ቀን ስትቀርቡ ትደነግጣላችሁ። ምናልባት ቀደም ብሎ ድናችሁ ዛሬ ደሞ ከጠፉት መሃል ልትሆኑ ትችላላችሁ። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ሰዎች ጋር ስለምትተዋወቁ ክብር አይሰማችሁ።

Chapter 2
ፈሪሳዊያን በውጭ በማያሳዩት ጻድቅነት/ቅድሰና ታላቅ ክብር ይሰማቸዋል

እየሱስም እንዲይ አላቸው " ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም "(ማቴዎስ 5፤20)

እዚህ ላይ እየሱስ ምን ማለቱ ነው? ከፈሪሳዊያን በላይ መጾም፤ መጸለይ እና አሥራት መስጠት አለብን?

እዚህ ላይ እየሱስ ስለ ጥራት ነው እንጂ ስለ ብዛት አልነበርም የተናገረው። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት የጸድቅናችን ጥራት ከፈሪሳዊያን በጣም የላቀ መሆን አለበት። እዚሁ ምዕራፍ ላይ በሚቀጥሉት ጥቅሶች ይህንኑ ያብራራል። የፈሪሳዊያን ጽድቅናቸው በውጭ ለሌሎች የሚታይ ብቻ ነበር። በውጭ ለሌሎች እንደ ሚይሳዩት የእግዚአብሔርን ተእዛዛት በመከተላቸው ታላቅነት ይሰማቸው ነበር። እየሱስ ግን ያለው እግዚአብሔር የሚፈልገው የውስጥ ጽድቅነት ነው። በውጭ የሚታዩትን ኃጢያቶች እንደ መግደልን የመሳሰሉ ሳይሆን በውስጥ ያለውን ንዴት ማስውገድ፤ በውጭን አመንዝራነት ማስወገድ ሳይሆን በውስጥ ሴትን አይቶ መመኘትን ማስወገድ ይጨምራል።

እየሱስ እንደተናገረው ንዴት እና ወሲባዊ ምኞት ሰውን ወደ ገሃነም እንዲገቡ የሚያደርጉ ኃጢያቶች ናቸው (ማቴዎስ 5፡22፣ 29፤30) ። ብዙ ክርስቲያኖች የፈሪሳዊ ባህሪ ስላላቸው በውጭ ለሰዎች በሚያሳዩት አኳኋናቸው በጣም ይመካሉ። ስለዚህም በአስተሳሰባቸው ለሚያደርጉት ኃጢያት ትኩረት አይሰጡም። ጸድቅናችሁን በውጭ ብቻ የሚታይበት ሌሎች ሁኔታዎችም ሊኖሩ ይችላሉ። "ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል"(1ኛ ሳሙኤል 16፤7)። ሌሎች አማኞች ስለመንፈሳዊነታችሁ ያላቸው አስተሳሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ምንም ዋጋ የለውም። እግዚአብሔር አስተሳሰባችሁን፤ ለድርጊቶቻችሁ ምን እንደሚያነሳሳችሁ እና አስተያየታችሁን ያያል። ልባችሁ ንጹህ ካልሆነ በሌሎች ዘንድ ባላችሁ ዝና አትመኩ።

Chapter 3
ፈሪሳዊያን ከኃጢያተኞች ጋር አይገናኙም

' " ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን። መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል? አሉአቸው " (ማቴዎስ 9፡11)

ፈሪሳዊያን ውሎአቸው ከመሰሎቻቸው 'ቅዱሳን' ፈሪሳዊያን ጋር ብቻ ነበረ። ከኃጢያተኞች ጋር በመታየቱ እየሱስንም እንኳን ይተቹ ነበር። ቅድስናችሁ ከማያምኑ ዘመዶቻችሁ ጋር እንዳትገናኙ ያደርጋችኋልን? በእርግጥ አንድነት የሚኖረን ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር ብቻ ነው። ሆኖም ከሌሎችም ጋር ወዳጅነት ሊኖረን ይችላል። እየሱስ 'የኃጢያተኞች ወዳጅ' ይባል ነበር። እንደ እየሱስ መሆን ከፈለጋችሁ የኃጢያተኞችም ወዳጅ መሆን አለባችሁ።

ፈሪሳዊ የሆነ ሰው የሚበከል ስለሚመስለው የማያምኑ ሰዎች የሠርግ ግብዣ ላይ አይገኝም። እየሱስ ግን የማያምኑ ዘመዶች ለሠርጋቸው ቢጋብዙት በደስታ ይሄዳል። ወደ ኃጢያተኛ ቤት ምናልባትም ዳንስ እና መጠጥ ወደ ነበረበት ቤት ሄደ። እዚያም ሂዶ ወንጌልን ለኃጢያተኞች ያካፍላል። ጽድቅናው የውስጥ ስለሆነ ከኃጢያተኞች ጋር መገናኘት አላረከሰውም። ምንም እንኳን አብዛኛውን ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቢያሳልፍም ብዙ ጊዜ ከኃጢያተኞች ጋር በመነጋገር አሳልፏል። ከኃጢያተኞች ወዳጅነት ከሌለን እንዴት ወደ ጌታ ልንመራቸው እንችላለን?

አንድ ጥሩ ጥያቄ ራሳችሁን መጠየቅ የምትችሉት ይህ ነው፡ ቤተ ክርስቲያናችሁ ውስጥ እናንት ወደ ጌታ ያመጣችኋችው ስንት ሰዎች አሉ? ምንም እንኳን በቤተ ክርስቲያናችሁ ውስጥ 20 ዓመት ያሳለፋችሁ ብትሆኑም ምናልባት አንድም ሰው ወደ ክርስቶስ ያላመጣችሁ ትሆናላችሁ። ይህ ሁኔታ የእናንተን አኗኗር ወይም ሕይወት የሚገልጽ አይመስላችሁም? ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም በብዙ ዓመታት ውስጥ አንድም ሰው ወደ ክርስቶስ አላመጡም። የዚህም ምክንያት ፈሪሳዊያን ስለሆኑ ይሆናል። በዚህ ነገር ላይ በእውነተኝነት ፈሪሳዊነታችሁን ካመናችሁ እግዚአብሔር ሌሎችን ወደ እሱ ለማምጣት ሊጠቀምባች ይችላል።

Chapter 4
ፈሪሳዊያን እንደ መነኑ ሰዎች ብቸኞች ናቸው

እኛና ፈሪሳውያን፥ ብዙ ጊዜ የምንጦመው፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? (ማቴዎስ 9፡14)

ፈሪሳዊያን ሌሎች ሰዎች እንዲጾሙ እና ኢንዲጸልዩ ያስገድዱ ነበር። መጾምን የመሳሰሉ ሥጋዊ ሥርአቶች ላይ ማትኮራቸው መንፈሳዊ የሚያደርግ ስለሚመስላቸው ይኮሩበት ነበር። እየሱስ ከፈሪሳዊያን የበለጠ ይጾም ነበር። የጾመውም ቅዱስ ስለነበረ ነው ኢንጂ ቅዱስ ለመሆን ብሎ አልነበረም። እየሱስ እንደፈሪሳዊያን በመጾሙ አይኮራም ነበር። በተጨማሪም ሌሎች እንዲጾሙ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አላስገደደም ዛሬም አያስገድድም። በእግዚአብሔር ዘንድ ጾም ዋጋ የሚኖረው በፈቃደኝነት ሲሆን በቻ ነው። ካለበለዚያ ጾም የሞተ(ፍሬአማ ያልሆነ) ሥራ ይሆናል።

የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች በተለያየ ደረጃ ባህታዊነትን እና ጾምን ይለማመዳሉ። አንዳንዶቹም ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር ፍትወተ ሥጋን ከመፈጸም ይቆጠባሉ። ነገር ግን ክርስቲያን በንደዚህ አይደለም ቅዱስ የሚሆነው። የትክክለኛ ሰው ምልክቱ እና ራሱን ሥርዐት የሚያሲዘው ከምግብ እና ከፍትወተ ሥጋ በመቆጠብ ሳይሆን ምላሱን በመቆጣጠር ነው (ያዕቆብ 3፡2)። በተጨማሪም አስተሳሰባችንን እና ዐይኖቻችንን መቆጣጠር አለብን።

እየሱስ በጥሩ ምግብ መደሰት ይችላል። በዚያን ጊዜ "በላተኛ" ነው ይሉት ነበር (ሉቃስ 7፡34)። መጀመሪያ የሠራው ተአምር ሠርግ ላይ ተጨማሪ የወይን ጠጅ መፍጠር ነበረ! ይህ ተአምር እየሱስ ካደረጋቸው ታአምራት ሁሉ አስፈላጊ ያልነበረ ሊመስል ይችላል። እንግዶቹ ብዙ የወይን ጠጅ ጠጥተው ነበር፤ ቢሆንም እየሱስ ምናልባት 200 እንግዶች ላሉበት ሠርግ 600 ሊትር ወይን ጠጅ ሠራላቸው። ይህም ማለት ለእያንዳንዱ ሰው 3 ሊትር ወይን ጠጅ ማለት ነው!! ለሠርገኞቹ ይህን ያህል ወይን ጠጅ መሥራት ለምን አስፈለገ? የእየሱስ መጀመሪያ ተአምር 'መንፈሳዊ' የሚባሉ ለምሳሌ የሞተን ማስነሳት የመሳሰሉ ሊመስለን ይችላል። ይህን ያደረገበት አንደኛው ምክንያት ወደ ምድር የመጣው ውጫዊ የሆኑ 'አትንኩ፣ አትቅመሱ' የሚሉ የሃይማኖት ትምህርቶችን ለማውደም ስለነበረ ነው።

ስለ ጾም ጊዜአቸው በረቀቀ መንገድ የሚያወሩ ክርስቲያኖች (በተለይም የአንዳንድ ሃይማኖት ወገን አባሎች) አግኝቻለሁ። እነዚህም ሰዎች ሲናገሩ "በቅርብ ጊዜ በ21 ቀን ጾም ላይ ሳለሁ ጌታ የሰጠኝን የከበረ ቃል ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ" ይህንን እና የመሳስሉትን ቃላት ይጠቀማሉ። ዋናው ዓላማቸው ስለ 21 ቀን ጾማቸው ሰውን ማስደነቅ ነው። ሌላቹ ቃላቶች ሁሉ ሁለተኛ ናቸው። እየሱስ ግን ስለጾማችን ለሌሎች እንዳንናገር ነግሮናል። ፈሪሳዊያን ግን በባሕታዊነታቸው ይኮሩ ነበር። በእርግጥ በክርስትና ኑሮ ምግብ ፤ መኝታ እና የፍትወተ ሥጋ ጉዳይ ላይ ሥነ ሥርዓት ያስፈልጋል። ቢሆንም ስለእነዚህ ጉዳዮች ለሌሎች መንገር ወይም መመካት አያስፈልግም።

Chapter 5
ፈሪሳዊያን በጥቃቅን የሌሎች አድራጎቶች ላይ ሂሣዊ ትንታኔን ያበዛሉ

ፈሪሳውያንም አይተው። እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት። (ማቴዎስ 12፤2)

በእስራኤል ሕግ መሠረት ሰዎች በእርሻ ውስጥ ሲያልፉ ጥራጥሬ ቀጥፈው መብላት የተፈቀደ እንደሆነ ፈሪሳዊያን ያውቁ ነበር። እዚህ ላይ ጥያቄአቸው ለምን በሰንበት ቀን 'ሥራ' ተሠራ ነበር። ፈሪሳዊያን በጥቃቅን የሌሎች አድራጎቶች ላይ ሂሣዊ ትንታኔን ያበዛሉ። በማቴዎስ 15፡2 እንደምናየው ለምንድን ነው ደቀመዛሙርቶችህ ከታላላቆቻችን እንደተማርነው ሥርዓት መሠረት እጃቸውን የማይታጠቡት ብለው እየሱስን ጠየቁት ። ፈሪሳዊያን ጥቃቅን ጉድለቶችን አማኞች ላይ ለማግኘት ሁልጊዜ ይከታተላሉ።

የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ሆናችሁ ከላይ የተጠቀሱትን የምታደርጉ ከሆነ ቤተ ክርስቲያናችሁ በፈሪሳዊያን የተሞላ ሊሆን ይችላል። ይህም የሚሆነው የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች አኗኗር የቤተክርስቲያን ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ነው። ይህንንም በዮሐንስ ራእይ ምእራፍ 2 እና 3 ላይ እናያለን። ነገር ግን ሽማግሌዎቹ ከፈሪሳዊነት ነጻ የሆኑ ቢሆኑ አብዛኛው የቤተ ክርስቲያን ሰዎችም ከፈሪሳይዊነት ነጻ ይሆናሉ።

ስለዚህ ለአማኞች ሁሉ ይህን ማለት እፈልጋለሁ፡ ሕግ የሚያጠብቁ እና ፈሪሳዊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን አትከተሏቸው። ለሽማግሌዎች መታዘዝ በቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው ኢንጂ ግላዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አይደለም። ማለትም ለምሳሌ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የእሁድ አገልግሎት ከጥዋት በ4 ሰዓት ይጀመራል ቢሏችሁ። እንደተባላችሁት ከጥዋቱ በ4 ስዓት ተገኙ። በመዝሙር ጊዜም የምንዘምረው መዝሙር ቁጥች 45 ነው ሲሏችሁ የተባለውን መዝሙር አብራችሁ ዘምሩ። መእምኑ እንዲነሱ ሲጠየቁ አብራችሁ ተነሱ። ተቀመጡ ሲባልም እናንተም ተቀመጡ። "ለቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መታዘዝ" ማለት የሄ ነው። ነገር ግን ክብር የሚገባው አኗኗር ከሌላቸው የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን የግል አኗኗር አትከተሉ። ካለበለዚያ እናንተም ትበላሻላችሁ። እየሱስን ተከተሉ። ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥልጣን ቢኖራቸውም ሕግ አጥባቂና ፈሪሳዊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን አትከተሉ። ከቤተ ክርስቲያን ውጪ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን የምትከተሉት የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው ብላችሁ የምትተማመኑባቸውን ብቻ ነው።

Chapter 6
ፈሪሳዊያን የሚኖሩት ሕግን በመከተል ነው

እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት። (ማቴዎስ 12፤10)

ፈሪሳዎያን ሕግ ተከትለው ነው የሚኖሩት። የእየሱስን ሕይወት ተከትለው አይኖሩም። አስቂኝ የሆነው ሕጋቸው በሕመም ላይ ያለ ሰው በሰንበት ቀን ከህመሙ ለመፈወስ መሻትን ይከለክላል። ዛሬም ቢሆን ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የመእምኑን ኑሮ የሚያካብዱ ሕጎችን ያሳልፋሉ። እነዚያ ፈሪሳዊያን እየሱስን "ይከሱትም ዘንድ" ነበር ይህን ጥያቄ የጠየቁት። ዛሬም ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ራሳቸው ያወጡዋቸውን ጥቃቅን ደምቦች የጣሰን ሰው ለማውገዝ ይቸኩላሉ። ለፍጥረት ሁሉ ሕግን ሰጪ እግዚአብሔር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ያልሰጠውን ሕግጋት ቤተ ክርስቲያን ላይ ማውጣት የእግዚአብሔርን ቦታ እንደመውሰድ ነው፤ ይህም "የጸረ ክርስቶስ መንፈስ ነው" (2 ተሰሎንቄ 2፡4)። ይህን የሚያደርጉ በመጨረሻም እንደነዚያ ፈሪሳዊያን ከሰይጣን ጋር አብረው "የወንድሞቻችን ከሳሽ" ይሆናሉ (የዮሃንስ ራእይ 12፡10) ።

ለምሳሌ የሴቶችን ራስ ስለመሸፈን ጉዳይ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ሰቶች ሲጸልዩ ወይም ትንቢትን ሲናገሩ ራሳቸውን ይሸፍኑ ይላል (1 ቆሮንቶስ 11፡5)። ነገር ግን የአንዳንድ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች "ሁል ጊዜ መጸለይ" ስላለባቸው ሴቶች ራሳቸውን ሁል ጊዜ (በቀን 24 ሰዓት) መሸፈን አለባቸው ብለው ያስተምራሉ። ወንዶች ሁልጊዜ ራሳቸውን እንዳይሸፍኑ (ኮፍያ ወይም ባርኔጣ እንዳያደርጉ) ብለው ስለማያስተምሩ አቋማቸው የሚወላውል እና ያልጸና መሆኑን ያሳያል። እህቶች መላ ጸጉራቸውን ከመሸፈን ይልቅ (በሙቀት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ራስን መሽፈን ስለማይመች) ወደ ኋላ ያለውን 15% ብቻ እንዲሸፍኑ ማድረግ ሌላ የሚወላውል አቋማቸውን ያሳያል።

ፈሪሳዊያን ብዙ ይሚያወላውሉ ሥራዓቶች አሏቸው። ሆኖም ይህንን ሁኔታቸውን አይገነዘቡም። ጸጉራቸውን በሙሉ እንደሚሸፍኑ እኔ ያየኋቸው እንደ ማዘር ቴሬሳን የመሳሰሉ ሮማን ካቶሊክ መነክሲቶች ናቸው። ጸጉር መሸፈንን እንደ ሕግ አድርገው በዚህ ላይ የሚያተኩሩ (ይህን የማይከተሉት ላይ የሚፈርዱ) አቋማቸው የሚወላውል መሆኑን አይቻለሁ። ተመጻዳቂ እና ፈሪሳዊያን ናቸው። እግዚአንሔር ሴቶች ጸጉራቸውን እንዲሸፍኑ ያለው ለምሳሌ/ ትዕምርት ነው እንጂ ሕግ እንዲሆን አይደለም። ስለዚህ የእህቶች ጸጉር 100% ተሸፈነ አልተሸፈነም ወይም ጸጉር ከሸፋን ስር ይታያል አይታይም ብዬ ጊዜዬን አላባክንም።

ፈሪሳዊነት ያለባቸው የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ቤተሰቦቻቸው ላይ ሳይሆን ለሎች ላይ ባጣም ጥብቅ ናቸው። ለዚህ ነው እየሱስ ለፈሪሳዊያኑ "አህያችሁ በሰንበት ቀን ወደ ጉድጓድ ቢወድቅ ምን ታደርጋላችሁ?" ብሎ ያላቸው። ከታመመ ሰው በላይ ለአህዮቻቸው ግድ ነበራቸው። የቤተ ክርስትያን መሪዎች ለቤተ ክርስቲያን ያወጡትን ደንቦች ሥራ ላይ ሲያውሉ ለቤተስቦቻቸው እንዳያደሉ በጣም መጠንቀቅ አለባቸው።

Chapter 7
ፈሪሳዊያንን ለአድራጎት የሚገፏፏቸው ቅናት እና ጥላቻ ናቸው

' " ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት " (ማቴዎስ 12፡14)

ሰው ላይ ያላችሁ ቅናት መግደል ላይ ላያደርሳችሁ ይችላል። ሆኖም ለግድያ የመጀመሪያው እርምጃ ቅናት እና ጥላቻ መሆናቸውን አትዘንጉ። የቃየንም አካሄድ ይኸው ነበር፡ ቅናት... ጥላቻ... ግድያ።

ፈሪሳዊያን ማድረግ የማይችሉትን ብዙ ስላደረገ እና በሰዎች ዘንድ ዝናን ስላተረፈ ፈሪሳዊያኑ እየሱስ ላይ ይቀኑ ነበር። ስለእየሱስ ጥቂት እውቀት የነበረው ጲላጦስ እንኳን ፈሪሳዊያን እየሱስ እንዲሰቀል የፈለጉት ከቅናት የተነሳ መሆኑን አስተውሎ ነበር (ሜቴዎስ 27፡18)። ሰው ላይ ቅናት ሲኖራችሁ በአነጋገራችሁ እና በአኳኋናችሁ ይታያል። ከእናንተ የተሻለ በሚሰብክ፤ የበለጠ ሀብት ባለው ወይም እናንተ የሌላችሁ የመንፈሳዊ ስጦታዎች ባለው ሰው ላይ ትቀኑ ይሆናል። ይህም ሲሆን ይህን ሰው ለመንቀፍ ጥቂት እንከን መፈለግ ቀላል ሆኖ ታገኛላችሁ። ይህ ስው ሲወድቅ ለማየትም ትጓጓላችሁ። የፈሪሳዊያን ሃይማኖት የቃየን ሃይማኖት ነው።

