ወንጌል እግዚአብሔር መጀመሪያ ላይ ሰውን ሲፈጥር እንዲኖር የፈለገውን አኗኗር አሁን መኖር እንደምንችል የሚያበስር የምሥራች ዜና ነው። ለክርስቶስ ሕግ ሙሉ በሙሉ የሚገዛ ሰው ሁልጊዜ በድል የተሞላ ሕይወትን ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን እየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው የተቀበሉ ብዙ ሰዎች የወንጌል ምስራች ወደ ሚጋብዘው የክብር ሕይወት ውስጥ ገና አልገቡም።
ለምን? አብዛኝውን ጊዜ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የክርስትና ሕይወታቸው ሲጀመር በጥሩ መሠረት ስላልተጀመረ ነው።
በክርስቶስ ዳግም ስንወለድ ያለን ሕይወት አዲስ ከሚገነባ ህንፃ ጋር ይመሳሰላል። ቤት ሲገነባ በጣም ወሳኝ የሆነው የቤት ክፍል መሠረቱ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ሶስተኛው ፎቅ ላይ ግድግዳው ቢሰነጠቅ ይህ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ መሠረቱ በደንብ እንዳልተሠራ ይጠቁማል። ሕይወታችንም ከዚህ ጋር ይመሰላል። በክርስቶስ ካመንን ከዓመታት በኋላ ክርስትናን ስንጀምር የተደረጉ ስህተቶች ውጤቶች መታየት ይጀምራሉ።
አዲስ ኪዳን በሃጢያት ላይ የድል ሕይወት ሊኖረን እንደሚችል ይነግረናል።
የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን በሮሜ 6፡14 ላይ እንመልከት። "ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና" እንዲሁም ከጭንቀት ነፃ የሆነ ሕይወት እና የደስታን ሕይወት እንድንኖር ታዘናል። ፊልጵስዩስ 4፡4,6 እንዲህ ይላል "ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ.... በአንዳች አትጨነቁ" ።
እግዚአብሔር እንድናደርጋቸው የሚያዘን ነገሮች ሁሉ እርሱ አስችሎን ማድረግ የምንችላቸውን ብቻ መሆኑን አስታውሱ።
ስለዚህ ትእዛዞቹ የተባልነው ለመፈጸም የሚያስችል ጸጋ እንደምናገኝ የሚያሳይ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ነው! ስለዚህ ከላይ ያሉት ትዕዛዛት ቀጣይነት ያለው ደስታንና ከጭንቀት ነፃ የሆነ ሕይወትን እግዚአብሔር መኖር እንደሚያስችለን የሚያሳዩ ናቸው።
ይህን የመሳሰሉ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ የተከበሩ ቃል ኪዳኖች አሉ። ከላይ የተጥቀሱት እንኳን ብቻ ወንጌል በእርግጥ የምሥራች/ መልካም ዜና መሆኑን ለማሳየት በቂ ናቸው።
የዚህ መጽሐፍ አላማም በሕይወታችሁ መልካም መሠረትን በመጣል የእግዚአብሔር አላማ በሕይወታችሁ እንዲፈጽም ነው። እያነበባችሁ መንፈስ ቅዱስ ለልባችሁ እንዲናገር ፍቀዱ።
ወደ በጎቹ በረት (ወደ እሱ መንግሥት) ትክክለኛ መግቢያው በሩ ሲሆን ነገር ግን አንዳንዶች በአጥር ላይ ዘለው ለመግባት እንደሚሞክሩ እየሱስ ተናገረ (ዮሃንስ 10፡1) ።
እግዚአብሄር የሰው ልጅ እንዲድን ያዘጋጀለት መንገድ ንሰሃ በመግባት እና በጌታ እየሱስ ክርስቶስ በማመን ነው። ያለው መንገድ ይህ ብቻ ነው። እግዚአብሔር በሌላ መንገድ ለመዝለል የሚሞክረውን ሰው በፍፁም አይቀበልም።
የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት የመጣው መጥምቁ ዮሃንስ ስለ ንሰሃ ሰበኮ ነበር። የእስራኤል ህዝብ እየሱስን እንደ ግል አዳኛቸው ለመቀበል የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነበር። ለእኛም ቢሆን ዛሬ ምንም አይነት ሌላ መንገድ የለም።
ንሰሃ እና እምነት
አብዛኛዎቹ የዛሬ አማኞች የዱሮዎቹን ክርስቲያኖች ያህል የጠለቀ እውቀት ወይም ሃይል ያላቸው አይመስልም። በተጨማሪም እንደጥንቶቹ አማኞች ሙሉ በሙሉ ለእምነታቸው የተሰጡ አይደሉም።
ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው ብላችሁ ታስባላችሁ?
የመጀመሪያው ምክንያት በሚገባ መልኩ ንሰሃ ስላልገቡ ነው።
በክርስቶስ ማመናቸው መልካም ነው። ሆኖም መጀመሪያ ላይ ንስሓ ሳይገቡ ነው ያመኑት። ስለዚህ ለውጣቸው ጥልቀት ያለው አይደለም።
የሚከተሉትን በጣም ታዋቂ መንፈሳዊ መዝሙር ቃላት ተመልከቱ።
"ያ ክፉ ወንጀለኛ በእውነት ያመነው፣
ባመነበት ቅፅበት ክርስቶስ ይቅር አለው"
ይህ እውነት ነው? ክፉ ወንጀለኛ ከልቡ ስላመነ ይቅርታን ያገኛል?
መጀመሪያ ንሰሃ መግባት የለበትም?
እውነተኛ እምነት ንሰሃን ይፈልጋል ልትሉ ትችላላችሁ። ነገር ግን ይሄ ለክፉ ወንጀለኛ ሰው ስለ ንሰሃ በአግባቡ ካልተነገረው በቀር በክርስቶስ ስለአመነ ብቻ እንደገና የተወለደ ሊመስለው ይችላል። ስለዚህ ተታሎ ሊሄድ ይችላል። እየሱስ እራሱ የሰበከው መልክት እንዲህ የሚል ነበር። "ንስሓ ግቡ በወንጌልም እመኑ" (ማርቆስ 1፡15) ። እየሱስም ሃዋርያቶቹን ይህንኑ በተመሳሳይ እንዲሰብኩ ነበር ያዘዛቸው። (ሉቃስ 24፡47) እነርሱም እንዳዘዛቸው አደረጉ። (ሐዋርያት ሥራ 20፡21)
የእግዚአብሔር ቃል በዚህ ላይ በጣም ግልፅ የሆነ ሃሳብ ያስቀምጣል። በእውነት ለመቀየር ንሰሃ መግባት እና እምነት ሊነጣጠሉ አይችሉም። እግዚአብሔር እነዚህን ሁለት ነገሮች አጣምሯቸዋል። ስለዚህም እግዚአብሔር ያጣመረውን ማንም ሊለያየው አይችልም። ንሰሃ መግባት እና እምነት የመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ሕይወት መሠረቶች ናቸው (ዕብራዊያን 6፡1)። በትክክለኛ ንሰሃ ካልገባችሁ የክርስትና መሠረታችሁ ላይ ችግር አለ ማለት ነው። ከዚህም የተነሳ ጠቅላላው የክርስትና ሕይወታችሁ የጠና አይሆንም።
መፅሃፍ ቅዱስ ሲናገር የጥበብ መጀመሪያ (የክርስትና ሀ ሁ) እግዚአብሔርን መፍራት ነው (ምሳሌ 9፡10) በእውነት ጌታን የምንፈራ ከሆነ "ከሃጢያት እንሸሻለን (ምሳሌ 3፡7)
ስለዚህ ንሰሃ ያልገቡት እና ከሃጢያት ያልሸሹት ለክርስትና ሕይወታቸው የመጀመሪያውን (ሀ ሁ) እንኳን አልተማሩም ማለት ነው።
ሐሰት እና እውነተኛ ንስሐ
ሰይጣን የሐሰት ንስሐን በማቅረብ ሰዎችን ስለሚያታልል ንሰሃ ገብታችሁ ከሆነ የእውነተኛ ንሰሃ መግባታችሁን ማረጋገጥ አለባችሁ። ሰይጣን አብዛኛው ሰው በአንድ ትዕዛዝ እንደሚኖሩ ያውቃል። ይህ ትእዛዝ "ስታጠፉ እንዳትያዙ!" ይላል። ስለዚህ ሃጢያት ሲሠሩ እንዳይያዙ የተለያዩ ዘዴዎችን እና መንገዶችን ያስተምራቸዋል።
ሌባ እንኳን ሲያዝ በሠራው ያዝናል ነገር ግን ይህ ንሰሃ መግባት አይደለም።
በመጽሐፍ ቅዱስም ውስጥ የሐሰት ንስሓዎችን እናያለን።
ንጉስ ሳኦል እግዚአብሔርን ባላከበረበት ወቅት ለሳሙኤል ሃጢያቱን ተናገረ ነገር ግን ህዝቡ እንዲያውቅበት አልፈለገም ነበር። የሰዎችን ክብር ነው የፈለገው። ከዚህም የተነሳ ከልቡ ንሰሃ አልገባም ይቅርታን የጠየቀው በሰዎች ስለተያዘ ብቻ ነበር። (1ኛ ሳሙኤል 15፡24-30) በንጉሥ ሳኦል እና በንጉሥ ዳዊት መሀከል የነበረው ልዩነት ይህ ነበር። ንጉሥ ዳዊት ከልቡ ሃጢያቱን የሚያምን እና የሚናዘዝ ነበር (መዝሙር 51) ።
ንጉስ አክአብ ከሳኦል ጋር ይመሳሰል ነበር። ኤልሳ ንጉስ አክአብን እግዚአብሔር ሊፈርድብህ ነው ብሎ ሲያስጠነቅቀው ንጉሡ ከጆንያ የተሠራ ልብስ ለብሶ ስለልጆቹ በጣም አዘነ (መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 21፡27-29) ። ነገር ግን ከልቡ ንሰሃ አልገባም። የእግዚአብሔርን ውሳኔ ብቻ ነበር የፈራው።
የአስቆሮቱ ይሁዳ ሁኔታ ግልጽ የሆነ የሃሰት ንሰሐን ያሳያል። እየሱስ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ባየ ጊዜ መጥፎ ስሜት ሲሰማው "ሃጢያተኛ ነኝ" አለ (ማቴዎስ 27፡3-5) ። ይህን ቃሉን ግን የሰጠው ዛሬ አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ለቄሶች ነበር! ምንም እንኳን በአድራጎቱ ቢያዝንም ንሰሃ ግን አልገባም። በእውነት ንሰሃ ገብቶ ቢሆን ኖሮ በተሰበረ ልብ ጌታን ይቅርታ ይጠይቅ ነበር። ነገር ግን ይህን አላደረገም።
ንስሐ መግባት ማለት ምን እንዳልሆነ ከነዚህ ምሳሌዎ ብዙ ምማር እንችላለን። እውነተኛ ንሰሃ ከጣኦቶች ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። (1ኛ ተሰሎንቄ 1፡9) ። ጣኦታት ከእንጨት እና ከድንጋይ ተሠርተው በአረማዊያን ማምለኪያ ቦታ የሚገኙ ብቻ አይደሉም። የነዚህኑ ያህል አደገኛ የሆኑ እና የማያስከፉ ሰዎች የሚያመልኳቸውንም ይጨምራሉ። እነዚህም የመደሰት፣ የምቾት፣ የገንዘብ፣ ታዋቂ መሆንን የመሻት፣ "እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን" የማለት እና የመሳሰሉትን ጣኦቶች ይጨመራል።
ሁላችንም እነዚህን ጣኦቶች ለብዙ አመታት ስናመልካቸው ቆይተናል። ንሰሃ መግባት ማለትም እነዚህን ጣኦቶች ማምለካችንን ትተን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ማለት ነው።