የሰው ዘር ታሪክ በሁለት መስመር ይጀምራል - አንደኛው መንፈሳዊ ነው (አቤል) ሁለተኛው የሃይማኖት ነው (ቃየን)። የቃየን ዋነኛው ኃጢያት አቤል ላይ መቅናቱ ነበር። የነዚህ ሁለቱ መስመሮች መጨረሻቸው፤ አንደኛው እየሩሳሌም (ትክክለኛው ቤተ ክርስቲያን) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ያሃሰት ቤተ ክርስቲያን (ባቢሎን) ነው። ምንም እንኳን ወንጌላዊ ዶክትሪን ቢኖረንም የቃየንን በቅናት የተሞላ ሃይማኖት የምንከተል ከሆነ መጨረሻችን ባቢሎን ነው የሚሆነው።

Chapter 8
ፈሪሳዊያን ተጠራጣሪዎች ስለሆኑ ሰዎች ላይ መልካም አመለካከት የላቸውም

ፈሪሳውያን ግን ሰምተው። ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ። (ማቴዎስ 12፤24)

እየሱስ አጋንንትን ከሰዎች ሲያወጣ "ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና። እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን (ይመጣል የተባለው መሲህ) አሉ" (ማቴዎስ 12፡23) ፈሪሳዊያኖቹ ግን እየሱስ እነሱ ማድረግ የማይችሉትን ስላደረገ ተበሳጩ። ስለዚህም ሥራውን በመጥፎ አጤኑት።

ሌሎችን የሚባርክ መልካም ነገር እንኳን ሰው ሲሠራ ፈሪሳዊያን መልካሙ ሥራ የተሠራበትን ምክንያት ወደ ክፋት ያዞሩታል። ፈሪሳዊያን ሌሎችን የሚተቹ እና ለቤተሰባቸው የሚያዳሉ ስለሆኑ ይህ ሥራ የተሠራው በልጆቻቸው ቢሆን የተሠራበትን ምክንያት መልካም አድርገው በሥራውም ይኮሩ ነበር።

ፈሪሳዊያን በጣም ተጠረጣሪዎች ስለሆኑ እና ሁሉም እንደእነሱ ራስ ወዳድ ስለሚመስላቸው ሰዎች የራሳቸው ጥቅም ሳይኖርበት ሌሎችን ብቻ ለመርዳት ይሠራሉ ብለው አያምኑም። ፈሪሳዊ ክሆናችሁ ሰዎች መልካም ነገር ያሚያደርጉበትን ምክንያት በመጥፎ ታጤናላችሁ። በተጨማሪም ሌሎች የተደሰቱበትን ነገር ትተቻላችሁ።

Chapter 9
ፈሪሳዊያን በንግግራቸው ግድየለሾች ናቸው

ፈሪሳውያን ግን ሰምተው። ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ። (ማቴዎስ 12፤24)

ፈሪሳዊያን በንግግራቸው ሰውን የሚይስከፋ እና የሚጎዳ ቃላት ከመጠቀማቸው ሌላ በግዴለሽነት በሰው ላይ ይፈርዳሉ። የእግዚአብሔርን ልጅ "የአጋንንት አለቃ" ማለትን አስቡ!

ለዚህ እርኩስ የሆነ የፈሪሳዊያን ትችት እየሱስ ምን ብሎ መለሰ ሰጠ?

"በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም። (ማቴዎስ 12፡32)

እየሱስ (እንደ ሰው) ፈሪሳዊያኑን ይቅር አላቸው። ነገር ግን በሰማይ ያለው እግዚአብሔር ይቅር አላላቸውም።

ሰዎች ላይ ኃጢያትን ስናደርግ ሁለት መሠረታዊ ሁኔታዎች አሉ።

1. አግድም ወይም ኃጢያት የተደረገበትን ሰው የሚመለከት ፣

2. ወደ ላይ ወይም በእግዚአብሔር ላይ የተደረገውን የሚመለከት

ለኃጢያተችሁ ይቅር እንድትባሉ ኃጢያት የተደረገበት ሰው ይቅር እንዲላችሁ ያስፈልጋል፤ በተጨማሪም እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸሁ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር ይቅር ከማለቱ በፊት ኃጢያት አድራጊው ንስሐ መግባት አለበት። ስለዚህ ምንም እንኳን ኃጢያት የተደረገበት ሰው ይቅር ቢላችሁም ከእግዚአብሔር ፍርድ ለመዳን ወደ እግዚአብሔር ንስሐ ገብቶ ይቅርታን መጠየቅ ያስፈልጋል።ከፈሪሳዊያኑ አንዱ ወደ እያሱስ ሂዶ "ጌታ ሆይ ብዔል ዜቡል ብዬ ሰለጠራሁህ አዝኛለሁ ይቅር በለኝ" ቢል እና እግዚአብሔርንም ይቅርታ ቢጠይቅ ኃጢያቱ ይሠረዝለት ነበር። በመጨረሻ ፍርድ ሲቀርብ ለኃጢያቱ ይቅርታን የሚያገኘው በዚህ ብቻ ነው። እየሱስ በምንናግራቸው ቃላቶች እንደሚፈረዱብን አስጠንቅቆናል (ማቴዎስ 12፡37)

በህክምናም ሆነ በጸሎት እርዳታ አልድን ያለ ህመም አላችሁ? በመዝሙረ ዳዊት 105፡15 ያለውን "የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ" የሚለውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስላልተከተላችሁ ይሆን? ስለ እግዚአብሔር ሰው በግድየለሽነት ተናግራችሁ ይሆን? ህመማችሁ የማይድነው ለዚህ ሊሆን ይችላል። ወይም በቅድስናቸው እና ለእግዚአብሔር በሚሠሩት ሥራ ከእናንተ አሥር ሺ ጊዜ ያህል የሚበልጡ ሰዎች ላይ በግድየለሽነት ፈርዳችሁ ይሆን?።ይህ ከሆነ ንስሓ መግባት እና ይህን ሰው ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ይፈውሳችኋል።

Chapter 10
ፈሪሳዊያን ሃይማኖትን ሰበብ አድርገው ያለባቸውን የቤተሰብ ኃላፊነት አይወጡም

"እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?
እግዚአብሔር። 'አባትህንና እናትህን አክብር'፤ ….
እናንተ ግን። 'አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት መባ ነው የሚል ሁሉ፥
አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ።"
(ማቴዎስ
15:1-9)

ፈሪሳዊያን ወላጆቻችሁን አክብሩ የሚለውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፍ አንድ ስው ግንዘቡን ለቤተ ክርስቲያን እስከሰጠ ድረስ ዕርዳታ የሚያስገልጋቸው ወላጆቹን መርዳት የለበትም ይላሉ። የዚህ ሰው ድሃ አባት ታምሞ ቢሞትም 'ቅዱስ' የሆነው ልጁ ለወንጌል ሥራ ገንዘብ እስከሰጠ ድረስ ምንም አይደለም!!

ይህን አስተሳስብ ካለንበት ዘመን ጋር ብናነጻጽረው፤ ፈሪሳዊው ሚስቱን "ዛሬ ማታ የቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ስላለብኝ ቤት ውስጥ ልረዳሽ አልችልም" ይላል። ወይም ጥዋት መጽሓፍ ቅዱሱ ላይ ስለ መቅደስ እያጠና (ዘጸአት 25) እግዚአብሔር እንዲያናግረው ይጠይቃል። ይህን ሲያደርግ ሚስቱ ቁርስ ታበስላለች፤ ልጆቻቸውን ለትምህርት ቤት ታዘጋጃለች በተጨማሪም የሚያለቅስ ሕጻን ልጅ ታባብላች። እግዚአብሔር ለዚህ ፈሪሳዊ "መጸሓፍ ቅዱስህን ዘጋ፤ ስለ መቅደስ የምታጠናውንም ትተህ ሂድ እና ሚስትህን እርዳ"! ይለዋል። የፈሪሳዊው ጆሮ ለእግዚአብሔር ድምጽ ስለደንቆረ እግዚአብሔር ያለውን አይሰማም። የመንፈሳዊነት አንደኛው ትልቅ ነገር ቤታችን ውስጥ ለሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ ኃላፊነትን መውሰድ ነው። "ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው" (1 ጢሞቴዎስ 5፡8)።

Chapter 11
ፈሪሳዊያን በቀላሉ ይቀየማሉ

ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው። "ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን"? አሉት።
እየሱስም "ተዉአቸው" አላቸው።
(ማቴዎስ 15:12-14)

ከላይ እንዳየነው ፈሪሳዊያን ሰዎች ወላጆቻቸውን እንዳያከብሩ ያስተምሩ ነበር። እየሱስ ይህን አድራጎት ስለተቃወመ ፈሪሳዊያኑ ተከፉ። ጌታ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌን ተጠቅሞ የግሳጼ ወይም የእርማት ቃል ወደ ፈሪሳዊያን ቢልክ ፤ ፈሪሳዊያኑ በቀላሉ ይከፋሉ። በክርስትና ሕይወት ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ ትምህርቶች አንደኛው በቀላል ከመከፋት ድል ማግኝት ነው። ስትታረሙ ከመከፋት ሙሉ በሙሉ ነጻ ካልወጣችሁ ከፈሪሳዊነት ነጻ የመሆን ተስፋ የላችሁም።

ቀድሞ ቤተ ክርስቲያናችን ይመጡ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በአንዳንድ ነገሮች ላይ ስለታርሙ ከፍቶአቸው ከነጭራሹ ቤተ ክርስሪያናችንን የተዉ አውቃለሁ። እነዚህ ሰዎች ዛሬ ጠፍትው ይገኛሉ፤ እስከመጨራሻም በዚያው እንደጠፉ ሊቀሩ ይችላሉ። በእርግጠኛነት እነግራችኋለሁ፤ እናንተም መታረም ወይም ግሳጼ ካስቀየማችሁ እንደ ፈሪሳዊያኑ መንገዳችሁ ወደ ገሃነም ሊሆን ይችላል።

እየሱስ ደቀ መዛሙርቱን "ተዉአቸው" አላቸው። ተከፍተው የሄዱትን ፈሪሳዊያን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ መሞከር የለብንም። እየሱስን ታዘን የሄዱትን ፈሪሳዊያን መተው አለብን። ንስሓ ከገቡ ወደ ጌታ እና ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ ይችላሉ እንጂ ቤተ ክርስቲያን ወደ እነሱ አትሄድም።

Chapter 12
ፈሪሳዊያን መንፈሳዊ ዐይናቸው የታወረ ነው

እየሱስም "ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ" አለ። (ማቴዎስ 15:14).

ፈሪሳዊያን ስለ መጸሓፍ ቅዱስ ሊቃውንት ናቸው። ነገር ግን መንፈሳዊነታቸው የታወረ ስለሆነ ስለመንፈሳዊነት ምንም ራዕይ የላቸውም። እየሱስ እንዲህ አለ "እነሱ ወደ ጉግጓድ(ገሃነም) ይወድቃሉ እነሱን የሚከተሉም እዛው ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ" (15፡14)።

ዕውር የሆነ ሰውን አትከተሉ። የቤተ ክርስቲያን መሪያችሁ ወይም ሽማግሌያችሁ መንፈሳዊ ዕይታ ያለው እና የእግዚአብሔርን ሰዎች የሚወድ መሆን አለበት። የመንፈሳዊ እይታን የሚያሳጣው የፍቅር ወይም ለሎችን የመውደድ እጦት ሲኖር ነው። በዚህ ሁኔታ ያሉ ሰባኪዎች በስብከታቸው ሰዎችን ያወግዛሉ። እየሱስን የሚወድ ሰው ጌታን በግልጽ ስለሚያይ እየሱስን በስብከቱ ከፍ አድረጎ ሊያሳያችሁ ይችላል። እንደዚህ ዓይነት መሪ ነው መከተል ያለባችሁ። በተጨማሪም ይህን መሪ ለመምሰል መሻት አለባችሁ።

Chapter 13
ፈሪሳዊያን ግብዞች ናቸው

አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፥ እርሱም ግብዝነት ነው። ሉቃስ (12፡1)

በእንግሊዝኛ hypocrite (ግብዝ) የሚለው ቃል ከግሪክ የመጣ ነው። ይህ ቃል ( hypocrite) በግሪክ ቋንቋ የቲያተር ተዋናይ ማለት ነው። በአንደኛ ክፍለ ዘመን ጊዜ ግሪክ ሄዳችሁ እነዚህ ሰዎች (hypocrites) የት ይገኛሉ ብላችሁ ብትጠይቁ የምታገኙት መልስ "ቲያተር ቤት" ነው። ተዋናዮች መድረክ ላይ ውጥተው ለአንድ ሁለት ሰዓት ከተዋናዩ ወደ ቤታቸው ሂደው የተለምዶ ኑሮአቸውን ይኖራለ።

በሆሊዉድ ሲኒማ አንድ ሰው የቲያትር ባላሙያ ስለሆነ ለጥቂት ጊዜ እንደ መጥምቁ ዮሓንስ በጣም ቅዱስ ሆኖ ሊሠራ ይችላል። ነገር ግን በመደበኛ ኑሮው ሰካራም እና አመንዝራ ሊሆን ይችላል።

ዛሬ ብዙ ግብዞች (ተዋናዮች) ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይገኛሉ። እሁድ እሁድ ጥዋት ለአንድ ሁለት ሰዓት የተዋናይነት ሥራቸውን ይሠራሉ። በዚህ ጊዜ በታላቅ ትያትር ጌታን ማመስገናቸውን ያሳያሉ። ነገር ግን በሌሎች ቀኖች ቤታቸው ብትሄዱ እሁድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያያችሁት ቲያትር (ድራማ) እንደሆነ ትገነዘባላችሁ። ቤታቸው ውስጥ በሚታየው የተለምዶ አኗኗር ግን ኑሮአቸው የማጉረምረም፤ የምሬት፤ የሃሜት እና እርስ በርስ የመጨቃጨቅ ነው። እናንተ እንደዚህ ናችሁ? ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሌሎች የምታሳዪት እና ቤታችሁ ወይም በሥራ ቦታችሁ የምታሳዩት ይለያያል?

Chapter 14
ፈሪሳዊያን ሰዎችን በንግግራቸው ማጥመድ ይወዳሉ

ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት። ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት። (ማቴዎስ 19፡3)

ፈሪሳዊያን ሰዎች የሚናገሩንት ነገር ይዘው የተናገሩትን ሰዎች በሌሎች ፊት ማሳጣት እና መውቀስን ይወዳሉ። እንዲያውም ሊያደናቅፏችሁ ስለሚፈልጉ ጥያቄም ሊጠይቋችሁ ይችላሉ። በሜቴዎስ 22፡15 እንደምናየው "ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ።" (በተጨማሪም ሉቃስ 11፡54 ይመልከቱ)።

እኔም እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች አጋጥመውኛል። አንዳንድ ጊዜ ከሌላ ቤተ ክርስቲያን መጥተው በምሰብከው ትምህርት ልባቸው የተነካ አንዳንድ አማኞች የማስተምረውን ትምህርት ለመውቀስ እንዲያመቻችው ጥያቄዎች ይጠይቁኛል። እነዚህ ሰዎች ፍላጎታቸው ከኃጢያት ነጻ የሆነ አኗኗር ሳይሆን ሌሎች ላይ እንከን መፈለግ ነው። ፈሪሳዊያኖችም ልክ እንደዚህ ነበሩ። ኢየሱስ የተናገራችውን ቃላቶች ያለአግባባ በመጠቀም ይከሱት ነበር። እንደዚሁም የዛሬ ፈሪሳዊያን እኔ የተናገርኳቸውን ቃላቶች ይጠመዝዛሉ።

የምንወደው ሰው ምንም ቢናገር በመልካም እናየዋለን። ለምሳሌ "ምናልባት የተናገረው ነገር አልገባኝ ይሆናል። ምናልባት እየቀለደ ይሆናል"... ወዘተ እንላለን። ነገር ግን ፈሪሳዊ እንደዚህ ብሎ ነገርን አያልፍም። ስለ እየሱስ እንደዚህ ተጸፏል "...ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፥ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፤" (ኢሳያስ 11፡3) ያህን ምሳሌ ነው እያንዳንዱ የእግዚአብሔር የሆነ ሰው መከተል ያለበት።

Chapter 15
ፈሪሳዊያን ልባቸው የደነደነ ነው

ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ (ማቴዎስ 15፡8)

የፈሪሳዊ ልብ ከእግዚአብሔር የራቀ ስለሆነ ደንዳና ነው። ቅቤ ወደ እሳት ብታቅርቡት ወዲያውኑ ይቀልጣል። ነገር ግን ማቀዝቀዣ ውስጥ ብታስቀምጡት ይጠነክራል። እንደ ዲንጋይም ሊጠነክር ስለሚችል ለመቁረጥ መሮ ያስፈልጋችኋል። የፈሪሳዊ ልብ እንደዚህ ነው። እግዚአብሔር እንደ እሳት ነው። ወደ እሱ ቅርብ ብትሆኑ ልባችሁ ሁልጊዜ ገር ይሆናል። ወደ እግዚአሔር ከቀረበ ዲንጋይ እንኳን ይቀልጣል።

ሌሎች ላይ ክፉ ከሆናችሁ ከእግዚአብሔር ርቃችኋል ማለት ነው። ፈሪሳዊያን ከእግዚአብሔር እጅግ የራቁ ስለነበሩ ሌሎች ላይ ክፉ ነበሩ። ፈሪሳዊያን በአፋቸው እግዚአብሔርን ሲያከብሩ "ጌታ ሆይ ምስጋና ይገባሃል" ወዘተ... ይላሉ። ነገር ግን ራሳቸውን አይመረምሩም። እግዚአብሔርን የሚያዳምጥ ሰው የራሱን ሁኔታ ይመረምራል እንጂ ሌሎች ላይ አይፈርድም። ይህም ልቡ ገር የሆነ ሰው ምልክት ነው።

ምንም እንኳን ፈሪሳዊያን ሰዎች ላይ ክፉ ቢሆኑም የራሳቸው ቤተሰቦች ላይ ለዘብ ያሉ መሆናቸውን አይቻለሁ። ሌሌች ላይ ሕግ ያወጣሉ። ነገር ግን እነዚህን ሕጎች ቤተሰቦቻቸው ላይ አያጠብቁም። በአድልኦ እና በግብዝነት የተሞሉ ናቸው።

የማያወላውሉ አቋምች ያስፈልጉናል። መጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ ካልተገለጸ ምን እንደሚያስፈልገኝ እና ምን እንደምሠራ እኔ የራሴ የማያውላውሉ አቋሞች አሉኝ። ለምሳሌ ያህል ሌሎችን ሰዎች ቴሌቪዢን ቤታችሁ ውስጥ ያስፈልጋችኋል ወይም አያስፈልጋችሁም አልልም። ኢንተርኔት ያለው ኮምፑተር ከቴሌቪዢን የበለጠ አደገኛ ነው። ሰዎችን ስለ ሁለቱም አደገኛነት አስጠንቅቃለሁ። ነገር ግን እንደፈሪሳዊያኑ በዚህ ላይ ሰሰዎች ሕግ አላውጣም። ሰዎችን ኮምፑተር እንዳትገዙ ሲሉ ቆይተው ጥቅሙን ሲያዩ ለራሳቸው የገዙ ፈሪሳዊያን አውቃለሁ።

Chapter 16
ፈሪሳዊያን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በአደባባይ ማምለክን አይወዱም

ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው። (ማቴዎስ 21፡15)

ፈሪሳዊያን ሌሎች ሰዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እግዚአብሔርን ሲያመልኩ ማየት ይረብሻቸዋል። የሚያምኑትም እግዚአብሔር ሰዎች ፊቱ ሲቀርቡ ጸጥ እንዲሉ ፤ ሲያመልኩም ዝግ ማለት ያስፈልጋል ብለው ነው።እየሱስ ግን መንግሥተ ሰማያትን ስለሚያስታውሰው ልጆች ጮክ ብለው ሲያመልኩ ደስ ነበር ያለው። በመንግሥተ ሰማያት አንዳንዴም የመብረቅን ያህል የሚጮህ የማያቋርጥ ምስጋና ነው ያለው (የዮሓንስ ራዕይ 19፡6) ። የኛ የአምልኮ ድምጽ ገና የዚያን ያህል ከፍታ ላይ አልደረሰም። ነገር ግን ግባችን እሱ ነው። ፈሪሳዊያን በስብከት ጊዜ ሰዎች መልካም ነገር ሰምተው "አሜን" ወይም "ሃሌ ሉያ" ሲሉ ይረበሻሉ!! ዞር ዞር እያሉም እንዲህ ያለው ሰው ማን እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋሉ። እነዚህ እና የመሳሰሉ ቃላቶች በቤተ ክርስቲያን ሰብሰባ ላይ መሰማት የለበትም! ይላሉ። በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች እንደ ሃዘን ቤት ዝም ብለው መቀመጥ አለባቸው ይላሉ። እነሱ ሲዘምሩ አኳኋናቸው እየሱስ ከሞት መነሳቱን የሰሙ አያስመስላቸውም!!!