እውነተኛ ንሰሃ አጠቃላይ ስብዕናችንን ያካትታል። ይህም ማለት አዕምሯችንን፣ ስሜታችንን እና ፍላጎታችንን ማለት ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ ንሰሃ መግባት ማለት በአዕምሯችን ስለ ሃጢያት እና ሰለ ዓለም ያለንን አመለካከት መቀየር ማለት ነው። ሃጢያታችን ከእግዚአብሔር እንደለየን እንገነዘባለን። የዚህ ዓለም የአኗኗር ዘይቤ ከእግዚአብሔር ሃሳብ የተቃረነ እንደሆነም እንመለከታለን። ስለዚህም እግዚአብሔርን ከማያስከብር ሕይወት መለየትን እንሻለን።
በሁለተኛ ደረጃ ንሰሃ መግባት ስሜቶቻችንን ያካትታል። ስለ ነበረን አኗኗር እንጸጸታለን (2ኛ ቆሮንቶስ 7፡10) ። ስለ አለፈው መጥፎ ድርጊቶቻችን ራሳችንን እንጠላለን። ከዚህም በላይ ሌሎች የማያዩት እኛ ግን በውስጣችን የምናየው መጥፎ ክፋት ያስጸይፈናል (ህዝቅኤል 36፡31) ።
በአኗኗራችን እግዚአብሔርን በጣም ስለጎዳነው በመጸጸት እናለቅሳለን። በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናየው በዙ ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች ሃጢያታቸውን በተረዱ ጊዜ እንዲህ ነበር ይደረጉት።
ዳዊት (መዝሙር 51), እዮብ (እዮብ 42፡6) እና ጴጥሮስ (ማቴዎስ 26፡75) እነዚህ ሰዎች ሃጢያታቸውን በተረዱ ጊዜ ተጸጽተው አልቀሰው ንሰሃ ገቡ።
እየሱስም እና ሃዋርያት ስለ ሃጢያታችን እንድናለቅስ እና ከልብ እንድናዝን ያበረታቱናል። (ማቴዎስ 5፡4, ያዕቆብ 4፡9) ይህ ወደ እግዚአብሔር የሚመልሰን መንገድ ነው።
በመጨረሻም ንሰሃ መግባት የእኛን ፍላጎት ያካትታል። ግትር ማንነታችንን ማለትም "ሁል ቢዜ የራሳችንን መንገድ ብቻ መፈለግን" አስወግደን እየሱስ ክርስቶስን የሕይወታችን ጌታ ማረግ ይኖርብናል። ይህ ማለት ከአሁን በኋላ እግዚአብሔር እንድናረግ የሚፈልገውን ሁሉ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ዋጋ ለመክፈል የሚያዋርድ ቢመስለንም ለመዋረድ ፈቃደኞች ነን ማለት ነው።
አባካኙ ልጅ ወደአባቱ ቤት በተሰበረ ልብ እና በተሰበረ ማንነት በመመለስ አባቱ የሚለውን ሁሉ ለማድረግ ወሰነ። ይህ እውነተኛ ንሰሃ ነው (ሉቃስ 15፡11-24)።
እያንዳንዷን የሠራናትን ሃጢያት ለእግዚአብሔር መናገር የለብንም። በእያንዳንዱ ሁኔታ ውስጥ የሠራነውን ሃጢያት በሙሉ ማስታወስም አይቻልም። አባካኙ ልጅ እንደዚህ አላደረገም። ያደረገው ነገር "አባት ሆይ በድያለሁ" አለ። እኛም ማድረግ ያለብን እንደዚሁ ነው።
የአስቆሮቱ ይሁዳም "በድያለሁ" ብሎ ነበር። ቢሆንም በአስቆሮቱ ይሁዳ ጸጸት እና በአባካኙ ልጅ ጸጸት እጅግ በጣም የተለያዩ ናቸው። እግዚአብሔር የምንናገረውን ቃል ብቻ አይደለም የሚያዳምጠው። ከምንናገረው ቃል ጀርባ ያለውንም መንፈስ ተመልክቶ የወስናል።
የ ንስሓ ፍሬዎች
መጥምቁ ዮሃንስ ፈሪሳዊያንን የንስሓን ውጤት ፍሬ እንዲያሳዩ ነግሮአቸው ነበር። (ማቴዎስ 3፡8) ። ከልባችን ንስሓ ከገባን ጠቅላላ አኗኗራችን ይቀየራል። ንስሓ ከገባን በኋላ በመጀመሪያ ማድረግ ያለብን ነገር በሕይወታችን የሠራናቸውን ስህተቶች/ጉድለቶች ማስተካከል ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የዘኪዮስን ታሪክ ስናነብ እየሱስ ወደ ቤቱ በገባ ሰዓት ሃጢያቱን ይናዘዝ ጀመር (ሉቃስ 19፡1-10) ። ዘኪዮስ ገንዘብን የሚወድ ሰው ቢሆንም ንሰሓ መግባት ምን እንደሆነ ገብቶት ነበር። የእየሱስ ደቀ መዛሙር መሆን ከፈለገ በሕይወት ዘመኑ ለሠራቸው ክፉ ሥራዎች ማስተካከያ ማድረግ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር።
ያም ማለት ዛኪዮስ ብዙ ሰዎችን ስላጭበረበረ ከፍ ያለ የገንዘብ ኪሳራ ሊያስከትልበት ነው ማለት ነው። ቢሆንም ከልቡ ንሰሃ ለመግባት ስለወሰነ ካለው ገንዘብ ግማሹን ለድሆች እደሚሰጥ እና ላጭበረበራቸው ደግሞ የወሰደባቸውን አራት እጥፍ እንደሚከፍል ለጌታ ነገረ።
ዘኪዮስ ያጎደለውን እንደሚያስተካክል ሲናገር ነው እየሱስ "ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል" ያለው። ያጠፋነውን/ያጎደልነውን ለማስተካከል ፈቃደኛ መሆን የእውነተኛ ንሰሃ ማስረጃ ነው (ሉቃስ 19፡1-10) ።
በክርስቶስ ትምህርት ላይ ጠቢቡ ሰው ቤቱን ሲሠራ ከአሸዋው ሥር አጥልቆ ከቆፈረ በኋላ በአለት ላይ መሠረቱን ይጥላል (ሉቃስ 6፡48) ። ሞኝ ሰውም በዚያው አከባቢ ቤቱን ይገነባል። ነገር ግን አጥልቆ ሳይቆፍር የቤቱን መሠረት በአሸዋ ላይያደርጋል።
ይህ ምሳሌ ከእውነተኛ እና ከሃሰተኛ ንሰሃ ጋር ማመሳሰል እንችላለን። ጥልቅ የሆነ ንሰሃ መግባት የምንችለው በሕይወታችን ላጠፋናቸው/ላጎደልናቸው ነገሮች ዋጋ ስንከፍል ነው።
መጀመሪያ ላይ ወደ ክርስቶስ ስንመጣ ጊዜ ወስደን ያልተቀየሩ ወይም ያልተለወጡ ማንነቶቻችንን እንዲለወጡ ምድረግ ያስፈልጋል። እዚህ ጋር የምናደርገው ለውጥ ላይ ላዩን ከሆነ እና ነገሮችን የምንሸፋፍን ከሆነ መሠረታችን ደካማ ከመሆኑ የተነሳ ቤታችን አንድ ቀን ይፈርሳል።
ማካካሻ ምንን ያካትታል
ካሳ ምን ያካትታል?
ይህ ማለት ታክሳችሁ ላይ መንግሥትን አጭበርብራችሁ ከሆነ የተጭበረበውን ገንዘብ መክፈል ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ለተጭበረበርው ክፍል በቀታ መክፈል ላይቻል ይቻላል። ነገር ግን ፍላጎት ካለ የሚፈለገውን ለማድረግ ምን ጊዜም መንገድ አለ። ይህ የሚሆነው ግን እግዚአብሔርን መታዘዝ ስንፈልግ ነው! ለምሳሌ መንግሥት የሚሽጣቸውን እንደ ቴምብሮች የመሳሰሉትን መግዛት እና ቀዶ መጣል። ይህን በማደረግ ገንዘቡ ወደ መንግሥት እጅ መግባቱን እናረጋግጣለን። ሰዎችንም ካጭበረበርን ገንዘባቸውን መልሰን ይቅርታ መጠየቅ አለብን። ይህን ስታደርጉ የምታደርጉበትን ምክንያት ነገሯቸው! ለብቻችሁ ይህን ማድረግ ካስቸገራችሁ ከሌላ ወንድም ጋር መሄድ ትችላላችሁ።
እዳችሁን በአንድ ጊዜ መክፈል ካልቻላችሁ አትጨነቁ ከፍላችሁ እስክትጨርሱ ድረስ በየጊዜው የምትችሉትን ያህል መክፈል ትችላላችሁ ። ነገር ግን ትንሽም ቢሆን መክፈል መጀመር አለባችሁ። እግዚአብሔር ዘኪዮስን የተቀበለው ዕዳውን ለመክፈል በወሰነበት ቀን ነው እንጂ ዕዳውን ከፍሎ በጨረሰበት ቀን አይደለም!
ያጭበረበራችሁት ሰው ለመክፈል አድራሻውን የማታውቁት ከሆነ የገንዘብ ሁሉ ባለቤት ለሆነው ለእግዚአብሔር መክፈል ትችላላችሁ። ይህ እግዚአብሔር ለእስራኤላዊያን የሰጠው ሕግ ነበር። (ዘኹልቁ 5፡6-8)
ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ከእኛ መሆን የለበትም። በዚህ ሁኔታ የመጣውን ገንዘብ እግዚአብሔር አይባርክልንም።
የጎዳነው ሰው ካለ፣ ምንም እንኳ ገንዘብ የሌለበት ሁኔታ ቢሆንም ከልብ ይቅርታ መጠየቅ አለብን።
የማውቃቸው ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ። እኝህ ወንድማማቾች ለብዙ ወራት ገንዘባቸውን አጠራቅመው ከዚህ በፊት ላጭበረበሩት የታክስ አና የጎምሩክ ቀረጥ መልሰው ከፈሉ። እግዚአብሔርም በባንክ በሚጠራቀም ገንዘብ ላይ ባረካቸው!
ሌሎችም የማውቃቸው ሰዎች ዱሮ በአውቶብስ እና በባቡር ሳይከፍሉ ይጓዙ በነበርበትን ጊዜ መክፈል የነበረባቸውን በጥንቃቄ ተምነው እዳቸውን በሙሉ መልሰው ከፍለዋል። በትንሹ የታመኑ ሰዎች ለእግዚአብሔር ታላቅ ነገርን ያደርጋሉ።
አንዳንድ ወደ ተመረቁበት ዩኒቨርሲቲ ሄደው የዲግሪ/ሰርቲፊኬት ፈተናዎቻቸው ላይ እንዳጭበረበሩ ለዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች የተናገሩ አውቃለሁ። ንጹህ ህሊና እንዲኖራቸው አስፈላጊም ከሆነ ድግሪያቸውንም ጭምር ለመመለስ ቆርጠው ተነስተው ነበር። እግዚአብሔርም ለእንደዚህ ያሉ አማኞች ባለስልጣኖችን በማራራት ይቅርታ እንዲያደርጉላቸው ያደርጋል።
ነገር ግን ሁል ጊዜ እንደዚህ ላይሠራ ይችላል። እንዲህ ብታደርጉ እግዚአብሔር የዩኒቨርሲቲው ድግሪያችሁን ሊያስወስድ ይችላል። ይህም ቢሆን የእግዚአብሔር ላናንተ ያለው ትክክለኛ ፍላጎት ይሆናል።
አንድ የማውቀው ወንድም ከብዙ አመት በፊት ከሰው ላይ ቴምብር ሰርቆ ነበር። ይህ ወንድም ስላደረገው ድርጊት ለሰረቀው ሰው የይቅርታ ደብዳቤ ላከለት። ትንሽም ሆነ ትልቅ ሌብነት ሌብነት ነው። እምነታችን የሚፈተነው በጥቃቅን ነገሮችም ነው።
ከዚህ በፊት የሠራችኋቸው ስህተቶች በማስታወስ ህሊናችሁን እንድታስጨንቁ ፈልጌ አይደለም። እንደዛ ማድረግ የለባችሁም። እግዚአብሔር ማስተካከል ያለባችሁን ያስታውሳችኋል። እግዚአብሔር የሚያስታውሳችሁ ላይ ብቻ ነው ማተኮር ያለባችሁ።
ነገሮች ይወሳሰቡ እና በአንዳንድ ነገሮች ላይ ምንም ማድረግ የማትችሉበት ጊዜ ይኖራል። በዚህ ጊዜ ማድረግ የምትችሉት በሠራችሁት ሥራ እንዳዘናችሁ ለእግዚአብሔር ገልጻችሁ ከርሱ ምህረት መጠየቅ ነው።
በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን አንዳንድ ነገሮችን ማስተካከል ስላልቻልን ሰይጣን የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰጠን እና ለዘለዓለም እንዲወቅሰን ዕድል ፈንታ ልንሰጠው አይገባም። እግዚአብሔር ሁኔታችንን በሙሉ ስለሚያውቅ ሊያስጨንቀን አይወድም። ፈቃደኛ አዕምሮ ካላችሁ አነሰም በዛም እግዚአብሔር መሥራት የምንችሉትን ይቀበላል። (2ኛ ቆሮንጦስ 8፡12)
ስለ ምሃሪነቱ እግዚአብሔር ይመስገን!