Chapter 17
ፈሪሳዊያን እውቀት አላቸው ታዛዥነትን የለባቸውም

እየሱስ እንዲህ አላቸው "ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል።
ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ። (ማቶዎስ 23:2, 3)

መጸሓፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ መጽሓፎች ሁሉ በላይ በማቴዎስ 23 ላይ እየሱስ የፈሪሳዊያንን ገጸ ባህሪ የበለጠ ይገልጻል። ማቴዎስ መዕራፍ 23 የአንደኛ ቆሮንጦስ ምዕራፍ 13 ተቃራኒ ነው። በሕግ መመራት በመንፈስ ቅዱስ ከሚገኘው አምላካዊ ፍቅር መመራት ጋር ተቃራኒ ነው። ስለዚህ ከፈሪሳዊነት እና ከሕግ አጥባቂነት ወጥተን ወደ መለኮታዊ ፍቅር ለመግባት ማቴዎስ መዕራፍ ሃያ ሶስትን በጥንቃቄ ማጥናት አለብን።

በሙሴ መቀመጫ ላይ ተቀምጠዋል ማለት ፈሪሳዊያኑ ከመጽሓፍ ቅዱስ ኮሌጅ ዲግሪ አግኝተው ብዙ ትክክለኛ የሆነ ዕውቀት ነበራቸው ማለት ነው። እየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ፈሪሳዊያን የሚሏችሁን ሁሉ አድረጉ ብሎአቸው ነበር። የሚያስተምሩት ትምህርት ትክክል ነበር ማለት ነው። ነገር ግን ትክክለኛነቱን እያወቁ እና እያስተማሩ እነሱ ግን በሚያስተምሩት አይታዘዙም ነበር።

ዕውቀት በጣም ጠቃሚ የመሆኑን ያህል አደገኛም ሊሆን ይችላል። ዕውቀት ከታዛዥነት ጋር ሲጣመር ብቻ ነው መንፈሳዊ ኑሮን የሚያመጣው። ነገር ግን ዕውቀት ያለ ታዛዥነት የመንፈሳዊ ሞትን ያመጣል። ዕውቀቱ ኖሮን የማንታዘዝ ከሆነ ዕውቀቱ ባይኖር ነው የሚሻለው። ዕውቀትን ከምግብ ጋር እንደዚሁም መታዘዝን ደግሞ ምግብ ሆዳችን ውስጥ ገብቶ ከመፈጨት ጋር ማመሳሰል እንችላለን። ምግብ ሆድ ውስጥ ሲፈጭ ነው ሰውነት የሚሆነን። ውኃን ወደ ወይን ጠጅ እንደ መቀየር ተአምር ያህል የምንበላውም ምግብ ወደ ሥጋ እና አጥንት ይቀየራል። ሰውነታችን ይህን ተአምር በየቀኑ ይፈጽማል።

ነገር ግን የምንበላው ምግብ ካልተፈጨ ሆዳችን ውስጥ በስብሶ ሊያሳምመን ወይም ሊገድለንም ይችላል። ብታስተውሉት የምንበላው ምግብ ስንበላው ቢጣፍጥም ካስመለሰን ሽታው የሚገማ ጣእሙም የበሰበሰ ነው። ይማንታዘዛቸውን ዕውቀቶች ስናከማችም እንዲሁ ነው የሚሆነው። ለዚህም ነው ብዙ ክርስቲያኖች መንፈሳቸው የማይጥመው። ከነዚህም ውስጥ መንፈሳቸው በጣም የማይጥመው ዕውቀታቸው በዝቶ ነገር ግን ለነዚህ ዕውቀቶች ታዛዥነታቸው ጥቂት ሲሆን ነው። ፈሪሳዊያን እንደዚህ ናቸው። እዚህ ላይ የሚያሳዝነው ንገር ፈሪሳዊያኑ ስለ ተበላሸው የመንፈሳቸው ሁኔታ አለመገንዘባቸው ነው። መንፈሳዊ የሆነ ሰው ግን የፈሪሳዊያንን የተበላሸው የመንፈስ ሁኔታ ቶሎ ይገነዘባል። የእግዚአብሔር የሆነ ሰው ያአንድን ሰው ፈሪሳዊነት ከአምስት ደቂቃ ውይይት በኋላ ሊገነዘብ ይችላል። ዓይኖቻቸው በትዕቢት ወይም በዝሙት የተሞላ ነው (ምሳሌ 6፡17 2ኛ ጴጥሮስ 2፡14)። የዝሙትነት ኑሮ ላይ የነበሩ ብዙ ሴቶች ከዳኑ ብኋላ መንፈሳቸው ወዲያውኑ አይጸዳም። ከዳኑ ከያሃ አመት በኋላም ዓይኖቻቸው የዝሙትንት ባህሪ ይኖራቸዋል። ወጣት ወንዶች ልጆችን ከንደነዚህ እንድትርቁ እላለሁ።

Chapter 18
ፈሪሳዊያን የሚሰብኩትን ተግባር ላይ አያውሉም

" እየተናገሩ አያደርጉትም.. " (ማቴዎስ 23፡3)

ይህ ጥቅስ የሃዋሪያት ሥራ 1፡1 ከሚለው ጋር ተቃራኒ ነው። የሃዋሪያት ሥራ ላይ እንደሚለው እየሱስ መጀመሪያ አደርገ ከዛም አስተማረ ነው የሚለው። ፈሪሳዊያን አስተማሩ ነገር ግን ያስተማሩትን አላደረጉም። እየሱስ ግን መጀመሪያ አድርጎ ከዚያም ስላደረገው ያስተምር ነበር!! እነዚህ ሁለት ተቃራኒ መንፈሶች ናቸው። የፈሪሳዊያን መንፈስ ያላቸው ጋለሞታ የሆነችውን የባቢሎን ቤተ ክርስቲያንን ይመሠርታሉ። የእየሱስ መንፈስ ያላቸው ደግሞ የኢየሩሳሌምን ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን ይመሠርታሉ።

እየሱስ ራሱ ያላደረገውን አላስተማረም። ከስብከቶች ሁሉ የላቀውን የተራራውን ስብከት (ማቴዎስ ምዕራፍ 5, 6 እና 7) ለማዘጋጀት እየሱስን ምን ያህል ጊዜ የፈጀበት ይመስላችኋል? ይህን ስብከት ለማዘጋጀት 30 ዓመት ነው የፈጀበት። ይህ ስብከት ከአእምሮ ሳይሆን ከነበረው ሕይወት የወጣ ነበር።

ሌላ ሰው ሲሰብክ የሰማችሁትን ስብከት ደግማችሁ ስትሰብኩ ይህ ስብከታችሁ በዕውቅት ላይ የተመሠረተ ከራስ የመነጨ ነው። ስለዚህ ሕይወት ወይም ቅባት አይኖረውም። እንደ እየሱስ መስበክ ከፈላጋችሁ ግን ቃሉን መጀመሪያ እንድትኖሩበት ያስፈልጋል ከዚያም መስበክ ይቻላል። አንዳንድ ሰዎች "ወንድም ዛክ ስብከትህን የኔ አገልግሎት ላይ መስበክ እችላለሁ?" ብለው ይጠይቁኛል። እኔም "መጀመሪያ የምትስብኩትን ከኖራችሁበት እና መልእክቱንም ከየት እንዳገኛችሁት በትክክል ከተናገራችሁ ትችላላችሁ" እላለሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

"ለሚንቁኝ ሁልጊዜ። እግዚአብሔር። ሰላም ይሆንላችኋል ብሎአል ይላሉ፤ በልቡም እልከኝነት ለሚሄድ ሁሉ። ክፉ ነገር አያገኛችሁም ይላሉ። ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው? …….። እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ።" (ኤርምያስ 23:17, 18, 21)

የሌላ ሰውን ስብከት ወስዳችሁ ሳትኖሩት እና ያገኛችሁበትን ሳታስታውቁ የምትስብኩት ለራሳችሁ ክብር ለማግኘት ነው። ይህ አደገኛ ልምድ የመንፈሳዊ ሞትን ያስከትላል። ስለዚህ ጉዳይ እግዚአብሔርም እንዲይ ይላል፤

"እነሆ፥ እያንዳንዱ ከባልንጀራው ዘንድ ቃሌን በሚሰርቁ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።
እነሆ፥ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው። እርሱ ይላል በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።" (ኤርምያስ 23:30, 31)

ባለፉት ሰላሳ አመታት የሰበኳቸው ትምህርቶች በተቻለኝ መጠን በሕየውቴ የኖርኩባቸው እውነቶች ናቸው። አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ። ሰዎችን የወንጌል ሰባኪ ሆናችሁ ወደ ሰሜን ህንድ ሂዱ ብዬ ሰብኬ አላውቅም። በመቶ የሚቆጠሩ የወንጌል ሰባኪዎች ወደ ሚያስፈልጉበት ቦታ ወንጌላዊያን እንዲሄዱ ያልተናገርኩበት ምክንያት እኔ ወንጌል ለመስበክ በሰሜን ህንድ ኖሬ ስለማላውቅ ነው።

አሁን የምለውን እውነቱን ተመልከቱ። ህንድ ውስጥ ያሉ የወንጌላዊ ተቋማት መሪዎች በምቾት በደቡብ ህንድ እየኖሩ ሌሎች ወደ ሰሜን ህንድ እንዲሄዱ ይገፋፋሉ። እነዚህ መሪዎች የራሳቸውን ልጆች በደቡብ ህንድ ምርጥ ትምህርት ቤት እና ኮሌጅ ይልካሉ። ነገር ግን ትምህርት ቤት የሌለበት ሰሜን ህንድ ባላገር ውስጥ ያሉትን የወንጌል ሰባኪዎች ልጆቻቸውን ወደ ሩቅ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲያስገቡ ይመክሯቸዋል። ይህን የምለው እነዚህ ሰዎች ላይ ለመፍረድ አይደለም፤ ፈራጃቸው እግዚአብሔር ነው። ነገር ግን ይህን ማለት እፈልጋልሁ፤ የነሱን አርአያ በፍጹም አልከተልም። እንደነሱ ራሴ የማላደርገውን ሌሎች እንዲያደርጉ ብሰብክ እኔም እንደነሱ ፈሪሳዊ እሆናለሁ ማለት ነው። በስሜን ህንድ ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ኖሮ ልጆቹን ያሳደገ ሰው ብቻ ነው ሌሎችም እንደሱ እንዲያደርጉ መናገር የሚችለው። የቀሩት ፈሪሳዊያን ናቸው። ይህ መርህ በሌሎች ሁኔታዎችም ላይ ተግባራዊ ነው።

ራሳችሁ ባልተለማመዳችሁት ነገር ላይ አትስበኩ። ወጣት ልጆች ከሌሏችሁ ሌሎች ወላጆችን ስለወጣት ልጅ አስተዳደግ አትምከሩ። ይህን ማድረግ ወንደላጤ የሆነ ሰው ለወላጆች ስለ ልጆቻቸው አስተዳደግ ምክር መስጠትን የሚመስል ሞኝነት ነው። አብዛኝውን ጊዜ ሌሎችን መባረክ የምንችለው ከመምከር አፋችንን ዘግተን ለነሱ በመጸለይ ነው።

ኬሚስትሪ ሳትማሩ ኬሚስቲሪ ማስተማር ትችላላችሁ? አትችሉም። የኮሌጅ ዲግሪያችሁ በእንግሊዝኛ ትምሀርት ቢሆን ማስተማር የምትችሉት እንግሊዝኛ ብቻ ነው። ይኸ አስተማሪ ሁሉ የሚያውቀው ተራ እውነት ነው። ንገር ግን ፈሪሳዊያን እንደዚህ ያለውን ተራ እውነት አያስተውሉም።

Chapter 19
ፈሪሳዊያን ሌሎችን በከባድ ሸክም ያስራሉ

"ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።" (ማቴዎስ 23:4).

ፈሪሳዊያን በሰዎች ፊት መንፈሳዊ ሆነው መታየትን ይወዳሉ። ስለዚህም ላቅ ያለ ስብከትን ያቀርባሉ። ነገር ግን የሚሰብኩትን ትምህርት ራሳቸው አይኖሩበትም።

ከዓመታት በፊት አንድ የወጣቶች ስብሰባ ላይ ከሁለት ተናጋሪዎች ውስጥ አንደኛው ነበርኩ። ሌላው ተናጋሪ ሁሉም ሰው ለእግዚአብሔር ከጊዜአቸው ከመቶ 10 (እንደ አሥራት) መስጠት አለበት ብሎ ሰበከ። ይህም ማለት በቀን 2 ስዓት ከ 40 ደቂቃ መጸሓፍ ቅዱስን በማንበብ እና በመጸለይ ማሳለፍ ማለት ነው። ስብከቱ ካበቃ በኋላ በጥያቄ እና መልስ ሰዓት ከወጣቶቹ አንዱ በዚህ ትምህርት ትስማማለህ? ብሎ ጠየቀኝ። አልስማማም ካልኩት በኋላ የተናገረውን ሰው "ወንድም አንተ በየቀኑ ለ 2 ስዓት ከ 40 ደቂቃ ያህል መጸሓፍ ቅዱስን በማንበብ እና በመጸለይ ታሳልፋለህ?" ብዬ ጠየቅኩት። እሱም በእፍረት ይህን አላደርግም አለ። እዛ የነበሩት ሁሉ ይህ ሰው ራሱ የማይሠራውን ሌሎች ላይ ግን ካባድ ጭነት የሚጭን ግብዝ ፈሪሳዊነቱን አዪ። ይህ አንድ ምሳሌ ነው።

አንዳንዶች ራሳቸው የማያደርጉትን ሌሎች ከገቢያቸው ከመቶ አሥር እንዲሰጡ ይገፋፋሉ። እንዲህ የሚያደርጉ ሁሉ ግብዝ ፈሪሳዊያን ናቸው። በክርስትና ዓለም ውስጥ ራሳቸው የማይሠሩትን አስቸጋሪ ተእዛዛትን ሌሎች ላይ ይሚጭኑ ፈሪሳዊ ሰባኪዎች ሞልተዋል። ባቢሎንን እየገነቡ የእግዚአብሔርን ሥራ የሚያፈርሱ ሰባኪዎች አሉ። በእግዚአብሔር ቃል ስዎችን ከመማባረክ ይልቅ ሰዎች ላይ ጫና ለማብዛት ይጠቀሙበታል።

ማቴዎስ 23፡4 እንዲህ ይላል፡

"ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።"

እንደነዚ ዓይነት ሰባኪዎች የእግዚአብሔርን ልጆች ከባድ ሸክም እንደሚጫንባቸው አህዮች ነው የሚያዩዋቸው። አንደ የዌንጌል መልእክት እንደ ሸክም ወይም እንደ በረከት ሆኖ ሊሰበክ ይችላል። ወሳኙ ሰባኪው ነው። ብዙ ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን የማይመጡት በእነዚህ ፈሪሳዊያን ሰባኪዎች የተነሳ ነው። ምንም እንኳን እየሱስ እና ፈሪሳዊያን ይሰብኩ የነበረው ብሉይ ኪዳን ተጠቅመው ቢሆንም የእየሱስ ስብከት ሰዎችን ነጻ ሲያወጣ የፈሪሳዊያን ትምህርት ግን ሰዎችን የባሰ የሚያስር ነበር። ዛሬም የፈሪሳዊያን ስብከት ይህንኑ ነው የሚያደርገው።

Chapter 20
ፈሪሳዊያን ከሰዎች ክብር ማግኘትን ይሻሉ

ፈሪሳዊያን "ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ" (ማቴዎስ 23፡5)

እየሱስ ፈሪሳዊያን መንገድ መጋጠሚያ ላይ ቆመው ጮክ ብለው ይጸልያሉ አለ (ማቴዎስ 6፡1)። እዚህ ላይ እየሱስ ሁኔታውን አጋንኖ ነበር የተናገረው። ይህንንም ያደርገው ይሚያዳምጡት ሰዎች ቁም ንገሩ ጎልቶ እንዲታያቸው እና ለነገሩ ትኩረት እንዲሰጡት ነበር። ለምሳሌ ዐይናቸው ውስጥ ግንድ እንዳለ ወይም ግመል እንደሚውጡ ተናግሮአል። እኔም በዚህ ነገር ላይ እየሱስን በመከተል ሰዎች ዋና ዋና የሆኑ ቁም ነገሮችን እንዲያስተውሉ አንዳንድ ነገር ላይ አጋንኜ እናገራለሁ። ሆኖም ዘገባ ወይም ሪፖርት ስናቀርብ ነገሮችን ማጋነን ትክክል አይደለም። ለምሳሌ ስብሰባ ላይ 150 ሰዎች እንደሆኑ የመጡት 200 መጡ አንልም! የእየሱስ አጋንኖ መናገር ግን ሰዎች ለመልእክቱ ትኩረት እንዲሰጡ ስለሚያደርግ ጠቃሚ ነበር።

እየሱስ አንድ ጊዜ ከሰዎች ክብር ለማግኘት ስለሚጸልዩ ፈሪሳዊያን ተናግሮ ነበር። ሁላችንም ከሰዎች ክብር ለማግኘት ጸልየን አናውቅም? እንዳንዴም ስንጸልይ ለጸሎታችን ሌሎች "ሃሌ ሉያ" ወይም "አሜን" ይሉ እንደሆነ እናዳምጣለን። ይህ ሲሆን ጸሎታችን ለሰዎች እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም። ይህም ፈሪሳዊነት ነው። ራሳችንን ከዚህ ኃጢያት ነጻ ማድረግ አለብን።

ሰባኪዎች ክብር ለማግኘት ይሰብካሉ? ሁል ጊዜ ስብከቴን ከጨረስኩ በኋላ ሰውን ለማስደሰት ነው ወይስ እግዚአብሔርን ለማስደሰት ነው የሞከርኩት ብዬ ራሴን እመረምራለሁ። ስብከቴንም እንዴት እንደማሻሽል አጠናለሁ። ምግብ የሚሠራ ሰው ሁሉ የምግቡን ጥራት ለማሻሻል ይሻል። የሚያሳዝነው ግን ጥቂት ሰባኪዎች ናቸው ስብከታቸውን ለማሻሻል የሚሞክሩ። ለዚህ ነው የብዙ ሰባኪዎች ስብከት አሰልቺ የሚሆነው። ሰባኪዎቹም ትምክህት ስላለባቸው ስብከታቸው ኃይለኛ እና የተቀባ ነው ብለው ያምናሉ። ሚስቶቻቸውን እንኳን ስለ ስብከታቸው ያላቸውን አስተያየት አይጠይቁም። ባለፉት አመታት ሁል ጊዜ ስብከቴን ለማሻሻል ጥሬአለሁ። ይህንን የማደርገው ስብከቴ እንደ እየሱስ ስብከት ጥልቅ ሆኖ የሰዎችን ልብ የሚነካ እንዲሆን ነው።