እግዚአብሔር የሚያከብሩትን ያከብራል (1ኛ ሳሙኤል 2፡30) ። እግዚአብሔርን የምናከብርበት አንደኛው መንገድ በትንንሽ ነገሮችም ለእርሱ ታማኝ ስንሆን ነው። ያጠፋነውን/ያጎደልነውን ካላስተካከልን ይህ ሁኔታ ሕይወታችንን ሙሉ ወደ ኋዋላ በሚጎትተን ሰንሰለት ይሆናል ። እግዚአብሔር ንጹህ ህሊናን ከገንዘብ፣ ከክብር፣ከድግሪያችን እና ከሥራችንም በላይ አስበልጠን ማያታችንን ይፈትናል።
አብዛኛዎቻችን ይህን ፈተና እንወድቃለን። ነገር ግን እግዚአብሔር ይመስገን በየትውልዱ እግዚአብሔርን ከማንኛውም ምድራዊ ነገር በላይ የሚወዱ ቀሪዎች አሉ።
ሌሎችን ይቅርታ ማለት
ንሰሃ መግባት የጎዱንን ሰዎች ይቅር ማለትን ይጨምራል። እየሱስ ሲናገር "ለሰዎች ግን ሃጢያታቸውን ይቅር ባትሉ÷ አባታችሁም ሃጢያታችሁን ይቅር አይላችሁም" (ማቴዎስ 6፡15) አለ። በመቀጠልም እየሱስ ሌሎችን ከአንገት በላይ ሳይሆን ከልባችን ይቅር ማለት እንዳለብን ተናገረ (ማቴዎስ 18፡35) ። ሌሎችን በሙሉ ልባችን እና ባጠቃላይ ይቅር ካላልናቸው በእግዚአብሔር ይቅር መባል የማይቻል ነው።
ምናልባት ሌሎች በእኛ ላይ የሠሩትን ነገሮች መርሳት አንችል ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ ክፉ ሥራዎች ወደ አእምሮአችን እንዳይመጡ መከላከል እንችላለን።
ምናልባት በጣም የበደላችሁን ሰው ከልብ ይቅር ለማለት ሊያስቸግራችሁ ይችላል። እንዲህ ሲሆን እግዚአብሔር ይቅር ማለት እንዲያስችላችሁ ጠይቁ። እግዚአብሔር ይቅር የምትሉበትን ኃይል እና ጸጋ እንደሚሰጣችሁ ፈቃዱ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሃጢያቶቻችንን እግዚአብሔር ይቅር እንዳለን ስናስብ እኛም እንደዚሁ ሌሎችን ይቅር ማለት ከባድ መሆን የለበትም። ሌሎችን ይቅር ሳንል ስንቀር ነው ሰይጣን በእኛ ላይ ኃይል የሚኖረው። ጳውሎስ ሲናገር "ይቅር ተባባሉ" "በሰይጣን እንዳንታለል" (2ኛ ቆሮንጦስ 2፡10-11) ።
ስለሰይጣን ያለን የተለወጠ አመለካከት
አንድ መስተካከል ያለበት ነገር ከሠይጣን እና ከክፉ መናፍሳት ጋር ያለው ግንኙነት ነው።
በኮከብ ትንበያ፣ በጣኦት አምልኮ፣ በእጅ መዳፍ ትንበያ፣ በአስማትና በመሳሰሉት ወይም በሮክ ሙዚቃ እና በጎጂ ዕፅዋት የምትደሰቱ ከሆነ ምንም እንኳን አንዳንዱን ሳታውቁ የጀመራችሁት ቢሆንም እነዚህን ነገሮች በመተው ከሠይጣን ጋር ያላችሁን ግንኙነት ማቆም አለባችሁ።
የመጀመሪያው ማድረግ ያለባችሁ እነዚህን ጣኦት የሆኑትን ነገሮች ማውደም ነው (መሸጥ አይደለም ነገር ግን ማውደም ነው) (ሐዋርያት ሥራ 19፡19 ተመልከቱ) ። ከዚያም እንደዚህ ብላችሁ ጸልዩ፣
"ጌታ እየሱስ ሆይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከሰይጣን ጋር ያደረኩትን ማንኛውንም ግንኙነት እተዋለው"።
ከዚያም በቀጥታ ለሠይጣን እንዲህ በሉት፣
"ሠይጣን በጌታዬ እና በአዳኜ እየሱስ ክርስቶስ ስም እቃወመሃለው። ከአሁን በኋላ የእየሱስ ክርስቶስ ስለሆንኩኝ ልትነካኝ አትችልም" ።
ያዕቆብ 4፡7 እንዲህ ይላል።
"እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል"
ስለዚህ ሰይጣን ከእናንተ ጋር ከአሁን በኋላ ምንም ህብረት አይኖረውም።
ከጌታ ጋር የምንቀጥል ከሆነ በተለያየ የሕይወታችን አቅጣጫ ብርሃን ያበራልናል። ይህ ብርሃን የሚበራልን በአለባበሳችን ወይንም በአነጋገራችን ወይም ቁጡ በሆነ ድምፃችን ወይም በምናነባቸው መጥፎ የመጽሓፍ አይነቶች ወዘተ ይሆናል። ስለዚህ ንስሓ መግባት እና ማስተካከል ያለብን ሁኔታዎችን በየጊዜው እየተገለጹልን ከነዚህ ንጻ እንሆናለን።
ቀኑን ሙሉ በማይቋረጥ ንሰሃ ውስጥ መጓዝ አለብን።
ንሰሃ የመጀመሪያው የክርስቲያን ሕይወት መሠረት ነው። ሁለተኛው ደግሞ እምነት ነው።
በእግዚአብሔር ማመን ማለት በርሱ ምተማመን እና ስሜታችን ወይም ሌሎች ሰዎች የሚሉትን ትተን ቃሉ የሚለውን ማመን ነው። ያን ያህል ቀላል ነው።
እግዚአብሔርን በተመለከተ ሶስት እውነታዎች።
1. ገደብ በሌለው ፍቅር ይወደናል።
2. እርሱ ጥበበኛ ነው።
3. ኃያል ነው።
እነዚህን እውነታዎች ማመን ይከብዳል? አይከብድም። ስለዚህ እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን ማመን መክበድ የለበትም።
ሄዋን የሰይጣንን ድምጽ በኤደን ገነት በሰማች ጊዜ የእምነቷ ውድቀት ነበር። የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ለእርሷ ለመልካም እንደነበረ አላመነችም ነበር። እግዚአብሔር ለእሷ ያለውን ፍፁም ፍቅር ስላላመነች ለእግዚብሔር አልታዘዝ አለች።
የእግዚአብሔርን ስጦታዎች የመቀበል እምነት
እግዚአብሔር ብዙ የሚሰጠን አስደናቂ ነገሮች አሉት። ስጦታዎች በሙሉ የፀጋ ስጦታዎች ናቸው። ሆኖም እንዚህን ስጦታዎች የምንቀበልበት እምነት ያስፈልገናል።
መጽሓፍ ቅዱስ "ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና" (ኤፌሶን 2፡8) ይላል። ፀጋ ከመንግሥተ ሰማያት በረከቶችን ወደ እኛ የሚያፈስበት የእግዚአብሔር እጅ ነው። እምነት ደግሞ የእኛ እጅ ወደ ላይ ተዘርግቶ በረከቶቹን ከእግዚአብሔር እጅ የምንቀበልበት ነው።
እግዚአብሔር በመጀመሪያ ላይ ስለሃጢያቶቻችን ይቅርታን ይሰጠናል። ንሰሃ ከገባን ማድረግ ያለብን እጃችንን ወደ እግዞአብሔር ዘርግተን ይህን የይቅርታ ስጦታችንን መቀበል ነው። ስጦታዎቹን ለማግኘት መሥራት ወይም መክፈል የለብንም። ቀራኒዮ ላይ ተከፍሎል። አሁን ማለት ያለብን "አባት ሆይ አመሰግንሃለው" ብለን መቀበል ነው። እምነት ማለት ይህ ነው።
እግዚአብሔር የሰጠንን የማንቀበል ከሆነ በእርግጥ እርሱን እንደ መስደብ ነው። ሥጦታውን ናቅነው ማለት ነው። ምናልባትም እግዚአብሔር የሚቀልድብን ይመስለን ይሆናል። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ህፃናትን እጃቸው ላይ ስጦታ በማሳየት እና ልጆቹ ስጦታውን ሊወስዱ ሲቅርቡ በማሸሽ እንደሚቀልዱባቸው ማለት ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ እነዚህ ሰዎች ክፉ አይደለም። አፍቃሪ አባት ነው። ሁልጊዜም መልካም ስጦታዎችን ሊሰጠን ይወዳል። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን "ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም" (ዕብራዊያን 11፡6) የሚለው።
በእግዚአብሔር ስንተማመን እግዚአብሔር ላደረግናቸው ሃጢያቶች ይቅር ይለናል። በተጨማሪም ከሃጢያት ኃይል ነፃ ያወጣናል።
እምነትን እንዴት እናገኛለን? እምነት የሚገኝበት አንድ ብቸኛ መንገድ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡ "እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው "(ሮሜ 10፡17) ። ይህም ማለት እግዚአብሔር በቃሉ እንዲናገረን ስንፈቅድ እምነትን እናገኛለን። የእኛም እምነት ሊጨምር የሚችለው በዚሁ መንገድ ነው።
ስለ ሃጥአያቶቻችን ክርስቶስ እንደሞተ እና ከዚያም እንደተነሳ እንዲሁም ንስሓ ገብተን በእርሱ ካመንን ወዲያወኑ ሙሉ በሙሉ ለሃጢያቶቻችን ይቅርታን እንደምናገኘ የምናውቀው በእግዚአብሐር ቃል ነው። መንፈስ ቅዱስም ይህ እውነት እንደሆነ በልባችን ይመሰክርልናል። ከቃሉ እና ከመንፈስ ቅዱስ ባገኘነው ሁለት ምስክርነት ይቅር እንደተባልን እና የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆንን እርግጠኛ እንሆናለን።
የእምነት ማረጋገጫ
ልጆቹ ስለመሆናችን ትክክለኛ ማረጋገጫ በልባችን እንዲኖረን እግዚአብሔር ይፈልጋል። ይህንን እውነት እንድንጠራጠር እግዚአብሔር በፍጹም አይፈልግም።
ሁልጊዜ በጥርጣሬ እንድንኖር ሰይጣን ተግቶ ይሠራል። እግዚአብሔር ብዙ የማረጋገጫ ቃል ኪዶኖችን ስለሰጠን እኛ ግን በፍጹም ጥርጣሬ ውስጥ መግባት የለብንም።
እየሱስ የተናገረውን ቃል ኪዳን እንመልከት፤
"አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም......እውነት እውነት እላችኋለው በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው" (ዮሃንስ 6፡37,47) ።
"ብዙዎች እንደተቀበሉት (ጌታ እየሱስ ክርስቶስን) ለእርሱ የእግዚአብሄር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣን ሰጣቸው"(ዮሃንስ 1፡12)
ጌታ እንዲህ ይላል፣
"ዓመፃቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም" (ዕብራዊያን 8፡12)። በእግዚአብሔር ማመንን ወንዝ ለመሻገር በጠንካራ ድልድይ ላይ ካለመጠራጠር እግራችንን ከማሳረፍ ጋር ማመሳሰል ይቻላል። ድልድዩ ጠንካራ እስከሆነ ድረስ እግሮቻችን ደካማ ቢሆኑም ምንም አይደለም። እንግዲህ ጠንካራ እምነት ማለት ምንድን ነው? ይህ ማለት በጠንካራ በሆነው እግዚአብሔርን እና ቃል ኪዳኖቹን ማመን ነው።
ስሜታችን ብዙውን ጊዜ በጣም አታላይ ነው። ስለዚህ ስሜታችንን በጭራሽ ማመን የለብንም። እውነት ፣ እምነት እና ስሜት ስለሚባሉ ሦስት ሰዎች አንድ ምሳሌ አለ። እነዚህ ሰዎች በጠባብ ግድግዳ ላይ ተከታለው እውነት ከፊት ለፊት ቀጥሎ እምነት መጨረሻ ላይ ስሜት ሆነው ይጓዙ ነበር። እምነት ዐይኖቹን ፊቱ ባለው እውነት ላይ እስካደረገ ድረስ ሁሉም መልካም ነበር። ሰሜት ከኋላ በትክክል ይከተል ነበር። ነገር ግን እምነት ዞር ብሎ ስሜት እንዴት እንደሆነ ለማየት ሲሞክር ተሰናክሎ ወደቀ እና ሞተ። እውነት ግን ምንም ሳይረበሽ ጉዞውን ቀጠለ!