ከሰዎች ክብርን ለማግኘት የምንሞክርባቸው ሌሎች ሁኔታዎችም አሉ። ሰለ ሥራቸሁ ስትዘግቡ እግዚአብሔርን ከማግነን ይልቅ ለእግዚአብሔር ስለ ሠራችሁት ሥራ ከሌሎች አድናቆትን ለማትረፍ ይሆናል። እግዚአብሔር ሥራችንን ካወቀ ይበቃል ብለን ቤተ ክርስቲያናችንን ከጀመርን ጀምሮ (እ.አ.አ 1975) ለማንም ስለ ሥራችን ዘገባ ወይም ፎቶግራፍ ልከን አናውቅም።

ክርስቲያን ውስጥ ከማይሰበኩት ኃጢያቶች አንደኛው ከሰዎች ክብርን ስለ መሻት ነው። ክብረን መመኘት ሰውን ፈሪሳዊ ያደርጋል። ፈሪሳዊ ማቋቋም የሚችለው ባቢሎንን ብቻ ነው።

የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ለማቋቋም ከፈለግን ክብርን ከሰው ከመሻት ራሳችንን ማንጻት አለብን።

Chapter 21
ፈሪሳዊያን የሰው አለባበስ ስልት ቅድስናን የሚያሳይ ይመስላቸዋል

"አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ" (ማቴዎስ 23:5)

ሌላው የፈሪሳዊያን ባህሪ በአለባበሳቸው "ቅድስና" መኩራት ነው።

እግዚአብሔር ለእስራኤላዊያን በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ ያደርጉ ዘንድ፥ በዘርፉም ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል እንዲያደርጉ አዘዛቸው። ይህንም ያደረገው ዘርፉን ባዩ ቁጥር ከሰማይ የመጣውን የእግዚአብሔርን ትአዛዛት እንዲያስታውሳቸው ነበር። (ኦሪት ዘኍልቍ 15፡38)

ፈሪሳዊያን ዘርፋቸውን ከሌሎች ትንሽ ያረዝሙታል። ቅድስናችን ከሌሎች በላይ ነው ብለው ለመኩራት እንዲያመቻቸው የሌሎች ዝርፍ 3 ኢንች ሲሆን የነሱን ዘርፍ 6 ኢንች ያደርጉታል።

ዛሬም በሚለብሱት "ቅዱስ" ልብስ የሚኮሩ ብዙ ፈሪሳዊያን አሉ። አንድ ጊዜ ቆንጆ የሃዋይ ሽሚዝ ሰው ሰጥቶኝ ነበር። እሱን ለብሼ ብታዩኝ ምን ትላላችሁ? አንዳንድ ክርስቲያኖችን ሊያስደነግጥ ይችላል። ይህም የነሱን ፈሪሳዊነት ያሳያቸዋል።

በቂ ጊዜ መጽሓፍ ቅዱስ ላይ ስለማናጠፋ ከየሱስ ጋር የሚቃረኑ ብዙ አመለካከቶች አሉን። ስለምንለብሰው ልብስ ሰዎች ምን ይሉናል ብለን እንጨነቃለን። የእየሱስ ቅድስና ግን ልብሱ ላይ አልነገረም።

ፈሪሳዊያን ሰዎችን ለምንቀፍ እንዲያመቻቸው ሌሎች ይሚለብሱትን፣ ጫማቸውን እና ጌጣ ጌጥ አጥብቀው ያያሉ። ለእንደዚህ ዓይነት ነገሮች ዐይኖቻቸው እንደ ጩሊሌ ዐይኖች ናቸው።

እየሱስ ወንዶች እንደሴት እንዳይለብሱ ተናግሯል (ማቴዎስ 11፡8)። መንፈስ ቅዱስ ሴቶች በአግባቡ በኅፍረት እንዲለብሱ ይመክራል (አንደኛ ጢሞቴዎስ 2፡9 አንደኛ ጴጥሮስ 3፡3) ከዚህ ሌላ ቅድስና በምንለብሰው ልብስ አይገኝም። በመሠረቱ ቅድስና የውስጥ ጉዳይ ነው።

Chapter 22
ፈሪሳዊያን ሥልጣን እና ክብር የሚያሰጥ ማእረግን ይወዳሉ

"በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥
7 በገበያም ሰላምታና። መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ።
8 እናንተ ግን። መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ።" (ማቴዎስ23:6-8)

ፈሪሳዊያን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ መሆንን ይወዳሉ። ፈሪሳዊነት ያለባቸው ሚስቶችም የባሎቻችው ሽማግሌ መሆን ያኮራቸዋል። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ስለሆናችሁ ወይም ባሎቻችሁ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ስለሆኑ ትንሽ እንኳን ኩራት የሚሰማችሁ ከሆን እናንት ከፈሪሳዊያንም ታላቅ ፈሪሳዊ ናችሁ። እንዲህ ዓይነት ሽማግሌዎች ባቢሎንን ነው የሚመሠርቱት። የዱሮ ፈሪሳዊያን "መምህር" ተብሎ መጠራትን ይውዱ ነበር። የዛሬ ፈሪሳዊያን ደግሞ "ፓስተር"፣ "የተከበሩ ቄስ"፣ "ቄስ"፣ "አባቴ" (ሌሎችም የቤተ ክርስቲያን ማዕረጎች) ተብለው መጠራትን ይወዳሉ። በሁለቱ መሃል ምንም ልዩነት የለም። ወንድም ተባብላችሁ ስትጠራሩም ያ መንፈስ ሊኖርባችሁ ይችላል። እንዚህ ፈሪሳዊያን ስብሰባዎች ላይ "ፓስተርነታቸው" እንዲታውቅ ተለይተው መድረክ ላይ መቀመጥን ይወዳሉ።

ከጥቂት ዓመት በፊት አሜሪካ ውስጥ ያለ የመጽሓፍ ቅዱስ ሴሚኔሪ በኢንተርኔት ላይ ስላለኝ አገልግሎት እና ስለጻፍኳቸው መጽሓፎች የተነሳ ሆነረሪ የዶክቶር ዲግሪ ሊሰጡኝ ስለወሰኑ ፎርም ሙላ ብለው ላኩልኝ። ምንም መልስ አልሰጠኋቸውም። እየሱስ ቢሆን ሆነረሪ የዶክቶር ዲግሪ ይፈልግ ነበር? በፍጹም አይፈልግም።

"እናንተ ግን። መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም። አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና። ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ። ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል።" (ማቴዎስ 23:8-12)

የቤተ ክርስቲያናችን ብዙ አማኞች ሕይወታቸውን እንድመራላቸው ሞክረዋል። ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንድነግራቸው ይጠይቁኛል። እዚህ ላይ ምንም አልነግራቸውም። የሚመስለኝን ሃሳብ ከሰጠኋቸው በኋላ እንዲህ እላቸዋለሁ "ሂዱና እግዚአብሔርን ስለ ሰጠኋቸሁ ሃሳብ ጠይቁ። የሰጠኋቸሁ ሃሳብ ሰላም የማይሰጣቸሁ ከሆነ እሱን ጥላችሁ እግዚአብሔር የሚላችሁን አድርጉ። መሪያችሁ ክርስቶስ ብቻ መሆን አለበት"

በዚህ ነገር ላይ ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ክርስቶስ እንዳስተማረው ከማድረግ ይልቅ በሰዎች የግል ኑሮ ውስጥ ገብተው እንዴት መኖር እንዳለባቸው መንገርን ይወዳሉ። እነዚህ መሪዎች ባቢሎንን የሚገነቡ ፈሪሳዊያን ናቸው። እነሱ በሕግ ሥር ሆነው ተከታዮቻቸውንም ከሕግ ሥር እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል። ማዕረግ፣ ሥልጣን እና ክብርን ስለሚወዱ ከመንፈስ የሚገኘውን ነጻነት አያውቁም።

Chapter 23
ፈሪሳዊያን ሌሎችን ያበላሻሉ

"እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ" (ማቴዎስ 23:13)

በእውነት እና ከልባቸው የተለወጡ ወጣት አማኞች በፈሪሳዊያን መሪዎች ተበላሽተው እናያለን። እነዚህ ወጣቶች ምናልባት በመጀምሪያ ላይ ለእግዚአብሔር ለመኖር እና ኃጢያትን ለማሸነፍ ታላቅ ፍላጎት የነበራቸው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን መሪዎቻቸው እንደ ቲያትር ተዋናዮች መድረክ ላይ ቆመው ሲሰብኩ እና "በእየሱስ ስም" ገንዘብ ሰብስበው እንደ ሃብታም የሲኒማ ተዋናዮች ሲኖሩ ያያሉ። ስለዚህ እነዚህ ወጣቶች መጀመሪያ ላይ የእየሱስ ተካታዮች ሆነው እየሱስ እነደኖረው ለመኖር ነበር ፍላጎታቸው። አሁን ግን የሚሹት እንደ ታዋቂ መሪዎቻቸው ለመሆን ነው። በታማኝነት ከቆዩ አንድ ቀን እነሱም ዝናን አትርፈው የሃብታም ኑሮ እንደሚኖራቸው ያልማሉ። ስለዚህ እነዚህ ፈሪሳዊ መሪዎች የወጣቶቹን አስተሳሰብ ስለአበላሹ ወጣቶቹ የእየሱስ ተከታዮች ሆነው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዳይገቡ እንቅፋት ሆነውባቸዋል።

የዛሬ ወጣቶች የሚከተሉት መልካም አርአያ የሚሆኑላቸው ሰዎች የሏቸውም። የሚያሳዝነው ነገር ዛሬ ማንም እንደ ጳውሎስ "እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ" (1ኛ ቆሮንጦስ 11፡1) ብሎ ማለትን የሚችል ሰባኪ የለም። ስለዚህ ወጣቶች እየሱስን ተመልክተው የሱን ምሳሌ እንዲከተሉ እመክራለሁ። እየሱስን አጥብቆ የሚከተል ሰው ካገኛችሁ እናንተም የዚህን ሰው ምሳሌ መከተል ትችላላቸሁ።

Chapter 24
ፈሪሳዊያን ደሆችን ይጠቀሙባቸዋል

"እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ " (ማቴዎስ 23፡14)

ፈሪሳዊያኑ የመበለቶቹን ቤት እንዴት እንዳመነመኑ አናውቅም። እግዚአብሔር ይባርካችኋል እና ንብረታችሁን "ለጌታ ሥራ" ስጡ እያሉ ለራሳችው ሊጠቀሙበት ይሆናል። የእስራኤል በደለኛ ዳኞች ከ700 ዓመታት በፊት (ኢሳያስ 10፡2) እንዳደረጉት መበለቶቹን ይዘርፉ ነበር።

ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዚሁ ዓይነት ብዝበዛ በድሆች ላይ ይካሄዳል። "ገንዘብ ከሰጣችሁን እግዚአብሔር ይባርካችኋል ህመማችሁንም ይፈውሳል" በማለት ከመበለቶች እና ከጡረተኞች ላይ ገንዘብ በመስድ የቴለቪዥን ሰባኪዎች የታወቁ ናቸው። አሮጊቶች እና ጡረተኞች ብዙ ህመም እና የተለያዩ ችግሮች ስለሚኖሯቸው የቴለቪዥን ሰባኪዎች ይህን ሁኔታ ይጠቀሙበታል። በስነ-ልቦና ወይም በሳይኮሎጂ ማታለል፣ ብዙ ስሜትን የሚቀሰቅሱ መልእክቶችን በመናገር እና ከመጽሓፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመናገር ከድሆች ላይ ገንዘብ ይወስዳሉ። ደሃ የሆኑ መበለቶች እነዚህን ስግብግብ አታላዮች አምነው ያለቻቸውን ጥቂት ገንዘብ ይሰጧቸዋል። ሰባኪዎቹም ይህን ገንዘብ በመጠቀም ተንደላቅቀው የግል አይሮፕላን፣ ቤቶች፣ ወዘተ ገዝተው ይኖራሉ።

ይህ ድሆችን የማታለል አሠራር በአሜሪካ ቢጀመርም አሁን በዓለም ሁሉ ተሰራጭቶአል። ብዙ ሰባኪዎች ህንድ ውስጥም በዚህ አሠራር ተሰማርተዋል። እንደነዚህ ዓይነት ፈሪሳዊያን የቀን ዘራፊ እና ሌቦች ናቸው።

ጳውሎስ ወደ ሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ድንቅ ምስክርነት ሰጠ ፤

" ማንንም አልበደልንም፥ ማንንም አላጠፋንም፥ ማንንም አላታለልንም።" (2ኛ ቆሮንጦስ 2፡7)

ይህ ሁሉም የእግዚአብሔር አገልጋይ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ መናገር የሚችለው ምስክርነት መሆን አለበት።

በማናቸም መንገድ ቢሆን ደሃ የሆኑ አማኞችን ማታለል ሰይጣናዊ እና እርኩስ አድራጎት ነው።

Chapter 25
ፈሪሳዊያን በአደባባይ ረጂም እና አስደናቂ ጸሎት ይጸልያሉ

"እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ" (ማቴዎስ 23:14).

በአደባባይ ረጂም ጸሎት የሚጸልዩ የግል ጸሎት ጊዜ እንደሌላቸው ለዓመታት አይቻለሁ። ይህን የሚያደርጉ ሁሉ ፈሪሳዊያን ናቸው። ሰዎች የተሰበሰቡበት ላይ ሲጸለይ ረጂም ንግግር የሚያደርጉ ሁሉ ፈሪሳዊ መሆናቸውን ተገንዘቡ። ብዙዎች ለማመስገን የተሰበሰቡበት ላይ ሰብሳቢዎቹ እያንዳንዱ ሰው አንድ ሁለት ደቂቃ እንዲጸልይ ከጠየቁ የሚጸልዩ ሁሉ ክተሰጠው ጊዜ ገደብ ማለፍ የለባቸውም። ነገር ግን ፈሪሳዊያን ይህን የጊዜ ገደብ አያከብሩም። የነሱ ጸሎት ከሌሎች እንዲረዝም ይፈልጋሉ። የዚህም ዋነኛዎ ምክንያት ፈሪሳዊያኑ ራሳቸውን በጣም ከፍ አድርገው ከማየታቸውም ሌላ በትዕቢት እና በትምክህት የተሞሉ ስለሆኑ ነው!

መጽሓፍ ቅዱስ ሰባኪዎችን እንዲህ ብሎ ያዛል፡ "እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤"(ሮሜ 12፡6)። ይህ ማለት የስብከታችን ርዝመት እና የሕይወታችን ብስለት ተመጣጣኝ መሆን አለበት። ንገር ግን እስካሁን ካገኘኋቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከመቶ ዘጠና ያህሉ ይህን ትእዛዝ በመጣስ እሁድ እሁድ ረጂም እና አሰልቺ መልእክት ይሰብካሉ። የዚህ አለመታዘዝ ዋነኛው ምክያት ፈሪሳዊያኑ ራሳቸውን በጣም ከፍ አድርገው ስለሚያዩ ነው።

Chapter 26
ፈሪሳዊያን የወንጌል መልእክተኛ ሆነው ያገለግላሉ፤ የሚገለገሉት ሰዎችም ሁለት እጥፍ የገሃነም ልጆች ይሆናሉ

"እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ።" (ማቴዎስ 23፡15)

ምናልባት ፈሪሳዊያን የወንጌል መልእክተኛነት አስተሳሰብ ይኖራቸው ይሆናል። ነገር ግን እነሱ የሚያሳምኗቸው ሰዎች ወደ ገሃነም ይሄዳሉ። ይህም የሚሆነው አዲሶቹን አማኞች ወደ እውነተኛ ንስሓ እና እምነት ስለማያመጧቸው ነው።

ፈሪሳዊያን ዋጋ ከፍለውበት ብዙ "የሃይማኖት ሥራ" ላይ ይሳተፉ ይሆናል (የዚህ ዓይነት ሥራ የእግዚአግሔርን ፍቃድ ከማከናወን ጋር አንድ አይደለም)። ሙሉ በሙሉ የክርስቲያን ሥራ ላይ ተሰማርተውም ይሆናል ሆኖም በእንሱ በኩል የሚመጡ አዳዲስ አማኞች ሁለት እጥፍ የገሃነም ልጆች ይሆናሉ። የዚህም ምክንያት አማኞቹን ስለ ንስሓ ሳያስተማሩ እና አማኞቹ ከኃጢያት መንገዳቸው ሳይወጡ "አምነናል" ስላሉ ብቻ ዳግም መወለዳቸውን ስለሚያረጋግጡላቸው ነው። እንደዚሁም የማይስተዋሉ ቃላቶችን አናግረው በመንፈስ ሳይሞሉ እነዚህን አዳዲስ አማኞች በመንፈስ ተሞልታችኋል ብለው ያሳምኗቸዋል። የዚህ ዓይነት ንግግር ከትክክለኛው የልሳኖች ስጦታ የተለየ ነው። ስለዚህ ሰዎችን ሁለት እጥፍ የገሃነም ልጆች ያደርጓቸዋል። በመጀመሪያ በኃጢያት የሚኖሩ የገሃነም ልጆች ነበሩ። አሁን ደግሞ ምንም እንኳን ስለ ኃጢያት ያላቸው አስተሳሰብ ባይቀየርም በአንዳንድ ፈሪሳዊ ሰባኪዎች ትምህርት የተነሳ "እየሱስ ወደ ልቤ ግባ" ብለው ስለተናገሩ ብቻ የዘላለም ህይወት እንዳላቸው አምነዋል። በተጨማሪም በየጊዜው አሥራታቸውን ከከፈሉ በሰማያት ቦታ እንደተረጋገጠላቸው ተነግሮአቸዋል። ስለዚህም ከወንጌል ተለይተው ይኖራሉ። ዘላለማዊነታቸው ስለተረጋገጠላቸው የወንጌል መልእክት አይቀይራቸውም። ይህ በአሁን ጊዜ የሚካሄድ ከፍተኛ ሽንገላ ነው። ለብዙ ዓመታት በቤተ ክርስቲያኖቻችን ያሉ እንዳንድ ሰዎች ምንም እንኳን እንደገና ተወልደናል ብለው ቢያስቡም ይህ አስተሳሰባቸው ትክክል እንዳልሆነ እነግራቸዋልሁ። ብዙ ፈሪሳዊ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሰዎች ዳግም የተወለዱ መሆናቸውን ወይም አለመሆናቸውን ማስተዋል ስለማይችሉ ቤተ ክርስቲያናቸው ማንንም ሰው ትቀበላለች። በዚህም የተነሳ በቤተ ክርስትያናቸው ውስጥ ብዙ ችግሮች ይከሰታሉ።

አንዳንድ ፈሪሳዊ መሪዎች ለድሆች ያደላሉ። ስለድህነታቸው ብቻ ሊያስደስቷቸው ይሞክራሉ። ይህን ሲያደርጉ እነዚህ ፈሪስዊያን እንደ እየሱስ የሆኑ ይመስላቸዋል! (ይህ ለሃብታሞች ከሚያደሉ ሰባኪዎች ተቃራኒ ነው ፟ -ያዕቆብ 2፡1-4)። በመንፈሳዊነታችን የላቅን ነን ብለው የሚያምኑ መሪዎች የጥፋት ዝንባሌ ስላላቸው እግዚአብሔር ለእስራኤል መሪዎች "በፍርድ ነገርም ለድሀው አታድላ" (ኦሪት ዘጸአት 23:3) አላቸው። ይህን ዓይነት አድልኦ ለድሆች ስለድህነታቸው ብቻ በማሳየት እነሱን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከለሎች አስበልጠው ስለሚያዩአቸው ሁለት እጥፍ የገሃነም ልጆች ያደርጓቸዋል። እየሱስ ሃብታም እና ደሃን እኩል ለማድረግ የመጣ ኮሙኒስት አልነበረም። እኔም ኮሙኒስት አይደለሁም። ክርስቲያን ነኝ። ድሃም ይሁኑ ሃብታም ትሁት እና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎችን ሁሉ አከብራለሁ። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ክርስትናን እና ኮሚኒዝምን ያደባልቃሉ።