በዚህ ምሳሌ ውስጥ ያለው ትምህርት ግልፅ ነው። የእግዚአብሔር ቃል የማይለወጡ እውነቶችን ያካተተ ነው። እምነታችን በእግዚአብሔር ቃል ላይ የቆመ ከሆነ ምንም አይነት ዉድቀት አይደርስብንም። ከዚህም የተነሳ ስሜታችን እኛን ይከተላል እንጂ እኛ ስሜታችንን አንከተልም።
ነገር ግን ስሜታችንን ማየት ወይም ማዳመጥን ስንጀምር በቀላሉ ወደ ጭንቀት፣ ወደ ተስፋ መቁረጥ እና ወደ ራስን ማውገዝ ውስጥ እንገባለን።
የእምነ ታችንን ስለመግለጽ
መጽሐፍ ቅዱስ እምነታችንን ማሳወቅ እንዳለብን ይናገራል።
"እየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህ፤ ሰው በልቡ አምኖ ይፀድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና" ። (ሮሜ 10፡9-10) ።
የአንደበታችን ምስክርነት በጣም አስፈላጊ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ማወጅ ማለት እግዚአብሔር በቃሉ የተናገረውን ደግመን ማወጅ ማለት ነው። ይህን ማድረግ እግዚአብሔር ለሰጠን ቃል ኪዳኖች አሜን (እንደተባለው ይሁን) እንደማለት ስለሆነ ከባድ መሆን የለበትም።
እምነት የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው በዘፍጥረት ምዕራፍ 15 ውስጥ ነው። እዚህ ምዕራፍ ውስጥ እግዚአብሔር አብረሃም ልጅ በሌለው ሰዓት እንደ ሰማይ ክዋክብት የብዙ ልጆች አባት እንደሚሆን የተናገረበትን ቦታ እናያለን። አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ይላል (ቁጥር 6) ። የዕብራይስጡ ቃል "እምነት" የሚለውን "አማን" ይለዋል። "አሜን" የሚለው ቃልም የመጣው "አማን" ከሚለው ቃል ነው። ትርጉሙም "እንደተባለው ይሁን" ማለት ነው። ስለዚህ አብርሃምም ያደረገው ነገር ለእግዚአብሔር ቃልኪዳን "አሜን" ማለት ነበር።
ትክክለኛ እምነት ይኸው ነው - እግዚአብሔርን አሜን ማለት።
በኋላ እንደምናየው አብራም ራሱን እግዚኦብሔር በሰጠው አዲስ ስም - አብርሃም ብሎ መጥራት ጀመረ። አብራሃም ማለት የብዙዎች አባት ማለት ነው። ሳራህ ሚስቱም እስከዚያ ድረስ ልጅ አልነበራትም። ይሄ ሁነታ ግን አብርሃም ላይ ምንም ለውጥ አላመጣም። እግዚአብሔር የተናገረውን ስላመነ ራሱን የብዙዎች አባት እያለ ነበር የሚጠራው። (ዘፍጥረት 17፡5) ። ምንም እንኳን የተባለው ተከናውኖ ሳናይ እግዚአብሔር ያለውን መናገር ለእምነት ምስክረነት መስጠት ነው።
እግዚአብሔር አድርጉ የሚለን ይህንን ነው - ምንም እንኳን ውጠቶቹን ባናይም በቃሉ የተናገራቸውን ነገሮች ደግመን መናገር ።
የእግዚአብሔርን ቃል ስንናገር በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት እንገልፃለን ከዚያም እግዚአብሔር በእኛ ቦታ መሥራት ይጀምራል።
ሰይጣንን የምናሸንፈው ስንመሰክር ነው። "ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት" (ራዕይ 12፡11) ። ሰይጣን እንደ ከሳሽነቱ ሁል ጊዜ የደህንነታችንን ማረጋገጫ እና በእግዚአብሔር ፊት በድፍረት እንዳንቆም ሊያሰናክለን ይጥራል። ሰይጣንን ለማሸነፍ ከፈለግን እግዚአብሔር የተናገረንን ቃል ለሰይጣን ማሳወቅ አለብን።
እየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንን ያሸነፈበት መንገድ ከመጽሓፍ ቅዱስ በመጥቀስ ነበር። "እንዲህ ተብሎ ተፅፏል … እንዲህ ተብሎ ተፅፏል… እንዲህ ተብሎ ተፅፏል…" በማለት (ማቴዎስ 4፡1-11) ።
የእግዚአብሔርን ቃል የምንጠራጠር ከሆነ እግዚአብሔርን ውሸታም እናደርገዋለን። ነገር ግን ሰይጣን ላይ የእግዚአብሔርን ቃል ስንጠቀም ከእግዚአብሔር እና ከቃሉ ጋር ቆመን ሰይጣንን እና ውሸቱን እንቃወማለን ማለት ነው። በተጨማሪም እንዲህ ስናደርግ ምንም እንኳን ያለንበት ሁኔታ እና ስሜታችን የሚነግረን የተለየ ቢሆንም ለሰይጣን የምንሰጠው መልእክት እግዚአብሔር የሚለው እውነት እንደሆነ ነው።
አዲስ ኪዳን የሚያስተምረን ሁለት የከበሩ እውነቶች አሉ። እነዚህም እግዚአብሔር ልጆቹን መምረጡ እና መቀበሉ ናቸው።
መመረጥ
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው እግዚአብሔር አስቀድሞ የመረጠን ልጆቹ ነን (1 ጴጥሮስ 1፡1-2) ። ይህ ማለት እ/ር በዘላለማዊ ችሎታው ልጆቹ የሚሆኑትን ከጊዜ መጀመሪያ በፊት ያውቅ ነበር።
በተጨማሪም "ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊት" እግዚአብሔር በክርስቶስ እንደመረጠን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (ኤፌሶን 1፡4)። ገና አዳም ከመፈጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት እያንዳንዳችንን ልጆቹ እንደሆንን እግዚአብሔር በስም ያውቀን ነበር። ስማቻችንም "የሕይወት መጽሐፍ" ላይ ተመዝግበው ነበር (ራዕይ 13፡8) ።
እነዚህ እጅግ ከፍተኛ ደህንነት ሊሰጡን የሚችሉ ሐቆች ናቸው።
የምንቆምበት የእግዚአብሔር መሠረት ሁለት እጥፍ ማኅተም እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል በእግዚአብሔር በኩል ያለው "እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑትን ያውቃል" ይላል። በሰው በኩል ያለው ደግሞ "የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ" ይላል። (2ኛ ጤሞቲዎስ 2፡19) ።
እግዚአብሔር ልጆቹን ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ያውቃቸው ነበር። ነገር ግን እኛ የእርሱ ልጆች መሆናችንን የምናውቀው ንሰሃ ገብተን ወደ እሱ ስንመለስ ብቻ ነው። ውስን የሆነው አእምሮአችን ግን እግዚአብሔር ልጆቹን እንዴት እንደሚመርጥ እና ለሰው ደግሞ እግዚአብሔርን የመምረጥ ወይም ያለመምረጥን ነጻነት እንደሚሰጥ አይረዳም። እነዚህ በኛ ግንዛቤ መገናኘት የማይቻላቸው ሁለት ትይዩ መስመሮች (parallel lines) ናቸው ። በሂሳብ የትይዩ መስመሮች ትምህርት ማብራርያ ግን እነዚህ መስመሮች ወሰን የሌለው ቦታ ላይ ይገናኛሉ - ወሰን የሌለው የእግዚአብሔር አእምሮ ውስጥ ማለት ነው።
ይህንን አንድ ሰው እንዲህ ብሎ አብራራው፤
በሕይወት መንገድ ላይ ስትጓዙ አንድ ቀን የተከፈተ በር ታገኛላችሁ። ከበሩ በላይ "ንሰሃ የገባና በክርስቶስ ያመነ በዚህ በር በመግባት የዘላለም ሕይወትን ያገኛል" የሚል ጽሁፍ አለ። በበሩ ወደ ውስጥ ከገባችሁ በኋላ ዞር ብላችሁ ስትመለከቱ በገባችሁበት በር በላይ "ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በክርስቶስ እየሱስ እግዚአብሔር ተመርጣችኋል" የሚል ጽሁፍ ታያላችሁ።
ተቀባይነትን ማግኘት
ለኃጢያቶቻችን ይቅርታን ማግኘት ያለፉትን በደሎች ያስወግዳል። ሆኖም ፍፁም ቅድስናን ስለማይሰጠን ፍጹም ቅዱስ ከሆነው እግዚአብሔር ፊት መቆም አንችልም። ስለዚህ ይህን ለማስተካከል እግዚአብሔር ለእኛ መፍትሄ ማድረግ ነበረበት።
ከእሱ ፊት ተቀባይነት እንዲኖረን ብቁ ማድረግ ነበረበት!
ተቀባይነትን ማግኘት ማለት እግዚአብሔር ፍጹም የሆነውን የክርስቶስን ጽድቅነት ለእኛ አደረገ ማለት ነው። ውጤቱም አሁን በእግዚአብሔር ፊት ስንቆም እንደ እየሱስ ፍጹም ሆነን ነው ማለት ነው! ይህ አስገራሚ እውነት ነው! እውነትም ነው! ይህ ማለት በአንድ ለማኝ ሰው የባንክ ሂሳብ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር እሱ ያልሠራበት እና የማይገባውን ብር ማግባት ማለት ነው። ይህ ገንዘብ ለለማኙ የነፃ ስጦታ ነው።
በእግዚአብሔር ተቀባይነትን ማግኘት ማለት ከዚህ በፊት በሕይወታችን ሙሉ ምንም ሃጢያት እንዳልሠራን ሆነን እና በአሁን ሰዓት በእግዚአብሔር ፊት ፃዲቅ ሆነን መታየት ማለት ነው።
የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል "በእርሱም ደግሞ ወደ ቆምንበት ወደዚህ ፀጋ በእምነት መግባትን አግኝተናል፤ በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን" (ሮሜ 5፡2) ። አሁን ወደ እግዚአብሔር መገኘት ውስጥ ያለምንም ፍርሃትና መጠራጠር መግባት እንችላለን። ይህን እንድናደርግ መንገዱን እግዚአብሔር ከፍቶልናልና።
በኤደን ገነት ውስጥ አዳምና ሄዋን ሃጢያትን እንደሠሩ የጥፋተኝነት ስሜትና የህፍረት ስሜት ስለተሰማቸው ራቁትነታቸውን በበለስ ዛፍ ቅጠል ሸፈኑ። እግዚአብሔርም የበለሱን ዛፍ ቅጠል ከላያቸው ላይ በማውለቅ እንስሳ ገድሎ በእንሰሳው ቆዳ አለበሳቸው።
እነዚያ የበለስ ዛፍ ቅጠሎች የእኛን ጥሩ ሥራ የሚያሳዩ ናቸው። እንደ ቅጠሎቹ ጥሩ ሥራችን በእግዚአብሔር ፊት ራቁትነታችንን ሊሸፍኑ አይችሉም። መጽሓፍ ቅዱስ ሲናገር መልካም ሥራዎቻችን በግዚአብሔር ፊት እንደመርገም ጨርቅ ናቸው (ትንቢተ ኢሳያስ 64፡6) ። የታረደው እንስሳ የእየሱስ ስለ እኛ ሃጢያት መሞትን የሚያሳይ ነው። የእንስሳው ቆዳ ደግሞ እኛን እንዲሸፍን የተሰጠው ፍፁም የሆነው የክርስቶስ ጻዲቅነት ነው። (ዘፍጥረት 3፡7,21) ።
ተቀባይነትን ማግኘት ከእግዚአብሐር የሚሰጥ ነፃ ስጦታ ነው። ማንም ሰው በሥራው ከእግዚአብሔር ተቀባይነትን አያገኝም። ስለዚህ "እግዚአብሔር እንዲቀበለን ጻድቅ መሆንን እንሻ" ማለት በጣም የተሳሳተ አባባል ነው።
ከዚህ አባባል ተቃራኒ የሆነ ነገር ግን ስህተት የሆነ አስተሳሰብ አለ። ይህም "በእግዚአብሔር ከተመረጥንና ተቀባይነትን ካገኘን ሃጢያትን ብንሠራ ምንም አይደለም" የሚል ነው። እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ስለመረጣቸው እና ስላጸደቃቸው ሃጢያትን አቅልለው የሚመለከቱ ሰዎች እግዚአብሔር ከመረጣቸው ውስጥ እንዳልሆኑ ያሳያሉ። (ሮሜ 4፡5 እና ያዕቆብ 2፡24 አነፃፅሩ)።
አንድ ጊዜ ከተመረጥንና ተቀባይነትን ካገኘን በኋላ የሰይጣን ክሶች በእኛ ላይ የሚያደርጉትን ውጤት ያጣሉ። "እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ካለ ማን ይቃወመናል?" (ሮሜ 8፡31) ። በእግዚአብሄር ተከሰናል ወይም ተጥለናን ብለን ፈጽሞ ማሰብ የለብንም።
"እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው" (ሮሜ 8፡33) ። ሀሌሉያ!