ስለ ቤተ ክርስቲያናችን በሁለት መንገድ ራሳቸንን እናታልላለን። አንደኛው በቤተ ከርስቲያናችን ብዙ ሃብታሞች፣ ባለሥልጣኖች (ብዙዎቹ ኃጢያተኞች ቢሆኑም) ስላሉ የተሻለ ቤተ ክርስቲያን ነው ያለን ብለን እናምናለን። ሌላው መንገድ ደሞ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ድሃዎች፣ ያልተማሩ (ብዙዎቹ ኃጢያተኞች ቢሆኑም) ተራ ሰዎች ስላሉበት የተሻለ ቤተ ክርስቲያን ነው ብለን እናምናለን። ሁለቱም የተለያየ መልክ ያላቸው ባቢሎናዊ ቤተ ክርስቲያኖች ናቸው። ድሆች ሁሉ መንፈሳዊ ናቸው ወይም ሃብታሞች ሁሉ መንፈሳዊ አይደሉም ብላችሁ አታስቡ። ድህነት እግዚአብሔርን መምሰል አይደለም። ሰዎችን ሁለት እጥፍ የገሃነም ልጆች አታድርጓቸው።

Chapter 27
ፈሪሳዊያን ከእግዚአብሔር ራእይ ሳይኖራቸው መጽሓፍ ቅዱስን ያብራራሉ

"እናንተ። ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች፥ ወዮላችሁ። እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? ደግማችሁም። ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችሁ።
እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን? ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ይምላል፤

በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤ በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል።" (ማቴዎስ 23:16-22)

ፈሪሳዊያን መጽሓፍ ቅዱስን የሚያብራሩት እነሱ በመሰላቸው ነው እንጂ ከእግዚአብሔር በተገኘ ራእይ አልነበረም። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል እንደመሰላቸው ቀይረው ይህ የእግዚአብሔር ሕግ ነው ብለው ይሰብካሉ። ዛሬም ይህን የሚያደርጉ ፈሪሳዊ ሰባኪዎች አሉ። በቃሉ ውስጥ ያለውን መንፈስ ስለማይረዱ ስብከታቸው በፊደሉ ላይ ያተኮረ ነው ፤ ነገር ግን "ፊደል ይገድላል" (2ኛ ቆሮንጦስ 3:6)። እነዚህ ሰባኪዎች በሚናገሩት ቅላቶች አይመሩም በተጨማሪም ሥርዓት አለመከተላቸውን እና በነገሮች ላይ ማወላወላቸውን አይገነዘቡም።

ለምሳሌ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጌጣ ጌጥ ማድረግ ኃጢያት ነው ብለው ያስተምራሉ። አርቲፊሻል እና ብዙ ገንዘብ የማያስወጣ ጌጣ ጌጥ የሚያደረጉ እህቶች ላይ ጥሩ አስተያየት የላቸውም። ነገር ግን እነዚሁ ሰባኪዎች ለራሳቸው ብዙ ገንዘብ የሚያወጣ እና በምቾት የተሞላ ቤት ያሠራሉ። በሚናገሩት ነገር አለመጽናታቸውን እና ሥርዓት አለመከተላቸውን አይገነዘቡም። ሕሊናቸውን ለመሸንገል መጽሓፍ ቅዱስ ስለ ጌጣ ጌጥ ነው እንጂ ቤታችሁን በውድ የእምነበረድ ድንጋይ አታድርጉ አይልም ይላሉ(1ኛ ጢሞቲዎስ 2:9; 1 ጴጥሮስ 3:3) ። ነገር ግን መጽሓፍ ቅዱስ አስፈላጊ ያልሆኑ ምቾቶችን ሁሉ እንድንተው ያናገራል።

ሌሎችም ብዙ እነዚህን የመሳሰሉ ድርጊቶች አሉ። እንደዚህ ዓይነት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቃልን የሚያስተምሩት ከመንፈስ ቅዱስ በተገኘ ራእይ ሳይሆን ለነሱ እንደሚያመች እና ሌሎች ላይ ለመፍረድ እንዲያስችላቸው አድርገው ነው።

Chapter 28
ፈሪሳዊያን ለእያንዳንዷ የሕግ ነጥብ ጥንቁቅ ናችው

"እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። (ማቴዎስ 23:23)

ፈሪሳዊያን ጥቃቅን የሁኑ የመጽሓፍ ቅዱስ ተእዛዛትን ያጋንናሉ። ቀላል እና ትናንሽ የሆኑትን ባማጋነን ዋና እና ታላላቅ አድርገው ያያሉ። ዛሬም ብዙ የዚህ ዓይነት ስብከቶች አሉ። ይህ ዓይነት ስብከት ሰዎችን ሕግ አጥባቂ ሆነው በዚህም ሁኔታቸው እንዲኮሩ ከማደረጉም በላይ ታላላቅ የሆኑ ትእዛዛትን አለመከተላቸውን እንዳይገነዘቡ ያደርጋቸዋል። እየሱስ ፈሪሳዊያንን የእንስላል፣ የከሙን ወዘተ አሥራታችሁን አትክፈሉ አላላቸውም። እየሱስ ያለው ዋና ዋና የሆኑት የእግዛብሔር ሕጎች ከአሥራት ይልቅ የበለጠ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ነው።

አራቱን ውንጌሎች አጥንቼ እየሱስ ስለተናገራቸው ዋና ዋና ርዕሶች ጽፌ ነበር። እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ፤ ንስሓ፤ የመንፈስ ድህነት፤ ገራምነት፤ ንጽህና፤ ስለ ኃጢያት ማዘን፤ ታክስን ስለመክፈል፤ ዳግም ስለመወለድ፤ እግዚአብሔርን በመንፈስ ስለማምለክ፤ ስለ ፍቅር፤ ስለ ትሁትነት፤ በትዳር ላይ ታማኝነት፤ ከሰዎች የተለምዶ ሥራዎች ስለመላቀቅ፤ ወዘተ። ስለአላባበስ ወይም ስለሴቶች ጌጣ ጌጥ ስለማድረግ ወይም ራሳቸውን ስለመሸፈን አንድ ጊዜም አልተናገረም። ነገር ግን በመጠኑ ስለመኖር እና ገንዘብን ስላለመውደድ ተናግሮአል።

ቀጥሎም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ሐዋርያት የፃፏቸውን መልእክቶች ላይ ትኩረት የተሰጣቸውን እና ያልተሰጣቸውን ርእሶች አጠናሁ። ይህንን ስላደረግሁ በስብከቶቼ ላይ የትኞቹ ርእሶች ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለብኝ ተማርኩ። እናንተም መጽሓፍ ቅዱስን እንደዚህ ካጠናችሁ እንደ ፈሪሳዊያን ሰባኪዎች ሳይሆን የምታስተምሩት ትምህርት ተመጣጣኝ ይሆናል።

Chapter 29
ፈሪሳዊያን ትክክለኛ ፈራጆች፣ መሃሪዎች እና እምነት የሞላባቸው አይደሉም

"ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። (ማቴዎስ 23:23)

ፈሪሳዊያን ከሌሎች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ትክክለኛ ያልሆነ እና ቅንነት የጎደለው ነበር። ኅብረተሰቡ ዝቅ አድሮጎ የሚያያቸው ሰዎች ላይ ምህረት አልነበራቸውም። በግል ኑሮአቸውም ታማኝ አልነበሩም። ይህ ሁሉ ሆኖ ስለሚጾሙ፣ ስለሚጸልዩ እና የመጸሓፍ ቅዱስ እውቀት ስለነበራቸው ራሳቸውን ቅዱስ አድረገው ነበር የሚያዪት። ፈሪሳዊያኑ የቆሸሸ ልብስ ለብሳ ወደ ሠርጓ እንደምትሄድ ሙሽራ ነበሩ። ሙሸሪቱም ሞገስ ስላለው አካሄዷ ላይ እንጂ የለበሰችው ቆሻሻ ልብስ ላይ አላተኮረችም። ራስ ውዳድነት፣ ትምክህት፣ ክፋት፣ እና አለመታመን በሕይወታችን እያለ በሃይማኖት አገልግሎታችን የምንመካ ከሆን፤ መንፈሳዊያን ነን ብለን ራሳችንን ነው የምናታልለው። በክርስትና ሕይወታችን ዋና ዋና የሆኑትን ነገሮች ተገንዝበን በመጀመሪያ እነሱ ላይ ማተኮር አለብን።

Chapter 30
ፈሪሳዊያን ትንኝን አጥርረው ግመሉን ይውጣሉ

"እናንተ ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ።" (ማቴዎስ 23:24)

ፈሪሳዊያን ብዙ የማያስፈልጉ ነገሮች ላይ ጥንቁቅ ናቸው (ትንኝን ያጠርራሉ)። ነገር ግን የመጽሓፍ ቅዱስ ትእዛዛትን አይከተሉም (ግመሉን ይውጣሉ)። እየሱስ ፈሪሳዊያኑን የሞቱ ትንኞችን መዋጥ መልካም ነው ማለቱ ሳይሆን ጸንተው ሥርዓት ስለማይከተሉ እና ዋና ዋና የሆኑ ነገሮች ችላ ስለማለታቸው ነው።

እንደነዚህ ዓይነት ፈሪሳዊያን በጥቃቅን ነገሮች ላይ በጣም ጥንቁቅ ናቸው። ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ንጹህ ልብስ ይለብሳሉ ቤታቸውንም በንጽህና ይጠብቃሉ። እነዚህ መልካም ባህሪዎች ናቸው። ነገር ግን እግዚአብሔር ከንዴት ወይም ከወሲባዊ ምኞት እንዲያድናቸው ከልብ አይማጸኑም። በተጨማሪም አስፈላጊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሥራ ላይ መሳተፍ ወይም ወደ ትናንሽ መንደሮች ሄደው ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ማምጣት የጊዜ እና የገንዘብ መስዋእት ስለሚጠይቅ እነዚህን እና የመሳሰሉትን ማደረግ አይፈልጉም።

በእንግሊዝኛ መጽሓፍ ቅዱስ (The Message Translation) ይህንን እንዲ ይላል "ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ የተሳሳተ የሕይወት ታሪካችሁን እየጻፋችሁ ነጠላ ሰረዝ እና ድርብ ሰረዝ ላይ ስትበረቱ ምን ያህል ጂል እንደምትመስሉ ትገነዘባልችሁ?"

በባንግሎር ከተማ ብዙ ክርስቲያኖች ገንዘብ ለማሸነፍ የሚሳተፉበት የመጽሓፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የማስታወስ ችሎታ ውድድር ይደረጋል። ይህን ውድድር ለማሸነፍ ተወዳዳሪው ጥቅሶቹን በትትክል መጻፍ ብቻ ሳይሆን ነጠላ ሰረዞችን እና ድርብ ሰረዞችን በትትክክል ማስቀመጥ አለበት!! አንዳንድ አማኞች ውድድሩን ለማሸነፍ ለሳምንታት ያህል የነጠላ ሰረዞችን እና ድርብ ሰረዞችን ቦታ ያጠናሉ። ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ኑሮአቸው ግን የመጽሓፍ ቅዱስ ትእዛዛት መከተላቸውን አያሳይም። ይህ ሁኔታቸው ለእነሱ ምንም አይመስላቸውም። በእንደዚህ ዓይነት ውድድር አንደኛ ወጥታቸሁ ዋንኛ ፈሪሳዊ ልትሆኑ ትችላላችሁ።

የወንጌል መጨረሻው እና ግቡ ፍቅር ነው። (1ኛ ጢሞቴዎስ 1:5) በፍጹም ልባችን በፍጹም ነፍሳችን በፍጹም አሳባችን በፍጹም ኃይላችን እግዚአብሔርን መውደድ አና ሌሎች አማኞችን ክርስቶስ እንደወደደን መውደድ። እንዲህ ዐይነት ፍቅር እንዲኖረን ከጣርን በክርስትና ኑሮ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው ምን እንደሆነ እንገነዘባለን።

Chapter 31
ፈሪሳዊያን በጥሩ አይን/ምስክርነት ለመታየት ስለሚሹ ውጫቸው ላይ ብቻ ያተኩራሉ

"እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ" (ማቴዎስ 23:25, 26)

ፈሪሳዊያን በውጭ የሚታየውን አኗኗራቸውን አጽድተው በራስ ወዳድነት እና በገንዘብ ወዳድነት የተሞላውን የልባቸውን ሁኔታ ግን ችላ ይሉታል። ኑሮአቸው የተመሠረተው በራስ ወዳድነት ነው። ሁልጊዜ የሚያስቡት የበለጠ ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ የበለጠ ክብር ለማግኘት እና እነሱ እና ቤተሰቦቻቸው በምቾት ኢንዲኖሩ ማድረግ ነው። የውጭ ኑሮአቸው ግን ሃይማኖተኛ እና ጻዲቅ ከመምሰል በላይ ሌሎች ክርስቲያኖች እንዲያዩላቸው ባንዳንድ አገልግሎት ውስጥ ይሳተፋሉ። ስለዚህም በሰዎች ዘንድ ዝናን ያገኛሉ።

እግዚአብሔር የሱን አድናቆት ወይስ የሰውን አድናቆት እንደምንፈልግ ይፈትነናል። በልቡ ያለውን እርከስና ችላ ብሎ በውጭ ለሰዎች የሚታየው ላይ ብቻ የሚያተኩር ሰው እግዚአብሔርን አይፈራም ማለት ነው። እንዲህ ዐይነት ሰው ፈሪሳዊ ነው። ሰዎች በውጭ የምናሳየውን ነው የሚያዩት እግዚአብሔር ግን ልባቸንን ነው የሚያየው (1ኛ ሳሙኤል 16:7) ዋነኛው የግዚአብሔር ሰው ምልክቱ በእግዚአብሔር ፊት የልቡን ንጽህና መጠበቁ ነው።

Chapter 32
ፈሪሳዊያን ሌሎች አደረጉ የሚባሉትን ክፋቶች እኛ ብንሆን አናደርገውም ነበር ይላሉ

"እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና። በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ። "(ማቴዎስ 23:29, 30)

ፈሪሳዊያን የሌሎችን ኃጢያት እና የድክመት አድራጎቶችን አይተው "እኛ እንደዚህ በፍጹም አናደርግም ነበር፣ እንደዚህ በፍጹም አንለብስም ነበር፣ እንዲህ አይነት ተግባር አንፈጸምም ነበር፣ እንደዚህ በፍጹም አንናገርም ነበር" ወዘተ ይላሉ።

ምንም እንኳን ጥሩ ክርስቲያን ብንሆንም የአዳም ልጆች ሁሉ በተፈጥሮ ብልሹ ሥጋ አንዳለው ማስተዋል አለብን። ፈሪሳዊያን በተፈጥሮአቸው ብልሹ ሥጋ እንዳላቸው አያስተውሉም። የእግዚአብሔር የሆነ ሰው ሌሎች የሚያደርጉትን ኃጢያት ሁሉ ከማደረግ ነጻ እንዳልሆነ ይገነዘባል። ኃጢያትን ከማድረግ የሚጠበቀውም በእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ይገነዘባል። አንድ የዱሮ ጻዲቅ ሰው አንድ ጊዜ ወንጀለኛ ሰው ሞት ተፈርዶበት የሞት ቅጣት ወደ ሚፈጸምበት ቦታ ተይዞ ሲወሰድ አይቶ "የእግዚአብሔር ጸጋ ባይኖር ይህ ሰው እኔ ነበርኩ አለ" ይህ ጻድቅ ሰው ልቡን ከፍቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ኃይል ባይቀበል ወንጀለኛው ሰው ያደርገውን ወንጀል ሁሉ ከማደርግ ነጻ እንዳልሆነ አስተውሏል። የእግዚአብሔር የሆነ ሰው ሁሉ ይህን ይገነዘባል። ፈሪሳዊያን ግን ይህን በፍጹም አያምኑም።

Chapter 33
ፈሪሳዊያን የእግዚአብሔርን ነብያት ያጠቃሉ

"ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ። (ማቴዎስ 23:34, 35)

ከነብይ እውነትን መስማት ፈሪሳዊያንን ይስከፋቸዋል። ስለዚህ እንደነዚህ ያሉትን ሰባኪዎች በተቻላቸው መንገድ ያጠቃሉ። የሚያወድሷቸውን ሰባኪዎች ይወዳሉ። ነገር ግን የሚገስጹ እና የሚያርሟቸውን ሰባኪዎች ይጠላሉ። የብሉይ ኪዳን ነብያቶች በፊት ለፊት ለእስራኤል ኃጢያታቸውን ይናገሩ ስለነበረ ሁሉም ተጠቅተዋል፣ አንዳንዶቹም ተገድለዋል። የእግዚአብሔር የሆነ ሰው ሲገጽሳችሁ እና ሲያርማችሁ ከከፋቸሁ ፈሪሳዊነት አለባችሁ ማለት ነው።

Chapter 34
ፈሪሳዊያን ሰዎች በነሱ ላይ ስላላቸው አስተሳሰብ ብዙ ይጨነቃሉ

"የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ ከሰማይ ብንል። እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ። ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።" (ማቴዎስ 21:25-27)

ፈሪሳዊያን በነገሮች ላይ አቋማቸውን ግልጽ ቢያደርጉ ሰዎች በአቋማቸው ላይ ስለሚኖራቸው አስተሳሰብ ይጨነቁ ነበር። አቋማቸውን የሚወስነው የእግዚአብሔር ቃል በሚያስተምረው ሳይሆን በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎች አስተሳሰብ ነው። የሮማኖች ወይም የግሪኮች አስተሳስብ አያስጨንቃቸውም ነበር። ነገር ግን የሚያተኩሩት አይሁዶች በነሱ ላይ ስላላቸው አስተሳሰብ ነበር።

የቤተ ክርስቲያናችሁ ሰዎች ፊት ጥሩ ለመምሰል ሕሊናችሁ ክሚነግራችሁ ትክክለኛ ነገር ሌላ የምታደርጉ ከሆነ ፈሪሳዊ ናችሁ። ብዙ ሰባኪዎች የሚናገሯቸው እና የሚያደርጓቸው ነገሮች አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ለማስደሰት እና በነሱ እንዲወደዱ ነው። ብዙ አማኞችም ልጆቻቸው ሥርአት እንዲኖራቸው የሚፈልጉት ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን ለራሳቸው ስም እና ክብር ነው። ስለዚህም ብዙ የማይጠቅሙ ሥርአቶችን አብዝተውባቸው በቆርቆሮ እንደተሠሩ የአሻንጉሊት ወታደሮች ያደርጓቸዋል።

እ. አ. አ. በ1987 ዓመተ ምህረት አንጋፋው ልጄ ሁለተኛ ደረጃ ጨርሶ ሁለት ኮሌጆች ተቀበሉት። አንደኛው ህንድ ውስጥ ያለው IIT ነበር ሌላው ደግሞ ከዚህ የተሻለ አሜሪካ ውስጥ ያለ ኮሌጅ (ስኮላርሺፕ ጭምር) ነበር። አሜሪካ ያለው ኮሌጅ ነው መሄድ የምፈልገው ሲለኝ "እሺ እልከሀለሁ አልኩት"።

(ዛሬ ብዙ ወጣቶች ህንድ ካለው ቤተ ክርስትያናችን ወደ አሜሪካ ሄደዋል። ነገር ግን እ. አ. አ. በ1987 ከቤተ ክርስቲያናችን አንድም የሄደ አልነበረም። በዚያን ጊዜ መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች ወደ አሜሪካ ወይም ወደ አርብ አገር አይሄዱም ብለው የሚያምኑ የፈሪሳዊ አስተሳሰብ የነበራቸው ወንድሞች ነበሩ።) ስለዚህ ልጄ እሺ ስላልኩት ተገርሞ "ልጅህን ወደ አሜሪካ መላክህን ሲሰሙ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ምን ይላሉ?" አለኝ። እኔ ግን ልጆቼ በክርስቶስ ነጻነት እንጂ ፈሪሳዊያን በፈጠሩት ሥርዓት እንዲኖሩ አላደርግም ነበር። ስለዚህ ልጄን "ይህ ሁኔታ እኔ ከሰዎች አስተሳሰብ ትጽእኖ ነጻ መሆኔን ወይም አለመሆኔን የሚፈትን ነው" አልኩት።

የሚደንቀው ነገር ልጄን ወደ አሜሪካ ስለላክሁኝ ይተቹኝ ከነበሩት ውስጥ አንዳንዶቹ ልጆቻቸውን ወደ አሜሪካ መላካቸው ነው። ፈሪሳዊያን እንደዚህ ናቸው። ለሌሎች ጥብቅ የሆኑ ሥርዓቶችን ይሰብኩና የነሱ ቤተሰቦች ላይ ሲመጣ ግን ሥርዓቶቹን ለዘብ ደርጋሉ። ከቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንኳን በጣም ጥቂቶች ናቸው ለቤተሰቦቻቸው የማያዳሉ።

የሰዎች አስተሳሰብ ትጽእኖ የሚያሳድርብን ከሆነ ልጆቻችንን ላዓለማዊነት አሳልፈን እንሰጣለን። በቤተ ክርስቲያናቸሁ ውስጥ ፈሪሳዊያን ሽማግሌዎች የፈጠሩትን የማይረባ እና አክራሪ ሥርዓቶች ተከትላችሁ የልጆቻችሁን ኑሮ አታበላሹ።

ጳውሎስ እንደዚህ አለ፤

"ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። (ገላትያ 6:14)

ሰዎችን ለማስደሰት መሻት መጥፎ ሽታ ያለው ክፍል ውስጥ እንደመኖር ነው። ከእንደዚህ ዓይነት ክፍል ውስጥ ውጥታችሁ በክርስቶስ የሚገኘው ነጻነት ወደ ሚሰጠው ጥሩ አየር ባለበት ቦታ ኑሩ።

Chapter 35
ፈሪሳዊያን ገንዘብ ይወዳሉ

" ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን" (ሉቃስ 16:14)

ብዙ ጊዜ ስለ ፈሪሳዊያን ስናስብ ለገንዘብ ያላቸውን ፍቅር አንመለከትም። ነገር ግን የገንዘብ ፍቅር ባህሪይ ግልጽ የሆነ የፈሪሳዊነት ምልክት ነው። ሌሎቹ 49 ምልክቶች እንኳን ባይኖራችሁ እና የገንዘብ ፍቅር ምልክት ብቻ ካላቸሁ ፈሪሳዊ ናችሁ። ፈሪሳዊያን ትኩረታቸውን ለጥቃቅን ሥራዓቶች ሰጥተው ገንዘብን አጥብቀው ይወዳሉ። በሉቃስ 16:13 እየሱስ እንዲህ አለ፤ "ለእግዚአብሔር እና ለገንዘብ (የቁሳቁስ ሃብት) መገዛት አትችሉም"። ፈሪሳዊያኑ ግን ገንዘብን ስለሚወዱ እና እግዚአብሔርንም የሚወዱ ስለመሰላቸው እየሱስ ላይ አፌዙ። (ቁጥር 14)። ማንኛውም አማኝ ምንም ያህል ሃብት ቢኖረው እንደ አገልጋዩ ሊጠቀምበት ይችላል። ነገር ግን ሃብቱን መውደድ ሲጀምር ፈሪሳዊ ይሆናል።

እግዚአብሔር ሰውን እንድንወድ እና ሃብትን እንድንጠቀምበት ነው የሰጠን። ነገር ግን ሠይጣን ይህንን ገልብጦ የሰው ዘር ሁሉ ሃብትን ወዶ በሰው እንዲጠቀም አደረገ። እየሱስ የመጣው ነገሮችን ለማስተካከል፣ ሰዎችን ወደን ሃብትን ለጥቅም እንድናውል (ሌሎችን በመባረክ)። የእግዚአብሔር የሆኑ ሰዎች በሃብታቸው ሌሎችን መባረክ ስለሚፈጉ ብዙ ቁሳቁስ አይሹም።

እየሱስ እንደዚህ ነበር የኖረው።

ብዙ ሰባኪዎች ሌሎች ላይ ጥቃቅን ሥርዓት ያበዛሉ እነሱ ግን ከሁሉም በላይ የገንዘብ ወዳጆች ናቸው። ፈሪሳዊ ስለሆኑ እና ሁልጊዜ አሳባቸው ገንዘብ ላይ ሰለሆነ መደበኛ ሥራቸውን ትተው ለራሳቸው ሃብት መሰብሰብ ላይ ያተኩራሉ።

Chapter 36
ፈሪሳዊያን ከሌሎች የተሻልን ነን ብለው ያስባሉ

"ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥
እንዲህ ሲል። ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ……እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ……ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ" (ሉቃስ 18:9-11)

በዚህ ምሳሌአዊ አባባል እንደምናየው በመጀመሪያ ፈሪሳዊው የጸለየው ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለራሱ ነበር።(ቁጥር 11) ከሌሎች የበለጠ ስለመሆኑ እግዚአብሔርን በልቡ አመሰገነ። ሰዎች እንዳይሰሙት ጮክ ሳይል በልቡ የተናገረው ራሱን ሲያሞግስ ሰዎች ቢሰሙት ትሁት ሰው ነው በመባል የሚያገኘውን ዝና ስለሚያጣ ነው!!

ለምሳሌ ሰው ሲናደድባችሁ እናንት ግን ንዴታችሁን ተቆጣጥራችሁ ዝም ትላላችሁ፣ ነገር ግን በልባችሁ "ጌታ ሆይ እንደዚህ ሰው ስላልሆንኩ እና ቁጣዬን ለመቆጣጠር ስላስቻልከኝ አመሰግነሃለሁ" ትላላችሁ። ይህን ስትሉ ጸሎታችሁ የፈሪሳዊው ጸሎት ጋር አንድ ነው። የተናደደባችሁ ሰው የ10 ጫማ "የቁጣ ጉድጓድ" ውስጥ ሲወደቅ እናንተ ደግሞ የ1000 ጫማ "የመንፈሳዊ ኩራት ጉድጓድ" ውስጥ ወደቃችሁ ማለት ነው። ከሁለቱ የትኛው ነው የከፋው? የተናደደው ስው ጥፋቱን ተገንዝቦ ንስሓ ግብቶ ወደ ጌታ ሊመለስ ይችላል። እናንት ግን መመጻደቃችሁን ላትገነዘቡ ትችላላችሁ። ስለዚህ ስለ መንፈሳዊ ኩራታችሁ ንስሓ አትገቡም ማለት ነው! በመጨረሻም በእግዚአብሔር ፊት የተናደደው ሰው ተሽሎ ይታያል። መንፈሳዊ ኩራት እንደ ሽንኩርት ነው። የላይኛው ቆዳ ሲገፈፍ ከሥር ሌላ አለ። እሱም ሲገፈፍ ከስሩ ደሞ አሁንም ሌላ ቆዳ አለ፣ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። በምድር እስካለን ድረስ የመንፈሳዊ ኩራትን ከህይወታቸን ጨርሶ ማስውገድ አንችልም። ነገር ግን ሌሎች ላይ መፍረድን ትተን ራሳችን ላይ ብንፈርድ ሽንኩርቱን በየጊዜው እያሳነስን እንሄዳልን።

የመንፈሳዊነት ኩራት በጣም የረቀቀ ስለሆነ በትህትና ሊሸፈን ይችላል!! አንደ የእሁድ እሁድ ቤተ ክርስቲያን የልጆች አስተማሪ ስለ ፈሪሳዊው እና ስለ ቀራጩ አስተምራ ስትጨርስ " ልጆች፣ እንደ ፈሪሳዊው ስላልሆንን እግዚአብሔር ይመስገን"!! አለች። እኛም ሳቅን እና "እንደ አስተማሪዋ ስላልሆንን እግዚአብሔር ይመስገን" አልን። በትክክል መንፈሳዊ ኩራት ብዙ ድርርብ ሽፋኖች እዳለው ሽንኩርት ነው!!

እየሱስ መጥቶ እሱን እስከምንመስል ድረስ ከኩራት እና ራስን ከመውደድ በጠቅላላ ነጻ መሆን እንችልም። እነዚህ ኃጢአቶች በጣም ብዙ ሽፋኖች እንዳለው ሽንኩርት ናቸው። በየጊዜው እነዚህን ነገሮች በሕይወታችን ስናይ ወዲያውኑ እያስወገድን ከሄድን ቀስ እያልን "ሽንኩርቱን" እያሳነስን እንሄዳለን ማለት ነው። እዚህ ላይ ግባችን እነዚህን "ሽንኩርቶች" በተቻለን መጠን ክርስቶስ እስከሚመጣ ድረስ እያሳነስን መሄድ ነው። ይህን ካደረጋቸሁ በትክክለኛው መንገድ ላይ ናችሁ፣ በተጨማሪም ፈሪሳዊ አትሆኑም።

Chapter 37
ፈሪሳዊያን በጻድቅነታቸው ያምናሉ

"ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥" (ሉቃስ 18:9)

በእምነት የሚገኘው ጽድቅነት ከእግዚአብሔር የሚገኝ ስጦታ ነው። ሌላው ዓይነት ጽድቅነት ራሳችን የምናፈራው ነው። ጽድቅናቸሁ የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ከፈለጋችሁ፣ በጽድቅናችሁ ትኮሩ እንደሆነ ራሳችሁን ጠይቁ። የምትኮሩ ከሆነ ጽድቅናችሁ እናንተ ያፈራችሁት ነው ማለት ነው። ከእግዚአብሔር ያገኛችሁት ስጦታ ቢሆን ምስጋና ታቀርባላችሁ እንጂ አትኮሩበትም። ፈሪሳዊያን የሚኮሩበት ጽድቅና ነው ያላቸው።

ስለ ጻፋችሁት መጽሓፍ ልትፎክሩ ትችላላችሁ። ነግር ግን ሌላ ሰው ሰለ ጻፈው መጽሓፍ አትፎክሩም። ስለዚህ በሕይወታችሁ ባሉት እንደ ትህትናችሁ፣ ቸርነታችሁ፣ የጸሎት ኑሮአችሁ የመሳሰሉ አንዳንድ መልካም ነገሮቻችሁ የሚያኮሩዋቸሁ ከሆኑ እናንተ ያፈራችኋቸው ናቸው ማለት ነው። በቸርነታችሁ እና በእንግዳ ተቀባይነታችሁ ብትኮሩ እነዚህ ባህሪዎች ሰው ሠራሽ ናቸው እንጂ መለኮታዊ ባህሪዎች አይደሉም። ምክንያቱም እነዚህ የእግዚአብሔር ባህሪዎች ከሆኑ እና ከእግዚአብሔር በነጻ የተሰጡ ክሆኑ እንዴት ትኮሩባቸዋላችሁ? እንግዳ ተቀባይነት መልካም ምግባር ነው፤ ነገር ግን ከኮራችሁበት ይህ ሥራችሁ በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው። ይህ መሠረታዊ ደንብ ጽድቅናን በማይመለከቱ ሌሎች ነገሮች ላይ ሁሉ ይሠራል። ምናልባት ከሌሎች የተሻለ ትዘምሩ ይሆናል ወይም የሙዚቃ መሣሪያ ከሌሎች የተሻለ ትጫወቱ ይሆናል ወይም ከሌሎች የተሻለ ትሰብኩ ይሆናል። ወይም ቤተ ክርስቲያናችሁ ክሌሎች ቤተ ክርስቲያኖች ይበልጥ ይሆናል። ማንኛችውም የምትኮሩበት ነገር እናንተ ሠርታችሁ ያፈራችሁት ነው። የእግዚአብሔር ሥራ ከሆነ ግን አትኮሩበትም።

ብዙ ሰዎች ለጌታ ስላደረጉት መስዋእቶች ጉራ ይነዛሉ። ይህ በግልጽ የሚያሳየው እየሱስ በመስቀል ላይ ለእነሱ ያደረገውን ታላቅ መስዋእት እንዳላዩ ነው። ፀሃይ ስታበራ አንድ ኮከብ እንኳን ታያላችሁ? አታዩም። እየሱስ በቀራኒዮ ያደረገው መስዋእ እንደ እኩለ ቀን ፀያይ በአእምሮአችን ሲበራልን የኛ ጥቃቅን መሰዋእቶች እንደ እኩለ ቀን ከዋክብቶች አይታዩም። በተጨማሪም "መስዋእቶች" ብለንም አንጠራቸውም። መስዋእቶቻችሁን የምታስታውሱ ከሆነ ከዋክብት በጨለማ ብቻ እንዲሚታዩ እናንተም ጨለማ ውስጥ ናችሁ ማለት ነው!!

በትህትና እና በእምነት መጥታች እየሱስ የሚሰጠውን የግዚአብሔርን ጽድቅነት ተቀብላቸሁ ዕድሜአችሁን በሙሉ ክብርን ሁሉ ለእስ ስጡ። ይህን ካደረጋችሁ ፈሪሳዊ ልትሆኑ አትችሉም።

Chapter 38
ፈሪሳዊያን ሌሎችን ይንቃሉ

"ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥" (ሉቃስ18:9)

ሰዎች ሌሎችን የሚንቁበት ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ። በልጅነታቸው ወላጆቻቸው በህብረተሰቡ ውስጥ ዝቅተኛ ቦታ የተሰጣቸውን፣ ሃብት ወይም ትምህርት የሌላቸውን ወዘተ እንዲንቁ አስተምረዋቸው ይሆናል። ትምህርት ቤት ውስጥ በጣም ብልህ ከሆናቸሁ እና ከክፍላችሁ ጥሩ ውጤቶች ካላቸሁ ሌሎች ተማሪዎችን በንቀት ልታዩ ትችችላላችሁ። በተጨማሪም ሞኝ ወላጆች ካሏችሁ እና ከሌሎች በላይ በጣም ብልህ ናችሁ እያሏችሁ ካሳደጋችሁ መጨረሻው ክዚህም ይብሳል።

ወላጆችን የምለምነው ነገር፤ ልጆቻችሁ ብልሆች ቢሆኑ ስለብልህነታቸው እየኮራችሁ አታበላሿቸው። በቤቴ ውስጥ ልጆቼ ለማንም ስለ ትምህርት ውጤታቸው ወይም ሽልማቶች እንዳይናገሩ ደንብ ነበረኝ። ይህም ኩራት ከሞላቸው የእግዚአብሔርን ፀጋ ወዲያውኑ እንደሚያጡ ስለማውቅ ነው። በዚያው ከቀጠሉ ኃጢያት ውስጥ ስለሚወድቁ ከተራ ወንድሞች ጋር ጓድኝነት መመሥረት አይችሉም። በዚህ ብዙ ወላጆች የልጆቻቸውን ሕይወት እንዳበላሹ ይሰማኛል።

ቋንቋ በትክክል የማይናገሩ ልጆች ላይ መቀለድ በልጆች መሃል የተለመደ ነው። ቤታችሁ ውስጥ ይህንን እንዳታበረታቱ መጠንቀቅ አለባችሁ። ከመሃላችን ከእናቱ ማህጸን ሲወጣ አነጋገሩ ትክክል ሆኖ የወጣ አለ? ስላለን ችሎታ ሁሉ እግዚአብሔርን ማመስገን አለብን። በዚህ መኩራት የለብንም። በመንግሥተ ሰማያት በምን እንደሚናገሩ ታውቃላችሁ? በፍቅር እና በትሀትና ነው። ይህን ዓይነት አነጋገር አሁኑኑ እንማር።

ምናልባት ቤትሽን በንጹህ የምትይዢ እና ቤት ውስጥ ሁሉ ነገር በትክክል እና በየቦታው የተቀመጠ ይሆናል። ከዚያ የሌላ ሰው ንጹህ ያልሆነ እና በግድየለሽነት የተያዘ ቤት ስታዪ የቤቱን ባለቤት ትንቂያለሽ። ይህ ሲሆን የቆሸሸው ቤት ባለቤት እግዚአብሔርን የምትፈራ ልትሆን ትችላለች። አንቺ ግን ፈሪሳዊ ነሽ።

አንዳንድ ወንድሞች የሙዚቃ ተሰጥኦ የሌላቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዝማሬያቸው እንደ ሌሎቹ ትክክል ሳይሆን የተዛባ ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር ሙዚቃውን ሳይሆን ቃላቶቹን ነውና የሚሰማው አትናቋቸው። አስተካክላችሁ ከምትዘምሩት ይልቅ አዛብቶ የሚዘምረው ወንድም ይሆናል ከልቡ የሚዘምረው። እንደዚህ ዓይነት ዘማሪዎች ጥሩ ድምጽ ያላቸውን ትሁት ስለሚያደርጉ እግዚአብሔርን ስለእነዚህ ሰዎች አመስግኜአለሁ። ቤተ ክርስቲያንን የሚያበላሹ ፈሪሳዊ ሙዚቀኞች ናቸው እንጂ የሙዚቃ ተሰጥኦ የሌላቸው ወንድሞች አይደሉም። እግዚአብሔር የሙዚቃ ችሎታ yeሌላቸውን ወንድሞች እንደ ማንኛውንም ሰው ያህል ይወዳል፣ ፈሪሳዊያንን ግን አይቀበልም። ጌታ ተመልሶ ሲመጣ ፈሪሳዊያን ብዙ ያላሰቡት ነገሮች ይጠብቋቸዋል።

ይህን ማለቴ በትምህርት ቤት አንደኛ አንውጣ ወይም ቤታቸንን አናጽዳ ወይም በሚገባ አንዘምር ማለቴ አይደለም። በተቻለን መጠን እነዚህን ነገሮች ሁሉ እናድርግ። ነገር ግን ራሳችንን ከፍ አናድርግ፣ ትሁት እንሁን እኛ ማድረግ የምንችላቸውን ነገሮች ማድረግ ያማይችሉትን አንናቅ።

በቀላሉ ሌሎችን የምንንቅባቸው ብዙ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላል። እዮብ 36:5 እንዲህ ይላል "እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም" እግዚአብሔርን እየመሰልን በመጣን ቀጥር ሰዎችን እናከብራለን እንጂ በምንም ምክንያት አንንቅም።

ስለዚህ ራሳቸንን አጽደተን እግዚአብሔር ሰዎችን እንደሚያይ ለማየት እንድንችል እንማር። "አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?" (1ኛ ቆሮንጦስ 4:7)

Chapter 39
ፈሪሳዊያን ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ያወድሳሉ

"እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና" (ሉቃስ 18:14)

ፈሪሳዊያን ራሳቸውን ከፍ ስለሚያደርጉ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የላቸውም። ከሌሎች በላይ ራሳቸውን ከፍ የሚያደርጉትን ሁሉ እግዚአብሔር ዝቅ ያደርጋቸዋል።

ራሳችንን ከሌሎች በላይ የምናደርግባቸው ብዙ የረቀቁ መንገዶች አሉ። ጠባያችን ሌሎችn የሚያሳንስ ወይም ዝቅ የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። ስጦታ ያላቸው ሰዎች እና ሙዚቀኞች በዚህ ላይ ትልቅ ፈተና አለባቸው። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሙዚቃ መሣሪያ የምትጫወቱ ከሆናቸሁ ሰዎች እንዲያደንቋችሁ አድርጋቸሁ አትጫወቱ። የምታደርጉት መእምኑ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ለመርዳት ነው እንጂ እናንትን ለማምለክ አይደለም!!