ይህ የወንጌል የምስራች ዜና ነው! ስለዚህ ሰይጣን ብዙ አማኞች እግዚአብሔር እንደመረጣቸው እና እንዳጸደቃቸው እንዳያውቁ ማድረጉ የሚያስገርም አይደለም።
የእሱ ደቀመዝሙር ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ ገልጾላቸው ስለ ነበረ እየሱስ ሐዋርያቶቹን ወደ ዓለም ሁሉ ሄዳችሁ ሰዎችን ደቀመዝሙር አድርጉ ሲላቸው ያለ ምንም ጥርጣሬ ምን ማለቱ እንደሆነ ገብቶአቸው ነበር (ማቴዎስ 28፡19)።
ሉቃስ 14፡25-35 ደቀመዝሙር ለመሆን መሟላት ያለባቸውን ሶስት ነገሮች ያብራራልናል። እዚህ ላይ እየሱስ አንድ ህንፃ ስለሚገነባ ሰው ይናገራል። ይህ ሰው መሠረት ከጣለ በኋላ በገንዘብ እጦት የተነሳ ህንጻውን መጨረስ ያቅተዋል (ቁጥር 28-30)። ይህ የሚያሳየን ደቀመዝሙር መሆን ዋጋ እንደሚያስከፍል ነው። መገንባት ከመጀመራችን በፊት በመጀመሪያ ደረጃ ወጪያችንን ማስላት እንዳለብን እየሱስ ነግሮናል ።
እግዚአብሔር ሀጥያታችን ከተወገደልን በኋላ ስለደቀመዝሙር ሳንረዳ ብዙ አመታትን እንድንጠብቅ አይፈልግም። እየሱስ ሰዎች ወደ እርሱ እንደመጡ ወዲያውኑ ደቀመዝሙርነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ይነግራቸው ነበር።
ደቀመዝሙር ለመሆን የማይፈልግ አማኝ ጣእሙን እንዳጣ ጨው ለእግዚአብሔር ዋጋ አይኖረውም (ሉቃስ 14፡35)።
ዘመዶቻችንን መተው
የደቀመዝሙርነት የመጀመሪያ ሁኔታ ለዘመዶቻችን ያለንን ተፈጥሮአዊ እና ግላዊ ፍቅር መቀነስ አለብን። እየሱስ ሲናገር "ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እህቶቹን የራሱንም ሕይወት እንኳ ሳይቀር ባይጠላ ደቀ መዝሙር ሊሆን አይችልም" (ሉቃስ 14፡26) ።
እነዚህ ጠንካራ ቃላቶች ናቸው። "መጥላት" የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? መጥላት የሚለው ቃል መግደል ከሚለው ቃል ጋር ይመሳሰላል (1ኛ ዮሃንስ 3፡15) ። መግደል ያለብን ነገር ቢኖር ለዘመዶቻችን ያለንን የተፈጥሮ ፍቅር ነው።
ይህ ማለት አናፈቅራቸውም ማለት ነው? አይደለም! በእርግጥ እንደዚያ ማለት አይደለም። ለሰው ልጅ ያለንን ፍቅር ስንተው እግዚአብሔር ደግሞ በሰማያዊ ፍቅር ይተካዋል። ከዚያም ለቤተሰቦቻችን የሚኖረን ፍቅር ንፁህ ይሆናል። ይህም ማለት በመጀመሪያ ደረጃ የምናፈቅረው እግዚአብሔርን እንጂ ዘመዶቻችንን አይሆንም።
ብዙ ሰዎች አባቶቻቸውን፣ እናቶቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውን፣ ወዘተ ማስቀየም ስለማይፈልጉ እግዚአብሔርን አያከብሩም። እግዚአብሔር ግን በሕይወታችን የመጀመርያው መሆንን ይፈልጋል። የመጀመርያውን ቦታ ካልሰጠነው የእርሱ ደቀመዝሙር መሆን በፍጹም አንችልም።
የእየሱስን ምሳሌ ተመልከቱ፤ ምንም እንኳን መበለት እናቱን ቢወድም በጥቃቅን ነገር ላይ ጭምር የአባቱን ፍጹም ፈቃድ እንዳይፈጽም እንድታደርገው አልፈቀደም። የዚህን ምሳሌ በጋሊላ ቃና ሠርግ ላይ እናያለን። እዚህ ላይ እየሱስ በእናቱ አነሳሽነት እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አልነበርም (ዮሃንስ 2፡4) ።
እየሱስ እንዴት ወንድሞቻችንንም እንደምንተው አስተምሮናል። ጴጥሮስ እየሱስን ወደ መስቀል ሞት እንዳይሄድ በከለከለው ጊዜ ከዚያ ቅደም ተናግሮት የማያውቀውን ከባድ ቃል በመጠቀም ሲመልስለት እናያለን። "ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና እንቅፋት ሆነህብኛል" አለው (ማቴዎስ 16፡23) ። ጴጥሮስ ይህን ሃሳቡን ያቀረበው ከፍ ባለ የሰው ፍቅር ነበር። ነገር ግን ጴጥሮስ የተናገረው የእግዚአብሔርን ፍቃድ የሚቃረን ስለነበረ እየሱስ ገሰጸው።
እግዚአብሔር ሁል ጊዜም በእየሱስ ፍቅር ውስጥ የበላይ ነበር። እኛም ተመሳሳይ አመለካከት እንዲኖረን ይፈልጋል። እየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ጴጥሮስን ምድር ላይ ካለ ነገር ሁሉ አስበልጦ ይወደው እንደሆነ ጠየቀው (ዮሃንስ 21፡15-17) ጌታን ከሁሉም ነገር አስበልጠው የሚወዱ ብቻ ናቸው የእሱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሀላፊነትን የሚሰጣቸው።
የኤፌሶን ቤተክርስቲያን መሪ መጀመሪያ ለጌታ የነበረውን ፍቅር እና ትጋት ስለቀዘቀዘ ከመሪነት መወገድ አስግቶት ነበር። (ራዕይ 2፡1-5) ።
ልክ እንደ መዝሙረኛው "በሰማይ ያለኝ ምንድነው? በምድርስ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ?" ማለት ከቻልን እውነትም ለደቀመዝሙርነት የመጀመርያውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተናል ማለት ነው (መዝሙረ ዳዊት 73፡25) ።
እየሱስ ከእኛ የሚፈልገው ፍቅር ስሜታዊ፣ የይሉኝታ፣ በመዝሙር ፍቅራችንን ለመግለፅ ለሰው ልጅ የምናቀርበውን አይደለም። የምንወደው ከሆነ እንታዘዘዋለን (ዮያንስ 14፡21) ።
የራሳችንን ሕይወ ት መጥላት
ደቀመዝሙር ለመሆን ማሟላት ያለብን ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ የራሳችንን ሕይወት መጥላት ነው። እየሱስ እንዲህ አለ፤ "ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር ...የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም" (ሉቃስ 14፡26)። ይህን ሲያብራራ እንዲህ አለ፤ "የራሱን መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ደቀመዝሙሬ ሊሆን አይችልም" (ሉቃስ 14፡27)። ይህ እየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች ሁሉ ጥቂት የተረዳነው ትምህርት ነው።
እየሱስ ደቀመዝሙር መሆን የሚፈልግ ሰው "ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ "አለ ሉቃስ (9፡23) ። ዕለት ዕለት ከፀሎትና እና መጽሐፍ ቅዱስ ከማንበብ በላይ አስፈላጊ የሆነው እራሳችንን መካድ እና መስቀላችንን መሸከም ነው። እራሳችንን መካድ ማለት ከአዳም የውረስነውን ሕይወታችንን መጥላት ማለት ነው። መስቀል መሸከም ማለት የራስን ሕይወት ወደ ሞት መውሰድ ማለት ነው። ይህን ሕይወት ወደ ሞት ከመውሰዳችን በፊት መጥላት አለብን።
የራሳችን ሕይወት በክርስቶስ ላለን ሕይወት ወና ጠላት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን "ሥጋ" ይለዋል። ሥጋችን የራሳችንን ክብር የራሳችንን ደስታ፣ የራሳችንን መንገድ እና የመሳሰሉትን እንድናገኝ ይፈትነናል። በእውነተኛነት ብንናገር አብዛኛዎቹ ምርጥ የምንላቸው ድርጊቶቻችን ሃቀኝነት የጎደላቸው እና ለግል ጥቅማችን የሚደረጉ እንደሆኑ እንገነዘባለን። ይህን ሥጋ ካልጠላን በቀር እየሱስ ክርስቶስን ልንከተለው አንችልም።
ለዚህ ነው እየሱስ ሕይወታችንን ስለመጥላት ደጋግሞ የተናገረው።
በእርግጥ ይህ ጉዳይ በወንጌል ስድስት ጊዜ ተደጋግሞ ተጠቅሷል (ማቴዎስ 10፡39 16፡25 በማርቆስ 8፡35 በሉቃስ 9፡24 በሉቃስ 14፡26 እና በዮሃንስ 12፡25) ። ጌታችንም ይህን ስለዚህ ደጋግሞ ተናግሮሯል። ቢሆንም ይህ ጉዳይ ሰባኪዎች ብዙ የማይሰብኩት ፣ ሰዎችም ያልተረዱት ሆኗል!
የራሳችሁን ሕይወት ለመጥላት መብታችሁን አትሹ፣ ዝና ማትረፍን አትፈልጉ ፣ የግል ምኞታችሁን፣ ፍላጎታችሁን፣ የኔ ያልኩት ብቻ የምትሉትን፣ ወዘተ ተዉት። የእየሱስ ደቀመዝሙር መሆን የምትችሉት ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ስትሆኑ ብቻ ነው።
ያለንን ሁሉ መተው
ደቀመዝሙር ለመሆን ሶስተኛው ቅድመ ሁኔታ ያለንን በሙሉ መተው ነው። እየሱስ እንዲህ አለ "ማንም ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀመዝሙሬ ሊሆን አይችልም" (ሉቃስ 14፡33)።
ንብረቶቻችን የራሳችን አድርገን የምንይዛቸው ነገሮች ናቸው። ሁሉንም መተው ማለት ማንኛውንም ነገር እንደራሳችን አድርገን አንቆጥርም ማለት ነው።
ምሳሌ በአብረሃም ሕይወት እናያለን። ይስሃቅ ለአብረሃም የእሱ የሆነ ልጁ ነበር። አንድ ቀን ይስሃቅን እንዲሰዋለት እግዚአብሔር አብረሃምን ጠየቀው። አብርሃምም ይስሃቅን መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ በመሰውያው ላይ አዘጋጀው። ነገር ግን እግዚአብሔር የአብረሃምን ፈቃደኝነት እና ታዛዥነት ስለተመከተ ጣልቃ በመግባት ይስሃቅን እንዳይሰዋ አደረገው (ዘፍጥረት 22)። ከዚያ በኋላ ምንም እንኳን ቤቱ ውስጥ ቢኖርም ይስሃቅ የግሉ እንዳልሆነ ተገነዘበ፣ ይስሃቅ የእግዚአብሔር ሆነ።
ያለንን ሁሉ መተው ማለት ይህ ነው። ያለንን ሁሉ መሰውያችን ላይ አድርገን ለእግዚአብሔር ማቅረብ አለብን።
እግዚአብሔር ካሉን ነገሮች አንዳንዶቹን እንድንጠቅምባቸው ሊፈቅድልን ይችላል። ቢሆንም እንደራሳችን አድርገን ማየት አንችልም። በራሳችን ቤት ውስጥ እንኳን ብንኖር ቤታችን የእግዚአብሔር እንደሆነ ማሰብና እርሱ ከክራይ በነፃ እንድንኖርበት እንደፈቀደልን ማሰብ አለብን! ይህ ነው እውነተኛ ደቀመዝሙርነት።
ንብረቶቻችንን በሙሉ እንደዚህ አድርገናል? ንብረቶቻችን የምንላቸው የባንክ ሂሳባችን፣ ሥራችን፣ ሙያችን፣ ስጦታዎቻችን፣ እውቀታችን፣ ሚስቶቻችን እና ልጆቻችን እንዲሁም በምድር ላይ አሉን የምንላቸውን ነገሮች በሙሉ ይጨምራል። እውነተኛ ደቀመዝሙር ለመሆን ከፈለግን እነዚህን በሙሉ በመሰውያችን ላይ ማቅረብ አለብን።
እግዚአብሔር በሙሉ ልባችን እንድንወደው ይፈልጋል። ማቴዎስ 5፡8 ላይ "ልበ ንጹሖች" የሚለው ይህን ነው። ንፁህ ህሊና ብቻ በቂ አይደለም። ንፁህ ህሊና የሚያሳየው ሃጢያትን እንደተውን ብቻ ነው። ንፁህ ልብ ሁሉንም ነገር የተወ ነው!
ስለዚህ እውነተኛ ደቀመዝሙርነት የሚከተሉት ላይ ስር ነቀል የሆኑ የአስተሳሰብ ለውጦችን ያካትታል።
1. ስለ ዘመዶቻችንንና የምንወዳቸውን ሰዎች
2. ስለ ራሳችን የግል ሕይወት እና
3. ስለ ንብረቶቻችን።
በክርስትና ሕይወት ጅማሬያችን ላይ እነዚህን ነገሮች ካልተጋፈጥን እውነተኛ መሠረትን ልንጥል አንችልም።
እየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀመዛሙርቶቹ ከነገራቸው ነገሮች አንዳንዶቹ፣
1. ሂዱና አሕዛብን ደቀመዝሙር እድርጉ፣
2. በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አጥምቋቸው፣
3. ያዘዝኳችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።
እዚህ ላይ የተእዛዛቶቹ ቅደም ተከተል አስፈላጊ ነው።
ደቀመዝሙር ለመሆን ፈቃደኛ የሆኑ ብቻ ናቸው መጠመቅ የሚችሉ። ህፃናት ወደ እየሱስ ሲመጡ እጁን ራሳቸው ላይ ጭኖ ባረካቸው። (ማርቆስ 10፡13-16) ። ነገር ግን ንሰሃ የገቡ አዋቂዎች ሲመጡ ደቀ መዛሙሮቹ እንዲያጠምቋቸው አደረገ (ዮሃንስ 4፡1-2 ተመልከቱ)።
ነገር ግን ዛሬ 'ቤተ ክርስቲያን' ውስጥ የምናየው ምንድነው? የምናየው ተቃራኒውን ነው። ህፃናቶች ይጠመቃሉ በአዋቂ ሰዎች ራስ ላይ እጆች ይጫናሉ (ለማረጋገጫነት)! ይህ እየሱስ ካደረገው ጋር በጣም ተቃራኒ ነው።
መንፈስ ቅዱስ በወረደበት የበዓለ ኀምሳ ቀን ብዙዎች ስለሃጢያታቸው ሲያዝኑ ጴጥሮስ "ንሰሃ ግቡ ተጠመቁ" አላቸው። ከዚህ ቀጥሎ መጽሓፍ ቅዱስ እንደሚለው "ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ"። (የሃዋርያት ሥራ 2፡38-41)
የእግዚአብሔርን ቃል አስተውለው የተቀብሉ እና ንሰሃ የገቡ ብቻ እንደተጠመቁ ግልጽ ነው። ይህን አድራጎት በ'ሃዋሪያት ሥራ' መጽሓፍ ውስጥ በተደጋጋሚ እናያለን።
ጥምቀት ማለት ምን ማለት ነው?
ሮሜ 6፡1-7 ስለጥምቀት ምንነት በግልጽ አስቀምጦታል። እዚህ ላይ አሮጌው ማንነታችን ከክርስቶስ ጋር እንደተሰቀለ እና ስንጠመቅ ከእየሱስ ጋር ሞተን እንደተቀበር ነው የሚያሳየው። አሮጌው ማንነታችን ከመቀየራችን በፊት የነበረው ሃጢያትን ማድረግ ይፈልግ የነበረው ማንነታችን ነው። ይህ ማንነት ከእየሱስ ጋር በመስቀል ላይ ተሰቀለ።
አዲሱን ኑሮ ከመኖራችን በፊት ይህንን መረዳት የግድ አስፈላጊ አይደለም። እግዚአብሔር ያለውን ማመን ብቻ ይበቃል። የእግዚአብሐር ቃል ክርስቶስ ጎልጎታ ላይ እንደተሰቀለ ሲነግረን እንደምናምን እዚህ ላይም የዱሮ ማንነታችን ከክርስቶስ ጋር ተስቅሏል ሲልም እናምናለን። እነዚህን ሁለት እውነቶች በእምነት እንቀበላቸዋለን።
አሮጌው ሰውና ስጋ አንድ አይደሉም። ስጋችን በውስጣችን ያለ የእግዚአብሐርን ፈቃድ የሚቃረን የግል ሕይወታችን ነው። ይህንን ሁላችንም እስክንሞት ድረስ ተሸክመን እንኖራለን። ስጋችንን ወደ ቤታችን ሊገቡ ካሰቡ ወንበዴዎች ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። አሮጌውን ሰው የማይታመን ሁልጊዜ በተከታታይ ለወንበዴዎቹ በር በመከፍት እንዲበጉ የሚያስችል አገልጋይ ጋር ይመሳሰላል። አሁን የሞተው ታማኝ ያልሆነው አገልጋይ ነው። ወንበዴዎቹ አስገዳጅና ጠንካሮች ናቸው! ነገር ግን አሁን ወንበዴዎቹ እንዳይገቡ በሩን ዘግቶ የሚይዝ አዲስ አገልጋይና አዲስ ሰውነት አለን።
ስንጠመቅ የአሮጌውን ሰው (ሃጢያት ማድረግ የሚወደው ሰው) መሞት፣ መቀበር እና ከክርስቶስ ጋር መነሳታችንን እናውጃለን።ከዚያም "በአዲስ ሕይወት እንመላለሳለን (ሮሜ 6፡4)
በኖህ ዘመን የነበረው የውሃ ሙላትም የጥምቀት ምሳሌ ነበር (1 ጴጥ 3÷20-21) ። እግዚአብሔር ዓለምን በሙሉ በውሃ ሙላት አጠፋ። ኖህም በመርከቡ ገብቶ ተርፎ አዲሱን ዓለም ለማየት ተላለፈ። አሮጌው ዓለም እና በውስጡ የነበሩ ነገሮች በሙሉ በውሃ ሙላት ተቀበሩ። ስንጠመቅ ዱሮ ከዓለም ጋር የነበረን ግንኙነት (ዓለማዊ ፋሽኖች፣ ዓለማዊ ጓደኞች፣ ወዘተ ጭምር) አሁን ማቋረጣችንን እና ከውሃ ውስጥ ስንወጣ ወደ አዲስ ዓለም ውስጥ መግባታችንን ነው የምናውጀው።
የጥምቀት ሁኔታ
አሁን ስለአጠማመቅ እንጠይቃለን። እንዴት ነው የምንጠመቀው?
Baptism (ጥምቀት) የሚለው ቃል የእንግሊዘኛ ቃል አይደለም። አዲስ ኪዳን በመጀመሪያ የተፃፈው በግሪክ ቋንቋ ነበር። ስለዚህም 'Baptism' የሚለው ቃል 'Bapto' ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም በውሃ/በፈሳሽ ራስን መሸፈን ወይም መስመጥ ማለት ነው። ይህ ለጥንት ሐዋርያት የጥምቀት ትክክለኛ ትርጉም ይህ ነበር። ማለትም በውሃ ውስጥ መስመጥ ማለት ነው። በሰዎች ራስ ላይ ውሃን ማርከፍከፍ ጥምቀት አይደለም።
ፍሊጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ሲያጠምቀው የነበረውን ሂደት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይነግረናል። (የሃዋሪያት ሥራ 8፡38,39)
‹‹… ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውሃ ወረዱ÷ አጠመቀውም። ከውሃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊሊጶስን ነጠቀው።… በእየሱስ ጥምቀትም ተመሳሳይ ነገር እናያለን።… ከተጠመቀም በኋላ ከውሃው ውስጥ ወጣ። (ማርቆስ 1፡10)
አዲስ ኪዳን ውስጥ ስናይ ጥምቀት ሁልጊዜ ውሃ ውስጥ በመነከር ነበር የተደረገው። ጥምቀት መቀበርን የሚያሳይ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ መነከር ያስፈልጋል። ሰዎችን ስንቀበር ራሳቸው ላይ አፈር በመንስነስ ሳይሆን ጠቅላላ ሰውነታቸውን በመሬት ሥር በማኖር ነው!
የሚገልጸው ለጥምቀት በቁ የሆኑት ሰዎች የዱሮው ማንነታቸው የሞተ እና ዳግመኛ ኃጢያት ማድረግን የማይሹ መሆናቸውን ነው። የሚቀበሩ የሞቱ ሰዎች ብቻ ናቸው! ያልሞተን ሰው መቅበር ወንጀል ነው!
በሶስቱም ስሞች ስለማጥመቅ
እየሱስ "በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም" አጥምቁ ብሎ አዘዘ (ማቴዎስ 28፡19)። እግዚአብሔር አንድ ስለሆነ ስሙ ነጠላ ነው። እግዚአብሔር አንድ ሁኖ ነገር ግን በሶስት የተለያዩ አካላት እንደሚገለጽ እየሱስ አስረዳ።
ለኃጢያታችን የሞቱት አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ አልነበሩም። ወልድ ነበር። እየሱስ ከአረገ በኋላ በአብ ቀኝ ተቀመጠ እንጂ በመንፈስ ቅዱስ ቅኝ አልተቀመጠም። እንደዚሁም ደቀ መዛሙርቱን እንዲረዳ የላከው መንፈስ ቅዱስን እንጂ አብን አልነበረም። ይህ በጣም ቀላል ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ሶስቱ በመዋጀታቸን ላይ ያላቸውን ሚና ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል።
በሃዋሪያት ሥራ ውስጥ በተደጋጋሚ እንደምናየው ሃዋሪያቱ ሰዎችን "በእየሱስ ስም" ያጠምቁ ነበር (የሃዋሪያት ሥራ 2፡38 ወዘተ)። እየሱስ በማቴዎስ 28፡19 ላይ ካለው ጋር እንዴት ነው ይህ ሊስማማ የሚችለው?