አንዳንድ ጊዜ የተጋቡ ሰዎች ስለአስደሳች የጋብቻ ኑሮአቸው ዕድሜአቸው ከፍ ላሉ እና ላላገቡ እህቶች ይነግራሉ። እንደዚህ ሲናገሩ ያላገቡት እሀቶች ሊሰማቸው የሚችለውን ከምንም ሳይቆጥሩ ስለ እነሱ የመልካም ጋብቻ ኑሮ ራሳቸውን ከፍ ያደርጋሉ። በዚህ አይነት ንግግር ሌሎችን መጉዳት አይገባም። ፈሪሳዊያን የሌሎች ሊሰማቸው የሚችለውን አዙረው አያዩም። ለዚህ ነው በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሌላቸው፣ እግዚአብሔር ትሁቶችን ነው የሚቀበለው።

ራሳችንን ከፍ ከፍ የምናደርግባቸው ሌሎች ብዙ መንገዶች ይኖራሉ። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ መንፈስ ቅዱስ እንዲያሳስበን መጠየቅ አለብን።

Chapter 40
ፈሪሳዊያን በአደረጓቸው ነገሮች ይኮራሉ

"እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ" (ሉቃስ 18:11, 12)

ጌታ እኛን ተጠቅሞ ስላደርገው ስንናገር ራሳችንን ለታላቅ ውድቀት እናጋልጣለን። ምስክረነታችን ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ እንዲሆን እንጂ እንደ ፈሪሳዊያን ባደረግነው ሥራ እንዳንኮራ በጣም መጠንቀቅ አለብን። በዚህ ነገር በተለይ ሰባኪዎች ሊወድቁ ይችላሉ። ከህንድ ወደ ምዕራብ አገሮች የሚላኩ ብዙ የክርስቲያን ሥራ ዘገባዎች አብዛኛውን ጊዜ የተጋነኑ ናቸው። እነዚህ ሠራተኞች ለእግዚአብሔር ታላላቅ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሆነ ለማሳመን ብለው በረቀቀ መንገድ ሌሎች የወንጌል አገልጋዮች ህንድ ውስጥ ከሚያደርጉት የበለጠ እየሠሩ እንደሆነ ይዘግባሉ።

ጌታን ስናገለግል ከፈሪሳዊነት ነጻ ለመሆን ራሳችንን እና አድራጎታችንን የመካብ ሥራ ፈጽሞ መደረግ የለበትም።

ለጌታ የምናደርገው ሥራ እሱ ብቻ እንዲያይ ከሌሎች መደበቅ አለብን። እግዚአብሔር ለትሑታን ብቻ ጸጋን ስለሚሰጥ በሥራችን ትንሽ እንኳን የምንኮራ ከሆንን ከጌታ ጸጋ ማግኘት አንችልም።

Chapter 41
ፈሪሳዊያን ሌሎችን ይከሳሉ

"ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው።መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች።
ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት።
የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ።" (ዮሃንስ 8:3-6).

በአመንዝራ የተያዘች ሴት በድንጋይ ትወገር ከሚለው ጀርባ ያለውን የግዚአብሔርን ልብ ፈሪሳዊያኑ አላስተዋሉም። እግዚአብሔር ሰቶች በድንጋይ ሲወገሩ ማየት አይወድም፣ ነገር ግን አመንዝራነትን ሰዎች ፈርተው እንዲሸሹ ፈለገ። እዚህ ላይ ፈሪሳዊያኑ ሕጉን ስለማክበር አልነበረም ፈላጎታቸው። ዋናው ዓላማቸው እየሱስን የሚከሱበትን ምክንያት መፈለግ ነበር። ኃጢያተኛዋን ሴት ከስሰው አሁን ደግሞ ምንም ኃጢያት የሌለበትን የእግዚአብሔርን ልጅ መክሰስ ፈለጉ። ፈሪሳዊያን እንደዚህ ናቸው። እግዚአብሔርን አይፈሩም። መልካም የእግዚአብሔር ሰው የሆነውን እንደ ማንም ይከሳሉ።

ፈሪሳዊያኑ እየሱስ የሚናገራቸውን ማንኛቸውንም ነገሮች ተጠቅመን መልሰን እሱን እንከሳለን ብለው አቀዱ። እየሱስ ሰትዮዋ "በድንጋይ ትወገር" ቢል ኖሮ ርህራሄ የለህም ብለው ሊከሱት፣ "አትውገሯት" ቢል ደግሞ አንተ የሙሴን ሕግ አትከተልም ብለው ሊከሱት ነበር። ውጤቱ ምንም ቢሆን ለማሸነፍ ተዘጋጅተው ነበር። ነገር ግን አላሸነፉም። ተሸነፉ! እየሱስ ወዲያውኑ አልመለሰላቸውም። ከአባቱ ቃል እስኪያገኝ ተቀምጦ ጠበቀ። ከአባቱ መልስ እንዳገኘ "ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት" አላቸው። ከአባቱ ያገኘው አንድ ዐረፍተነገር መፍትሔ ሆነ።

በእንደዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን የምትሰሙ ከሆናችሁ ምንም ረጂም ስብከት አስፈላጊ አይደለም። አንድ ዐረፍተነገር የጠላታችሁን አፍ ያዘጋል። ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ፈሪሳዊ ላልሆኑ እና ሌሎችን ለማይከሱ በጥበብ የተሞሉ ቃላትን ይሰጣል። ለነዚህም ሰዎች ይህን ቃል ገብቷል፣

"ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።" (ሉቃስ 21:15)

እየሱስ አመንዝራነትን ይቃወም ነበር? አዎ፣ በሚገባ ይቃወም ነበር። ነገር ግን ማመንዘርን ከመቃወሙ በላይ ሕግ አጥባቂነትን ይቃወም ነበር። ይህንንም እዚህ ላይ በግልጽ እናያለን፣ ስታመነዝር የተያዘቸው ሴት በአንድ በኩል ስትሆን ሕግ አጥባቂዎቹ ፈሪሳዊያን ደግሞ በሌላ በኩል ነበሩ። በመጨረሻም አመንዝራዋ ሴት ብቻ ቀርታ በእየሱስ እግር ስር ሆና እናያለን። የቀሩት እየሱስ በተናገረው ቃል ተባርረው ሄዱ። የሴትዮዋን እና የፈሪሳዊያኑን ሁኔታ ስናስትያይ፣ ማመንዘሯ በሴትዮዋ ዐይን ውስጥ እንዳለ ጉድፍ ሲሆን የፈሪስዊያኑ ሕግ አጥባቂነት እና ጥላቻ ግን በፈሪሳዊያን ዐይን ውስጥ ያለ ምሰሶ ነበር።

አሁን ራሳችሁን ጠይቁ፣ ስንት ጊዜ ነው መልካም ወንድሞች እና እህቶችን ማመንዘርን በሚያክል ነገር ሳይሆን በጥቃቅን ነገሮች የከሰሳችሁት። እነሱ በሌሉበት በቤታችሁ ውስጥም ሆነ በሌላ ቦታ ስለ እንሱ ያወራችሁትን አስቡ። በእንደዚህ አይነት ወሬ ስትሳተፉ በዐይናችሁ ያለው ምሰሶ - በሰው ላይ በመፍረድ፣ ሌሎችን በመክሰስ - በየጊዜው እያደገ ለመንፈሳዊ ነገሮች አሳውሮአችኋል። መጭረሻ ላይ ማንን ጎዳችሁ? ከማንም በላይ ራሳችሁን ነው የጎዳችሁት።

ዐይኑ ውስጥ ምሰሶ ያለበት የዐይን ሃኪም ሆኖ ከሌሎች ሰዎች ዐይን ውስጥ ጎድፎች ሊያወጣ ይችላል? "ዐይናቸው ውስጥ ያሉት ጥቂት ጉድፎች ብቻ ስለሆኑ ወንድም እና እህቶቻችሁን አትንኳቸው እነሱ ዐይኖች ውስጥ ያሉት ጉድፎቹ ሁሉ ቢደማመሩ ዐይናችሁ ውስጥ ያለውን መሰሶ አያክሉም።"

እየሱስ ለምንድን ነው የከሳሽ መንፈስን ይቃወም የነበረው? ምክንያቱም በሰማይ በነበረ ጊዜ ሰይጣን (የወንድሞቻችን ከሳሽ) ሰዎችን "ቀንና ሌሊት" ያለማቋረጥ ሲከስ ይሰማ ነበር (የዮሃንስ ራእይ 12:10)። ምድር ላይ ሳለ በሰዎች ላይ ይህንን የመክሰስ መንፈስ ሲያይ ሰይጣንን ያስታውሰው ነበር። እየሱስ የመክሰስ መንፈስን የዚያን ጊዜም አሁንም አይወድም። ሌሎችን ስትከሱ ለእየሱስ ሰይጣንን እንደምታውሱት ታስተውላላችሁ?። ዐይናቸው ውስጥ ያለው ምሰሶ ስለሚያሳውራቸው ብዙ አማኞች ይህን አያዩም።

አንድ ላለፈው 30 ዓመታት የሰበኩት ትምህርት፤' በመንፈስ ለማደግ ከፈለጋችሁ ሌሎች ላይ መፍረድን አቁማችሁ ራሳችሁ ላይ መፍረድ ጀምሩ'። በሚያጎላው መነጽራችሁ ራሳችሁን ነው እንጂ ሌሎችን አትዩበት። ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ልንገራቸሁ፤ በራሳችሁ ፍረዱ። ይህን መቼ ነው የምታቆሙት? ተቀይራችሁ እየሱስን ስትመስሉ ማቆም ትችላላችሁ። ሃዋሪያው ዮሃንስ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ ለአማኞች እንዲህ አለ፤

" እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን። በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።" (1ኛ ዮሃንስ 3:2, 3)

ስለዚህ እንዴት ነው የቤተ ክርስቲያን መሪ ሰዎች ሲሳሳቱ ሊያርማቸው የሚችለው? ይህን ማድረግ የሚችለው በምሕረት ብቻ ነው፤ ጌታ ለእሱ እንዳደረገለት እሱም ለሌሎች ከፍተኛ ምሕረት ማሳየት አለበት። እየሱስ አመንዝራዋ ሴት ያደረገችውን ኃጢያት ችላ አላለም። መጀመሪያ ላይ በታላቅ ርሀራሄ "እኔም አልፈርድብሽም" አላት። ቀጥሎም "ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ" ብሎ አስጠነቀቃት። የእግዚአብሔር ጸጋ ኃጢያታችንን አይቀበልም! መጀመሪያ ይቅር ይለናል፣ ቀጥሎም ያስጠነቅቀናል ከዛም ኃጢያትን እንዳንሠራ ይረዳናል።

ፈሪሳዊያኑ ለምንድን ነው ጥለው የሄዱት? ሲሆን ወደ እየሱስ መጥተው በኃጢያታቸው ከልባቸው አዝነው " "ሕግ አጥባቂ መሆናችን እና የተደበቁ ኃጥያቶቻችን ተገልጸዋልናል ጌታ ሆይ እባክህ ይቅር በለን። ከዚችም ሴት የባስን መሆናችንን ተገንዝበናል። እባክህን ምህረትህ አድርግልን" ማለት ነበረባቸው። ነገር ግን አንዳቸውም እንደዚህ ብለው ወደ እየሱስ አልመጡም።

እናንተስ? በሌሎች ላይ ልዩ ልዩ ጉድለቶችን የምታወጡ፣ ዛሬ እየሱስ እንዲገጻችሁ ትፈቅዳላችሁ?

አንዳንድ ሰዎች ስለእኔ ሰለተናገሩት ነገር መጥተው ይቅርታ ሲጠይቁ ከልባቸው እንዳልሆነ እገነዘባልሁ። ይህ የሚያሳየው ስለ ኃጢያታቸው ንስሓ ገብተው ሳይሆን ሕግ ተከትለው ለህሊናቸው እንዲመች ብለው ነው። ሕግ አጥባቂዎች ስለሆኑ ደግመው ይህን ዓይነት ኃጢያት ውስጥ እንደሚወድቁ እርግጥኛ ነኝ። በደንቡ መሠረት "ሕግ ቁጥር 347- ስለቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ እርሱ በሌለበት መጥፎ አትናገሩ" የሚለውን ሕግ ስለተላለፉ ይቅርታ ማለት እንድሚያስፈልጋቸው ተገንዝበው ነው። ስለዚህም ደንቡን ተከትለው "ሕግ ቁጥር 9 - ሰው ካስቀየማችሁ ይቅርታ ጠይቁ"!! እንደሚለው የደንቡን ያደርጋሉ። ውስጣቸው ግን የተቀየረ ነገር የለውም። ኑሮአቸው በፊት እንደነበረው ይቀጥላል።

እግዚአብሔር ኃጢያቶቻችን ላይ ብርሃን ሲያበራልን ብርሃኑ አሳውሮን እንደሞተ ሰው በየሱስ እግር ላይ ወድቀን (ዮሃንስ ራእይ 1:17) ራሳችንን በምድር ላይ ካሉት እንደ ታላላቅ ኃጢያተኞች እንቆጥራለን (1ኛ ጢሞቲዎስ 1:15)። እንደዚህ ተሰምቶአችሁ ያውቃል? ወይስ ትንሽ ስህተት ነው ያደረግንው ብላችሁ ታልፉታላችሁ? ይህን ካደረጋችሁ ፈሪሳዊያን ናችሁ ማለት ነው። ስለዚህ ነገሮች ደህና ስለማይሆኑላችሁ የሌሎች ዐይን ውስጥ ጥቃቅን ጉድፍ እያየ በዲንጋይ ስለሚወግረው ደንዳናው ልባችሁ ንስሓ ገብታችሁ እግዚአብሔር ይህን ልባችሁን እንዲያፈርስላችሁ ጠይቁ።

ያዕቆብ 2:13 እንደሚለው "ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና"። በዚህ ነገር ብዙ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በደለኞች ናቸው። ወላጆችም ልጆቻችሁ ላይ ምህረተቢስ እንዳትሆኑ መጠንቀቅ አለባችሁ።

አማኞች ማመንዘር ኃጢያት እንደሆነ ስለሚያውቁ በአመንዝራነት የወደቀ የቤት ክርስቲያን መሪ ከሥራው ይሰናበታል እንጂ ቤተ ክርስቲያኑ አይፈርስም። ስለ "ቅድስና" ስለሚሰብክ አደገኛው የሆነው ግን ሕግ አጥባቂው መሪ ነው። ይህን ያልተገነዘቡ መሪውን ተከትለው እነሱም ሕግ አጥባቂዎች ይሆናሉ። እንደ ዕውር መሪ ፈሪሳዊው እሱ ወደ ወደቀበት የሕግ አጥባቂነት ጉድጓድ ሌሎችንም ይመራል።

ሌሎች ላይ ስትፈርዱ አና ሌሎችን ስትከሱ ያላችሁ አስተሳሰብ አሥር ጊዜ እንኳን በማመንዘር ስትወድቁ ከሚኖራችሁ አስተሳሰብ እንደሚብስ አይታችኋል? ባለፈው ሁለት ወራት አሥር ጊዜ በማመንዘር ብትወድቁ ምን ያህል ነው ንስሓ የምትገቡት? የከሳሽነት መንፈስ ካለባችሁ ከዛ በላይ ንስሓ መግባት አለባችሁ።

Chapter 42
ፈሪሳዊያን እግዚአብሔር አባታቸው እንደሆነ ያስባሉ፣ ነገር ግን ትክክለኛው አባታቸው ሰይጣን ነው

"ኢየሱስም አላቸው። እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር… እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ" (ዮሃንስ 8:42, 44)

እየሱስ ፈሪሳዊያንን አባታችሁ ዲያቢሎስ ነው ብሎ ፊት ለፊት ነገራቸው። አንዳንድ ሰባኪዎች ሰው የዲያቢስ ልጅ ይሆናል ብለው አያምኑም። እየሱስ ግን ይህን አለ። እሱ እውነትን ከማንኛችንም የበለጠ ያውቃል። እነዛ ፈሪሳዊያን እግዚአብሔር አባታችን ነው ብለው ያስቡ ነበር። ነገር ግን በእርግጥ አባታቸው ሰይጣን ነበር። የዛሬ ፈሪሳዊያንም እንዲሁ ናቸው። ልጆች የአባቶቻቸውን ተፈጥሮ ያሳያሉ፤ እንደ ዲያቢሎስ አባታቸው ፈሪሳዊያን "የወንድሞች ከሳሾች" ናቸው ። የሚገርመው ነገር ብዙ "ክርስቲያኖች" ይህ የሰይጣን ባህሪ መሆኑን ሳያስተውሉ ሌሎች አማኞችን ይከሳሉ፣ ያወግዛሉ። ስለዚህ ሰይጣን አባታቸው ነው ማለት ነው! እንደዚህ አይነት ሰዎች እንዴት እግዚአብሔር አባታችን ነው ብለው ያስባሉ? ይህ ሙሉ በሙሉ እውነት ነው! የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ፈሪሳዊያን እየሱስ የነገራቸውን አላመኑም። የዛሬም ፈሪሳዊያን አያምኑትም።

ቤተ ክርስቲያናችን ለሚሳተፉ አንዳንድ ሰዎች ምንም እንኳን አስቀድመው "ጌታ እየሱስ ወደ ልቤ ግባ" ቢሉም ከሕይወታቸው በማየው ጌታን የሚያውቁ እንደማይመስለኝ ነግሬአቸዋለሁ። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ታማኝ ሆነው (እንደ እየሱስ) ለሰዎች እውነት አይነግሩም። ሰዎችን ከገሃነም ከማዳን ይልቅ የሚያተኩሩት ከሰዎች ስለሚያገኙት ክብር ላይ ነው። ስለዚሀ ያላመኑ ሰዎች ደም በነዚህ መሪዎች እጅ ላይ ነው።

Chapter 43
ፈሪሳዊያን ውሸታሞች እና ነብሰ ገዳዮች ናቸው

Paste your document here

"እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።" (ዮሃንስ8:44)

ፈሪሳዊያኑ በአመንዝራነት የተያዘችውን ሴት ለመግደል ፍላጎት ነበራቸው። የዛሬ ፈሪሳዊያን በጣም የሰለጠኑ ስለሆኑ የሚገድሉት በምላሳቸው ነው።

እውነትም እንኳን ቢሆን መጥፎ ወሬ እያወራችሁ የሰውን ስም ገድላችኋል? ሰይጣን አማኞችን ለእግዚአብሔር ሲከስ ውሸት ለእግዚአብሔር በመናገር አይደልም። ለእግዚአብሔር ውሸት መናገር እንደማይችል ስለሚያውቅ ክሶች በእውነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በከሳሽነት መንፈስ ቢሆንም ስለኃጢያታችሁ ለእግዚአብሔር የሚናገረው እውነት ነው። እንደዚሁም በከሳሽነት መንፈስ እውነት ተናግረን የአማኝ ስም ማጥፋት እንችላለን። ማንኛችሁም እንደዚህ አይነት ወሬ ስለልጆቻችሁ አታውሩም። ሴት ልጃችሁ ባመንዝራነት ብትወድቅ ቤተ ክርስቲያናችሁ ላሉት ሁሉ ስለዚህ ታወራላችሁ ወይስ በታቻላችሁ መጠን ትደብቃላችሁ? ብዙ ወንድ እና ሴት ልጆቻችሁ የማይረቡ ነገሮችን ሠርተዋል። እናንተ ወላጆች ግን የልጆቻችሁን ስም ለመጠበቅ በፍቅር ነገሮቹን ተሸፋፍናላችሁ። ይህን ለናንተ ልጆች ያደረጋችሁትን ለምን ለሌላ ወንድም ልጆች አታደርጉም? ከቤት ክርስቲያን ውስጥ "ገዳዮችን" ሁሉ ማስወገድ አለብን።

ፈሪሳዊያን ውሸታሞች ናቸው። ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ አንድ ያየሁት ነገር አለ፤ አንድ አማኝ ወደ ነበረበት ወደ ሁዋላ ሲመለስ ወዲያውኑ ውሸት ይጀምራል። ሰይጣን ወዲያው ልቡን እና ምላሱን የወሰደ ነው የሚመስለው። ውሸታቸውን አጣፍጠው እውነተኛ ይመስላሉ። እውነቱን ትተው ይህንንም ያንንም ያወራሉ። ሲናገሩም ፊታችሁን አያዩም። ዲያቢሎስ የውሸት አባት ሆኖ ውሸትን የምታፈራለት እናት ይፈልጋል። ልባችሁን ለዲያቢሎስ ስትሰጡ ብቻ ነው በናንተ በኩል ውሸትን ማፍራት የሚችለው። ጴጥሮስም ሐናንያን እንዲህ ብሎ ጠየቀው፤ "ሰይጣን በልብህ[ውሸት] ስለ ምን ሞላ?" (የሐዋርያት ሥራ 5:3) የሚዋሽ ሰባኪ በሚዋሽበት ጊዜ ምላሱን ለሰይጣን ሰጥቶአል። እንደዚህ ዐይነት ሰባኪ ኃጢያቱን ተናዝዞ እና ንስሓ ግብቶ ይህን ዓይነት ልማድ እስኪተው ድረስ እግዚአብሔር ምላሴን ይጠቀምበታል ፣ይቀባኛልም ብሎ ማሰብ አይችልም።

ግድያን የምንጠላውን ያህል ውሸትንም መጥላት አለብን።

Chapter 44
ፈሪሳዊያን የማያዳምጣችውን ያጠቃሉ

ፈሪሳዊያኑ (እውር ለነበርው እና አሁን ለዳነው)" መልሰው። አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወለድህ፥ አንተም እኛን ታስተምረናለህን? አሉት። ወደ ውጭም አወጡት (ከሲናጎግ አስወጡት)። "(ዮሃንስ 9:34).