ሁለት ተቃራኒ የሚመስሉ ዐረፍት ነገሮችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይተን በቅርብ ስናጠናቸው ሁለቱም ትክክል መሆናቸውን እንገነዘባለን።
አብ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የአረማዊ ሥላሴ እንዳልሆኑ በግልጽ ለማሳየት ሃዋሪያቶቹ ወልድን እየሱስ ክርስቶስ ብለው ይጠሩ ነበር። ስለዚህም ሰዎችን "በአብ በወልድ እየሱስ ክርስቶስ እና በመንፈስ ቅዱስ" ስም ያጠምቁ ነበር። "በእየሱስ ክርስቶስ ስም" የሚለው ጥምቀት ከዚህ የመጣ ነው።
ከእምነት የመነጨ ታዛዥነት
የክርስቶስ ተከታዮች ሕይወት በታዣዥነት የተሞላ ለማድረግ በመጀመሪያ ላይ መከበር ያለበት ትእዛዝ ጥምቀት ነው። ይህም ታዛዥነት ከእምነት የመነጨ እንጂ በሰው አእምሮ ግንዛቤ (reasoning) የመጣ አይደለም።
እየሱስ እንደሰው አስተሳሰብ ቢሄድ ኖሮ ለመጠመቅ ወደ መጥምቁ ዮሃንስ ባልሄደ ነበር። ላለመጠመቅ ብዙ ምክንያቶችን ሊያመጣ ይችል ነበር። ለምሳሌ ያህል በሕይወቱ ምንም ኃጢያት አልነበረም። ዮሃንስም ለምን እየሱስ መጠመቅ እንዳስፈለገው አልገባውም ነበር። እየሱስ ግን እነዚህን የሰው አስተሳሰቦች ወደ ጎን አድርጎ መንፈስ ቅዱስ የሚለውን ታዘዘ (ማቴዎስ 3፡15)።
"በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤" (ምሳሌ 3፡5) የሰው አስተሳሰብ መንፈሳዊ እውነቶችን ስለማይገነዘብ በማሰብ ችሎታ ላይ መተማመን ዋነኛው የእምነት ጠላት ነው።
ስንጠመቅ ከሰውነታችን መጨረሻ ላይ ውሃ ውስጥ የሚገባው አናታችን ነው። ይህ ትልቅ ምልክት ነው! የማሰብን የበላይነት ማጥፋት በጣም አስቸጋሪ ነው! የአዳም ልጆች ሁሉ የሚኖሩት ነገሮችን አሰላስለው እና በራሳቸው ተማምነው በሚወስኑት ነው። ስንጠመቅ እንደዱሮው በራስ ማስተዋል ላይ መተማመናችን እንደሞተ ነው የምንመሰክረው። አሁን የምንኖረው በእምነት እና ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ነው። (ማቴዎስ 4፡4 ሮሜ 1፡17)
አንዳንድ ክርስቲያኖች ጥምቀትን እንደ አነስተኛ ጉዳይ ነው የሚያዩት። ኤልሳዕ ንዕማን ከቁምጥናው እንዲድን ሰባት ጊዜ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እንዲነከር ሲነግረው መጀመሪያ ላይ ንዕማን ትእዛዙን ንቆ አልተቀበለም ነበር። ነገር ግን ከበሽታው የዳነው ይህን ቀላል ትእዛዝ በመከተሉ ነው (መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 5፡10᎐4)። እግዚአብሔር በትናንሽ ነገሮች ላይ ታዛዥነታቸንን ይፈትናል።
ለእግዚአብሔር መታዘዝ ፈጽሞ መዘግየት የለበትም። የዱሮው ማንነታችሁ በእውነት ሞቶ ከሆነ ወዲያውኑ መቀበር አለበት። የሞተን ሰው አለመቅበር ወንጀል ነው!
"አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ" (የሐዋርያት ሥራ 22፡16)
ለሁላችንም የሚያስፈልጉ ሁለት ዋና ነገሮች አሉ። አንደኛው ስላለፉት ኃጢያቶቻችን ይቅርታን ማግኘት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለወደፊት እግዚአብሔርን የሚያስደስት አኗኗርን መኖር መቻል ነው። የመጀመሪያውን የእየሱስ መሞት ፈጽሞታል። ለሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ሰጥቶናል።
ለኑሮ እና ለአገልግሎት የሚያስፈልግ ኃይል
ከላይ የተጠቀሰውን የመጀመሪያውን አስፈላጊ ነገር እኛ በራሳቸን በፍጹም ማድረግ አንችልም። በእግዚአብሔር መደረግ ነበረበት። ሁለተኛውም እንዲሁ ነው፤ በራሳችን ኃይል የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሁሉ አሟልተን እሱን የሚያስደስት ኑሮ መሥርተን መኖር አንችልም። አንዳንድ አስተዋይ የሆኑ አማኞች ገና ክርስትናን ሲጀምሩ ሁኔታቸውን ተገንዝበው ወዲያውኑ እግዚአብሔር ይህን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። ሌሎች ደግሞ ለብዙ ዓመታት በራሳቸው ሞክረው ከተሽነፉ በኋላ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ኃይል እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።
የአንዳንድ ሰዎች ሁኔታ ግን የሚያሳዝን ነው፤ እነዚህ ሰዎች ብዙ ጊዜ በራሳቸው ሕይወታቸውን ለመቀየር ሞክረው ስለአቃታቸው እግዚአብሔርን የሚያስደስት የድል ኑሮ መኖር አይቻልም ብለው ስለወሰኑ ተስፋ ቆርጠው የተሸነፈ ኑሮ ይኖራሉ።
ይህም ሁኔታ ለጌታ ያለንን አገልግሎት እና ያለንን ምስክርነት ጭምር ይመለከታል። ብዙ አማኞች የክርስትና ኑሮአቸው ጅማሬ ላይ ለክርስቶስ ምስክር መሆን እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። ሆኖም በአብዛኛው ጊዜ ቃላቶችን አስተካክሎ ለሌሎች እንደሚገባቸው አድርጎ የመናገር ኃይል ላይኖራቸው ይችላል። በዚህ የተነሳ አንዳንዶች ይህ የመናገር ችሎታ እጦት ከተፈጥሮአቸው ስለሚመስላቸው ለክርስቶስ ምስክሮች ከመሆን ተስፋ በመቁረጥ በዚያው ይተዉታል።
ለሎች ደግሞ እግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ሊሰጣቸው ቃል እንደገባ ስለሚያስተውሉ እግዚአብሔርን ጠይቀው ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን ኃይል ያገኛሉ። እነዚም ሰዎች በድፍረት እና ከሰብአዊ ባህሪ ውጭ የሆነ ስጦታዎች ኖሮአቸው ምንም ሳያፍሩ ለክርስቶስ ውጤታማ ምስክሮች ይሆናሉ።
የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆነው ከመንፈስ ስንወለድ ነው። ከመንፈስ መወለድ እና በመንፈስ መጠመቅ (መነከር) የተለያዩ ናቸው። እግዚአብሔር እንደሚፈልገን ለመሆን እና እሱ እንድናደርግ የሚፈልገውን ለማድረግ ኃይል የምናገኘው በመንፈስ ስንጠመቅ ነው።
የአዲስ ኪዳን የበኩርነት መብታችን
በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ሥራ መሥራት እንዲያስችላቸው መንፈስ ቅዱስ የነበረው አንዳንድ ሰዎች ላይ ነበር። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ማንኛውም ሰው መንፈስ ቅዱስን ሊቀበል ይችላል። መንፈስ ቅዱስ የመጣው የእየሱስን ታላቅ ክብር ሊያሳየን እና እየሱስን እንድንመስል ሊያስችለን ነው።
መጥምቁ ዮሃንስ ሁለት አገልግሎቶች እንደሚኖሩት ተናግሮ ነበር። አንደኛው ኃጢአትን ማስወገድ ሲሆን ሁለተኛው ሰዎችን በመንፈስ ቅዱስ ማጥመቅ ነበር (ዮሃንስ 1፡ 29, 33)። ሁለቱንም መለማመድ ያስፈልገናል።
በአዲስ ኪዳን ውስጥ መጀመሪያ ላይ ያለው የተስፋ ቃል ይህ ነው፡
"እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል" (ማቴዎስ 1፡21)
በአዲስ ኪዳን ሁለተኛው የተስፋ ቃል ደግሞ ይህ ነው፤
"እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል" (ማቴዎስ 3፡11)
አዲስ ኪዳን በነዚህ ሁለት የተስፋ ቃላቶች መጀመሩ ታላቅ ትርጉምን ያዘለ ነው። ጊዜው እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ልዩ ዘመን ነበር። የአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ነበር። ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ልጆች ይህ ሁለት የበኩርነታችን መብት/ውርስ ነው - ከኃጢያታችን መዳን እና በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ። እግዚአብሔር ግማሹን ሳይሆን እነዚህን መብቶች በሙሉ ሊሰጠን ይፈልጋል።
የመጀመሪያው አምስቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍቶች የሚጀምሩት በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የተስፋ ቃል ነው (ማቴዎስ 3፡11፤ ማርቆስ 1፡8፤ ሉቃስ 3፡16፤ ዮሃንስ 1፡33፤ የሃዋሪያት ሥራ 1፤5) ሆኖም ብዙ ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል የራሳቸው አድርገው ከመውሰድ ቦዝነዋል።
የሕይወት ውኃ ወንዝ
በአዲስ ኪዳን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ዙፋን ተነስቶ ወደ ምድር በሚፈስ ወንዝ ጋር ይማሰላል (ዮሃንስ ራዕይ 22፡1 የሃዋሪያስ ሥራ 2፡33)። በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ማለት በፏፏቴው ስር መነከር ማለት ነው። የተጠሙ ሁሉ ወደ እርሱ መጥተው መንፈስ ቅዱስን ቢቀበሉ ከነሱ ውስጥ የሕይወት ውኃ ወንዝ እንደሚፈስ እየሱስ ተናግሯል (ዮሃንስ 7፡37)።
መጠነኛ እምነት ያላቸው አማኞች ግን እንደ ወንዝ ሳይሆን በእጅ እንደሚሠራ ፐምፕ (hand-pump) ናቸው። የዚህም ዓይነት ፐምፕ ከብዙ ልፋት በኋላ የሚያወጣው ውኃ ጥቂት ጠብታዎችን ነው። ይህ ሁኔታ እንዲህ መሆን የለበትም። ጥማታችን ወደ ጌታ ቢያመራን ነገሮች ሁሉ ይቀየራሉ። እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍላጎት በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተን ለሌሎችም በረከት እንድንሆን ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ በመጀመሪያ መረዳት ያለብን ምን እንደሚያስፈልገን ነው። ብዙ አማኞች በቃላት ትርጓሜዎች ላይ የማይረባ ክርክር ውስጥ ገብተው ይታያሉ። የሚያስፈልገን ኃይል ነው እንጂ የአሰያየም ዓይነት አይደለም። አሰያየማችን ተስተካክሎ ሕይወታቸን ግን ምንም ለውጥ የማይታይበት ከሆነ ምን ዋጋ አለው? በእውነተኛነት ወደ እግዚአብሔር መጥተን ሌሎችን የሚባርክ የሕይወት ውኃ ከሕይወታችን እንደማይመነጭ እንመን። ይህን የመጀመሪያ እርምጃ ከወሰድን እግዚአብሔር የጠየቅነውን እንደሚስጠን እናምናለን።
በመንፈስ ቅዱስ ለመጠመቅ የሚያስፈልጉን የእግዚአብሔርን ስም ከፍ ለማደርግ ሃያል ጥማት እና እግዚአብሔር ቃል የገባልንን እንደሚፈጽም የማያወላውል እምነት መኖር ነው። ስለዚህ በታላቅ ጥማት እና እምነት ይህን ኃይል እንድናገኝ ብንጠይቅ እግዚአብሔር አይነፍገንም።
ስለ ኃይል መጎናጸፍ
የመጀመሪያዎቹ ሃዋሪያት እየሱስን የተከተሉት ሁሉን ነገር ትተው ነበር። ሆኖም እግዚአብሔር የወሰነላቸውን አገልግሎት ለመፈጸም ከመሰማራታቸው በፊት በመንፈስ ቅዱስ እስከሚጠመቁ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው።
እየሱስም ቢሆን የአደባባይ አገልግሎቱን የጀመረው የኃይል እና የመንፈስ ቅዱስ ቅባት ካገኘ በኋላ ነበር (ሃዋሪያት ሥራ 10፡38)። እየሱስ ይህ ቅባት ካስፈለገው እኛ ደግሞ ምን ያህል ያስፈልገን ይሆናል።
እየሱስ ሃዋሪያቶችን "ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ" አላቸው (ሉቃስ 24፡49)። በድጋሚ ከማረጉ በፊት መንፈስ ቅዱስ እናንተ ላይ ሲወርድ "ኃይልን ትቀበላላችሁ" አላቸው (የሃዋሪያት ሥራ 1፡8)። የበዓለ ኀምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። እነዛ ፈሪ እና ብኩን የነበሩ ሁሉ ወዲያውኑ ደፋር እና በእሳት የተቀጣጠሉ የጌታ ምስክሮች ሆኑ። እየሱስ ልክ እንደነገራቸው ኃይል ተቀበሉ።