ፈሪሳዊያኑ እውር ሆኖ ለተወለደው ሰው ዐይኖቹ እንዲያዩለት ፈውስ መስጠት አልቻሉም። እየሱስ ግን ፈወሰው። ፈሪሳዊያኑ በዚህ ፈውስ ተናደው ኃጢያተኛ ነህ ብለው የተፈወሰውን ሰው ከምኩራባቸው አባረሩት።

ፈሪሳዊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ትእዛዛቸውን ሰዎች ካልተከተሉ ከቤተ ክርስቲያናችን ትወጣላችሁ ብለው ያስፈራራሉ። ፈሪሳዊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሰዎች ላይ ያላቸውን ሥልጣን እና ሰዎችን በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግን ይወዳሉ። እየሱስ ወንድምህ ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ወቅሰህ ወደ መልካም መልሰው (ማቴዎስ 18:15)። ሰውን ከቤተ ክርስቲያን ማባረር የመጨረሻ እርምጃ መሆን አለበት። ሁልጊዜ አላማችን ወንድሞችን ከኃጢያት ማዳን መሆን አለበት።

አማኞች በኃጢያት ሊወድቁ እና ስህተት ሊሠሩ ይችላሉ። ይህ ሲሆን የዚህ ሰው ቤተ ክርስቲያን መሪ ሁለት ምርጫ አለው፤ እየሱስ እንደተናገረው ይህን ሰው ማናገር ወይም ፈሪሳዊያን የሚያደርጉትን ማድረግ። እየሱስ የሚፈልገው ይህ ወንድም መንገዱን ቀይሮ እንዲመለስ ነው። ዲያቢሎስ ግን ይህን ሰው ሊያጠፋ ነው የሚፈልገው። ፈሪስዊያን ከዲያቢሎስ ጋር እንድ ላይ ሆነው እነሱን የማይሰሙትን እና ለእነሱ ሥልጣን የማይገዙትን ሁሉ ያስቸግራሉ፣ ያጠቃሉ።

Chapter 45
ፈሪሳዊያን እነሱ ማድረግ የማይችሉትን ተአምር የሚያደርጉ ሰዎች ላይ ይቀናሉ

"እንግዲህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰብስበው። ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና…እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ።" (ዮሃንስ 11:47, 53)

ዮሃንስ 11 ላይ እየሱስ አላዛርን ከሞት እንደ አስነሳ እናያለን። በዚህ ፈሪሳዊያን መደሰት ነበረባቸው። ተአምሩን ያደረገው ሰው ከነሱ መሓል ስላልሆነ አልተደሰቱም! እየሱስ ከነሱ ሳይሆን ከሌላ የሃይማኖት ወገን (ዲኖሚኔሽን) ነበር! በዚህ የተነሳ ፈሪሳዊያኑ በጣም ቀንተው ነበር። ቅናት በጣም ግልጽ ነው። ስለሆነም የፈሪሳዊያኑን ቅናት ዓለማዊው ጲላጦስ እንኳን ተገንዝቦት ነበር። (ማቴዎስ 27:18) ስለ ቅናት ተጠንቀቁ።

ፈሪሳዊያን ተአምር የሚያደርጉ ሰዎች ላይ ይቀናሉ። ዛሬ የሚታየው የቴሌቪዥን ወንጌላዊያን የሚያደርጉት እና ሰውን የሚያታልሉበት የውሸት "ተአምራትን" ማለቴ ሳይሆን ዛሬም በየቦታው የሚደረጉትን እውነተኛ ተአምራትን ማለቴ ነው። እነዚህን ተአምራት በቴለቪዥን ላይ የሚታዩ ሳይሆኑ (በሓዋሪያት ሥራ ላይ እንዳለው) ወንጌል ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሰበክባቸው ቦታዎች ላይ ይታያሉ። ለምሳሌ ሰሜን ህንድ እንዲህ ዓይነት ቦታ ነው። የሓዋሪያት ሥራ ላይ ብዙ ተአምራት ይደረጉ የነበሩት ወንጌል ለመጀመሪያ ጊዜ የሚስበክባቸው ቦታዎች ላይ መሆኑን ብዙዎች አይገነዘቡም። ዛሬ ተአምራትን ለማድረግ እግዚአብሔር የሚጠቀምባቸው ሰዎች ያልታወቁ ተራ አማኞች ናቸው። እኑሱም እንደ እየሱስ ስላዩት ትአምራት ለሌሎች አያወሩም።

እግዚአብሔር የተአምራት እግዚአብሔር ነው። ተአምራትን አያደርግልንም ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ ፈሪሳዊ ናችሁ ማለት ነው። ስትታመሙ ህመማችሁን ከመቀበል እግዚአብሔር እንዲፈውሳችሁ ጸልዩ። የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን ሌሎች የሌላቸው መብቶች አሉን። "ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል"( ዕብራውያን 6:5) መቅመስ እንችላለን። ፈውስን ማግኝት የእግዚአብሔር ፍቃድ ካልሆነ ለጳውሎስ እንደሰጠው (2ኛ ቆሮንጦስ 12:7-10) "ከፈውስ የተሻለ ነገር" እንዲሰጣችሁ ጠይቁ። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ከሆናችሁ እና የታመሙ ሰዎች ጸልዩልን ቢሏችሁ ባላችሁ እምነት ለታመሙት ፈውስ እና እግዚአብሔር ወደ እሱ እንዲያቀርባቸው መጸለይ አለባችሁ። እግዚአብሐር ለጸሎታችሁ መልስ የታመሙትን ሲፈውስ ምስጋና እና ክብርን ለእግዚአብሔር ብቻ ስጡ እንጂ እናንተ እንዳትሞገሱበት መጠንቀቅ አለባችሁ። ይህን ካደርጋችሁ ፈሪሳዊ ትሆናላችሁ።

Chapter 46
ፈሪሳዊያን የሚያደርጉትን በማያደርጉ የእግዚአብሔር ሰዎች ላይ ይፈርዳሉ

ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ። ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም አሉ። (ዮሃንስ 9:16)

ፈሪሳዊያን ሰዎችን የሚገመግሙት በመለኮታዊነታቸው ሳይሆን ሥነ ሥርዓት ተከታዮች በመሆናቸው ወይም ባለመሆናቸው ነው። እየሱስ ከእግዚአብሔር አይደለም ብለው ያሉት እንደ እነሱ ሰንበትን አላከበረም ብለው ነበር። እኛም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳንድ ነገሮች እኛን እንደሚመስሉን መደረግ አለባቸው እንል ይሆናል። እኛ እንደሚመስለን ያማያደርጉ ሰዎችን ከእግዚአብሔር አይደሉም እንል ይሆናል። አግባብ የሌለው ጥላቻ ቤተ ክርስቲያንን ሊያፈርስ የሚችል ታልቅ መቅሰፍት ነው።

ሳልቬሽን አርሚ (በ19ነኛው ክፍለ ዘመን ዊሊያም ቡት በሚባል ሰው የተጀመረ ቤተ ክርስቲያን) በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጊዜአቸው የክርስቶስ እራት አይወስዱም። ይህንንም የሚያደርጉበት ምክንያት ብዙዎቹ አዳዲስ አማኞች ብዙ ይሰክሩ የነበሩ ስለሆነ ወይን ጠጁ ሲሸታቸው የዱሮው ጠባያቸው እንዳይቀሰቀስባቸው ነው። ብዙ የተጠመቁ አማኞች ከልብ የተቀየሩ ስላልነበረ የውኃ ጥምቀትን አቁመው ነበር። ነገር ግን ዊሊያም ቡት በዚያን ጊዜ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ስለነበረ እሱና ሚስቱ በሺ የሚቆጠሩ ብዙ ሃገር ውስጥ የተጣሉ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ አምጥተዋል። ስለ እንደዚህ አይነት ሰው ምን ታስባላቸሁ? ፈሪስዊያን በፍጹም አይቀበሉትም። እኔ ግን የዛሬ 150 ዓመት እንግሊዝ አገር የምኖር ቢሆን ኑሮ ከዊሊያም ቡት በስተቀር ሌሎች በማያደርጉት ሥራ ላይ ተሳትፌ ሰካራሞችን፣ ሴትኛ አዳሪዎችን፣ እና ሌቦችን ወደ ክርስቶስ አመጣ ነበር። በጌታ ራት እና በጥምቀት አቋማቸው ላይ አልስማማም ሆኖም በዚህ የተነሳ ብቻ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን አቋም አልገመግምም።

እንደ እነ ዊሊያም ቡት የመሳሰሉትን ሰዎች ከመተቸት መጠበቅ አለብን። በእርግጥ ጴጥሮስ አቋሙን ስላወላወለ ጳውሎስ ተችቶት ነበር (ገላቲያ 2:11)። ሆኖም እግዚአብሔር ለጳውሎስ የሰጠውን ጸጋ ጴጥሮስ ተገንዝቦ ነበር (ገላቲያ 29)። ስለዚህም እንደ ጳውሎስ ያለ ሰው ጴጥሮስን መተቸት ይችላል።

ዛሬ የእግዚአብሔርን ሰዎች የሚተቹ እነማን ናቸው? አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ አይነት ሰዎች ለጌታ ምንም ያላገለገሉ እና እግዚአብሔር ያልመሰከራላቸው ናቸው። እንደነዚህ አይነት ሞኝ አማኞች እግዚአብሔር የነሱን ሺ እጥፍ ያህል የሚጠቀምባቸውን ሰዎች መተቸት ይወዳሉ። ይህ ፈሪሳዊነት ነው።

Chapter 47
ፈሪሳዊያን እግዚአብሔር ምልክቶች እንዲሰጣቸው በመጠየቅ እግዚአብሔርን ይፈትናሉ

በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና። መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን አሉ። (ማቴዎስ 12:38).

ፈሪሳዊያን እውነት ነው ብለው ነገሮችን ለመቀበል ምልክት ወይም ተአምር ማየት ስለሚፈልጉ በእምነት ብቻ መኖር አይችሉም። ስለዚህም ነው የማያውቁትን እናውቃለን የሚሉ የሃይማኖት መሪዎች የሃሰት ምልክቶችን በማሳየት ፈሪሳዊያንን የሚያታልሉት። ተአምር እና ምልክት እንዲያሳያችሁ እግዚአብሔርን መጠየቅ መንፈሳዊነት እንዳይመስላችሁ። ይህ የፈሪሳዊ ምልክት ነው። ይህ ቃል በማቴዎስ 16:1 ተደግሞ እናየዋለን።

Chapter 48
ፈሪሳዊያን ስለ ጠፉ ሃጢያተኞች ግድ የላቸውም

ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው ብለው መለሱላቸው። (ዮሃንስ 7:49)

የዛሬ ፈሪሳዊያንም ወደ ገሃነም ስለሚሄዱ ሰዎች የዚሁ አይነት አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይችላል። "እነዚህ እየሱስን አዳኛቸው አድርገው የማይቀበሉ ሰዎች ገሃነም ይገባሉ" ይላሉ። ነገሩ እውነት ነው። ሆኖም እንደዚህ የሚናገር ስው ስለ ጠፉት ሰዎች ግድ ሰለሌለው ፈሪሳዊ ነው ማለት ነው። ወደ ገሃነም ስለሚሄዱት ሰዎች ግድ ከሌላችሁ ፈሪሳዊነታችሁ የተረጋገጠ ነው።

ለሌሎች ስንመሰክር ሊጨንቅን ያሚገባው የመዳናቸው ጉዳይ ነው እንጂ ደማቸው በእጃችን ላይ እንዳይሆን ፍራቻ መሆን የለበትም። አንዳንድ ክርስቲያኖች ድርሻቸውን መወጣት ስለሚመስላቸው ትንንሽ ጽሁፎችን ምንም ሳይለዩ በየመኪናው ላይ እና በየቤቱ ሲያሰራጩ አይቻለሁ። "ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና" (ዮሃንስ 3:17)። ነገር ግን ዛሬ ይሚሰራጩ እንደዚህ አይነት ጽሁፎች ወጤት የማያምኑትን ሰዎች የሚንቅፍ እና የሚኮነን ነው። ይህ አድራጎት ከራስ ወዳድነት የተነሳ ለአድራጊው ህሊና እንዲመች ነው እንጂ ላላመኑት ስላለው ፍቅር የተነሳ የጠፉትን ወደ አዳኛቸው እግር ላማምጣት አይደለም። ጽሁፍ ከሚያሰራጩ አብዛኛዎቹ ለጠፉት የሚጨነቁ ሊመስላቸው ይችላል። ይህ አስተሳሰብ ግን ትክክል አይደለም። ይህን የሚያደርጉ ፈሪሳዊያን ናቸው።

Chapter 49
ፈሪሳዊያን ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ለባሀላዊ አድራጎታቸው የበለጠ ክብር ይሰጣሉ

እንዲህም አላቸው። "ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል።"(ማርቆስ 7:9)

ቤተ ክርስቲያኖች ሁሉ ባህላዊ የሆኑ ሥርዓቶች አሏቸው። እነዚህ ሥርዓቶች ከእግዚአብሔር ቃል ከበለጡባችሁ ፈሪሳዊያን ናችሁ ማለት ነው። እየሱስ ፈሪሳዊያንን ባህላዊ ሥርዓታችሁን ከእግዚኣብሔር ቃል አብልጣችሁ ካያችሁ በየጊዜው (1)" የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ"፣ (2) "ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል"፣(3)" ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ"(ማርቆስ 7:8-13) አላቸው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ከኃጢያት ነጻ መሆን አለመሆናችንን ሁላችንም ራሳችንን መመርመር አለብን። በተለምዶ የምታደርጓቸው ባህላዊ ሥርዓቶች እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችሁ ከመውደድ እና ሌሎች አማኞችን (ከሌላ ሃይማኖት ወገን ቢሆኑም) እየሱስ እንደወደዳችሁ ከመውደድ ይበልጥባችኋል? የናንተን የቤተ ክርስቲያን የተለምዶ ሥርዓቶች የማይከተል የእግዚአብሔ ልጅ በናንተ ዘንድ ተቀባይነት ያጣል? ይህ ከሆነ ፈሪሳዊ ናችሁ።

Chapter 50
ፈሪሳዊያን በሰዎች ፊት ራሳቸውን ማጽደቅ የወዳሉ

እንዲህም አላቸው። "ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኵሰት ነውና"። (ሉቃስ 16:15)

አዳም ስላደርገው ኃጢያት ሃላፊነትን አልወሰደም። እግዚአብሔር "ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በውኑ በላህን?" ብሎ ሲጠይቀው። ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛው መልስ "አዎ ጌታዬ" መሆን ነበረበት። እሱ ግን እንዲህ አላለም። መጀመሪያ በሚስቱ ከዚያም ይችን ሚስት በሰጠው በእግዚአብሔር አሳበበ!! (ዘፍጥረት 3:12) ።ራስን ማጽደቅ ማለት ይህ ነው። በዚህ የተነሳ አዳም ከገነት ተባረረ።

በመስቀል ላይ የነበረው እና የዳነው ሌባ ከዚህ በጣም የተለየ ነበር። "በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው" አለ።(ሉቃስ 23:41) በሁሉም ቦታ እና ሁኔታ ላይ ፈሪሳዊ ራሱን እንደ ጻዲቅ አድርጎ ያሳያል። ራሱን ዝቅ በማድረግ በትህትና ስህተቱን መቀበል እና ስለ ሠራቸው ኃጢያቶች ራሱን ጥፋተኛ ማድረግ አይችልም። የተሰቀለው ሌባ በአግባብ ባላሳደጉት ወላጆቹ፣ ባሳሳቱት ጓደኞችቹ ወይም በፈረደበት ዳኛ ላይ አላሳበበም። ገነት ኃጢያታቸውን አምነው ለሚቀበሉ እንጂ በሌሎች ላይ በሚያሳብቡ ስላልሆነ ሙሉ በሙሉ "እውነተኛ ፍርድ ነው" ያገኘሁት በማለቱ በዚያኑ ቀን ከእየሱስ ጋር ወደ ገነት ሄደ።

ራሳችሁን ጻድቅ ለማስመሰል ሚስታችሁን፣ እግዚአብሔርን ወይም ሌሎች ላይ የምታሳብቡ ከሆናችሁ ወደ ገሃነም እያመራችሁ ያላችሁ ፈሪሳዊያን ናችሁ። እየሱስ ለፈሪሳዊያን መጨረሻ ላይ የተናገረው የሚያስፈራ ነበር፤ "እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?" (ማቴዎስ 23:33)

"ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤ አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና።የወንድማማች መዋደድ ይኑር።"(ዕብራዊያን 12:28 እስከ 13:1)

ፈሪሳዊነት ያመረቀዘ ቡግንጅ ውስጥ እንዳለ መግል ነው። በየቀኑ ስትጫኑት መግል መውጣቱን ይቀጥል። በመጨራሻም ሁሉም ወጥቶ አልቆ ከመግል ነጻ ይሆናል። እንዲሁም ፈሪሳዊነታችን ተጠራርጎ እስኪለቀን ድረስ ውስጥችን ያለውን ሁልግዜ ጨምቅን ማውጣት አለብን።

ይህንን በቅንነት እናስተውል፤

"ጌታዬ ሆይ ጥፋተኛው እኔ ነኝ፣ ፈሪሳዊ የሆኑት ባለቤቴ፣ ወይም ወንድሜ፣ ወይም እህቴ፣ ወይም ለሎች ሰዎች አይደሉም። ፈሪሳዊ የሆንኩት እኔው ራሴ ነኝ። እንድትምረኝ እና ከፈሪሳዊነት ነጻ እንድታወጣኝ እለምነሃለሁ። ያንተ ተከታይ እና መልካም የእግዚአብሔር ሰው እንድሆን ጸጋህን አብዛልኝ። ለእኔ ምሕረትህን እንዳሳየኸኝ እኔም እንዲሁ ለሌሎች ሁልጊዜ ምሕረት እንዳደርግ አስችለኝ"

ዕድሜአችንን ሁሉ በዚህ መንገድ ተጉዘን አንድ ቀን ወደ እሱ መንግሥት በደስታ እንድንገባ ጌታ ይርዳን።

አሜን አሜን