የክርስትናን ኑሮ መኖር የሚያስችለን የእግዚአብሔር ኃይል በሕይወታችን ውስጥ ሲኖር ነው እንጂ ሕግጋትን ማወቅ እና መከተል አይደለም። በመንፈስ ቅዱስ ስንጠመቅ የምናገኘው ኃይል እግዚአብሔርን እንድንታዘዝ እና እንድናገለግል ያስችለናል።
ልዩ ልዩ የመንፈስ አሠራሮች
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በንፋስ ይመሰላል። ንፋስ በተለያየ ጊዜ ወደ ተለያየ ኣቅጣጫ ይነፍሳል። እየሱስ "ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው" አለ (ዮሃንስ 3፡8) ። ስለዚህ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ የሚያሳዩት ለውጦች የተለያዩ ናቸው። እዚህ ላይ ዋነኛው ነገር ውስጣቸው በኃይል መሞላቱ ነው። ቤተ ክርስቲያንን እንደ ክርስቶስ አካል እንድንመሠርት እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ 'የኃይል ስጦታ' ይሰጠናል። እያንዳንዳችን የትኛውን ስጦታ እንደምናገኝ የሚወስነው እግዚአብሔር ብቻ ነው ።
ከነዚህ ስጦታዎች ውስጥ (1ኛ ቆሮንጦስ 14፡1-5) ትንቢት መናገር (ሰዎችን ለማነሳሳት፣ ለማበረታታት እና ለማጽናናት በኃይል እና በሥልጣን ለመስበክ) ከሁሉም በላይ ተፈላጊ ስጦታ ነው። ሌሎችም የማገልገል፣ የማስተማር፣ የመፈወስ፣ የመምከር፣ የገንዘብ መስጠት፣ የመሪነት፣ ወዘተ ስጦታዎች አሉ (ሮሜ 12፡6-8)፣ 1ኛ ቆሮንጦስ 12፡8-10)። በአእምሮአችን እና በምናውቀው ቋንቋችን ሳንገታ እግዚአብሔርን እንድናመሰግንበት እና እንደንጸልይበት እግዚአብሔር በአዲስ ቋንቋ (በልሳን) የመናገር ስጦታን ይሰጣል።
በመንፈስ ቅዱስ ያልተጠመቃችሁ ከሆነ እግዚአብሔርን ከልብ በመሻት ይህ በበኩር ልጅነታችሁ ያገኛችሁትን መብት ውሰዱ። "እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?... አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም" (ሉቃስ 11፡13፣ ያዕቆብ 4፡2) ።
ስለዚህ እግዚአብሔርን ከልባችን በመማጸን ያዕቆብ ፐኒኤል ላይ እንዳደረገው "ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም" እንበል (ዘፍጥረት 32፡26)።
እግዚአብሔር ዘንድ አድልኦ የለም። ለሌሎች ያደረገውን ሁሉ ለናንተም ያደርጋል። ዛሬም ቢሆን በትጋት ለሚሹት እግዚአብሔር ይከፍላል (ዕብራዊያን 11፡6)። ስሙን ከፍ አድርጎ ለሚያመስግን ሁሉ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ለመስጠት በጣም ዝግጁ ነው።
የወንጌል ሁለቱ ዋነኛ መልእክቶች እየሱስ በአመንዝራነት ለተያዘችው ሴት በተናገራት ይጠቃለላሉ፤
"እኔም አልፈርድብሽም"; እና (2) "ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ" (ዮሃንስ 8፡11)
መጽደቅ የክርስትና ሩጫ የሚጀመርበት/መነሻ ቦታ ሲሆን ቅድስና ደግሞ ሩጫው የሚካሄድበት መንገድ ነው። መቀደስ ማለት መለየት ማለት ነው። ስለዚህ ቅድስና ከኃጢያት፣ ከዓለማዊነት እና በራሳችን ላይ ብቻ ከሚያተኩር ኑሮ ሁሉ የምንለይበት ሂደት ነው።
የሩጫ ተሳታፊዎች ወደ ሩጫው መነሻ ቦታ የሚመጡበት ምክንያት የሩጫው ውድድር ላይ ለመሳተፍ እንደሆነ ሁሉ እኛም ወደ ክርስቶስ የምንመጣበት ምክንያት ለቅድስና ነው። አንድ ሯጭ ውድድሩ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት ሳይኖረው ከሌሎች ሯጮች ጋር ሩጫ ቦታ ላይ መገኝቱ ፋይዳ የለውም።
እግዚአብሔር ለኛ ያለው ፈቃድ
አብዛኞቻችን ወደ ክርስቶስ የመጣነው ለሆነ የግል ጥቅም ነው፤ ከህመም ለመፈወስ ወይም ከገሃነም እሳት ለመዳን ይሆናል። ምንም እንኳን የመጣነው ለራሳችን ጥቅም ቢሆንም እግዚአብሔር ተቀበለን።
ምንም እንኳን ወደ አባቱ ቤት የተመለሰው የሚባላውን ሲያጣ ቢሆንም የጠፋው ልጅ አባት ልጁን በጣም ስለሚወደው ልጁ ሲመለስለት በደስታ ነው የተቀበለው። እግዚአብሔርም እንደዚህ ነው!
የክርስትና ኑሮን የምንኖረው መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ብቻ ከሆነ የሚያሳዝን ነው። እግዚአብሔር ለሕይወታቸን ያለው ፈቃድ እየገባን ሲመጣ ፈቃዱን ለመፈጸም መጓጓት አለብን። የልባቸው ዓይኖች በርተው "የመጥራቱ ተስፋ" እንዲታያቸው ጳውሎስ ኤፌሶን ለነበሩት ክርስቲያኖች ይጸልይ ነበር (ኤፌሶን 1፡18)።
ሮሜ 8፡29,30 መጥራቱ ተስፋ ምን እንደሆነ ይነግረናል።
"ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤"
እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፈቃድ እየሱስን እንድንመስል ነው። ቅድስና ማለት ይኽ ነው፣ በየጊዜው የበለጠ እየሱስን መምሰል ማለት ነው። እንድሳተፍበት የተበረታታነው የክርስቲያን ሩጫ ይህ ነው። ይህንኑ ሩጫ አስቀድሞ የሮጠው እየሱስ ላይ አይኖቻችንን አድርገን ሩጫችንን እንቀጥል። ዕብራዊያን 12፡1,2)።
ከኃጢያት መላቀቅ
በዚህ ሩጫ የመጀመሪያው ድርጊት ኃጢያት ማድረግ ማቆም ነው። በኦሪት ሕግ ኃጢያትን ለማቆም የሚያበረታታ ወይም ልባዊ ምክር አልነበረም። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሃዋሪያቶቹ ሁሉ እንደተስማሙት ሁለቱ ዋና የወንጌል መልእክቶች ልክ እየሱስ እንዳለው ከውግዘት ነጻ መሆን እና ኃጢያት መሥራትን ማቆም።
ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎች "ኃጢአትንም አትሥሩ" አለ (1ኛ ቆሮንጦስ 15፡34)። ዮሃንስም "ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ" አለ (1 ዮሃንስ 2፡1)። ጴጥሮስም "ኃጢአትን ትቶአልና" ብሎ ያበረታታናል (1 ጴጥሮስ 4፡1)።
በሮሜ መዕራፍ 5 ላይ ጽድቅና በእምነት እንደሚገኝ ከገለጸ በኋላ ጳውሎስ ይህን ጥያቄ ያቀርባል፤ "እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? " (ሮሜ 6፡1)። እንደገና ደግሞ (ጠበቅ አድርጎ) "እንግዲህ ምን ይሁን? ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢአትን እንሥራን?" (ሮሜ 6፡15)። የሁለቱም ጥያቄዎች መልስ 'አይደለም' ነው። አንድ ጊዜም እንኳን ኃጢያት እንዳናደርግ አጥብቀን መሻት አለብን።
ይህ ከባድ መልእከት ነው? በኃጢያት ሥራቸው መቀጠልን ለሚፈልጉ መልእክቱ ከባድ ነው! በኃጢያት መያዛቸው ላንገፈገፋቸው ግን ነጻ የሚያደርግ አስደሳች መልእክት ነው። ማንም እስረኛ የሆነ ሰው ነጻ ሆኖ እንደሚለቀቅ ቢሰማ በጣም ደስተኛ ነው የሚሆነው። እንዲያ ዓይነት መልእክት ለዚህ ሰው ከባድ መልእከት ይሆናል?
እየሱስ የተቀባው ይህን ለማወጅ ነበር፡ "(በኃጢያት)ለታሰሩትም መፈታትን ....... (በሰይጣን) የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ" (ሉቃስ 4፡18)።
የአዲስ ኪዳን ታላቅ ቃል ኪዳን ይህ ነው፡
ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ (በእየሱስ በተመሠረተው አዲስ ኪዳን) በታች እንጂ ከሕግ (ብሉይ ኪዳን) በታች አይደላችሁምና።
በዚህ ጉዳይ ላይ ድል ለማግኘት የሚቻለው በመጀመሪያ ላይ የዚህ ዓይነት ሕይወት ሊኖራችሁ እንደሚቻል ስታምኑ ነው።
ወደ ኃጢያት የሚመሩ አፈታታኝ ሁኔታዎች እና ኃጢያት
ኃጢያትን ማድረግ እና ኃጢያትን ለማድረግ መፈተን የተለያዩ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ "ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች" (ያዕቆብ 1፡14,15)። ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የስጋችን ምኞት ካልፈጠረው በስተቀር ኃጢያት ከልባችን አይመነጭም። ሰይጣን ወይም ስጋችን ወደ አእምሮአችን ሃሳቦችን ሲያመጣ እንፈተናለን። አእምሮአችን በሃሳቦቹ ሲስማማ ኃጢያት ይረገዛል።
መፈተናችን ጥፋተኞች አያደርገንም። እየሱስም ተፈትኖ ነበር። ሆኖም አንድ ጊዜም ቢሆን ኃጢያት አልሠራም። ሙሉ በሙሉ ንጹህ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ እየሱስ "በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው" (ዕብራዊያን 2፡17) "በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው" (ዕብራዊያን 4፡15) እኛ እንደምንፈተነው ይፈተን ነበር፣ ነገር ግን ኃጢያትን ሥርቶ አያውቅም ነበር።
ብዙ ሰዎች እየሱስ ኃጢያትን ያሸነፈው ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ስለ ነበረ ነው ብለው ስለሚያምኑ ኃጢያት አለመሥራቱ አያስደንቃቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ብታስታውሱ እየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን እኩልነት ትቶ "ራሱን ባዶ አደረገ" ይላል። (ፊልጵስዩስ 2፡6,7) ምንም እንኳን በሰማይ እግዚአብሔር ቢሆንም በምድር በነበረ ጊዜ እንደማንኝውም ሰው ስለነበር ዛሬ እኛ ማግኘት የምንችለውን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር ያገኘው። ለዚህ ነው ይህንን ሩጫ "እየሱስን ተመልክተን" እንድንሮጥ የተነገረን። ዛሬ "ከኃጢአት ጋር (ስንጋደል)" የሚያበረታታንን የእሱን ምሳሌ ማየት እንችላለን (ዕብራዊያን 12፡2-4)። ይህም የሚሆነው እኛን የሚያጋጥሙን ፈታናዎች ላይ ሁሉ እየሱስ እንደ ሰው ሆኖ ድል ስለነበረው ነው። ስለዚህ ልንከተለው የምንችል ምሳሌ እና አርአያ ሆነልን (ዕብራዊያን 6፡20)።
"እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር" ማለት ይህ ነው፣ ክርስቶስ "በሥጋ (የ)ተገለጠ''... "በመንፈስ የጸደቀ" (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16) ። ምንም እንኳን እንደ እኛ ስጋ ቢለብስም ሕይወቱን በሙሉ መንፈሱን ንጹህ አድረጎ ጠበቀ።
እኛም እንደ እየሱስ ድልን የማኘት ተስፋ የሚሰጠን ይህ ነው። "በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በእየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል" እሱን ተከትለን መግባት እንችላለን (ዕብራዊያን 10፡20)። የቅድስና መንገድ ይህ ነው።
የቀድሞው ሰው እና አዲሱ ሰው
ቀድመን እንዳየነው የቀድሞው ሰው የሚመሰለው ሌቦች ቤት ውስጥ እንዲገቡ በሚፈቅድ በማይታመን ዘበኛ ነው። ይህ የቀድሞው ሰው ሞቶ ተቀብሯል። አሁን በውስጣችን ያለው አዲስ ሰው ግን "አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ" (ዕብራዊያን 10፡7) የሚል ነው።
የእየሱስ ደቀ መዝሙር ኃጢያት ሊያደርግ እንደሚችል እናውቃለን። ሆኖም የእየሱስ ደቀ መዝሙር ኃጢያት ማድረግ እና የማያምን ሰው ኃጢያት ማድረግ አንድ አይደሉም። ይህም ልዩነት ጽዳቷን በምትጠብቅ በድመት እና በአሳማ መካከል ባለው ልዩነት መመሰል ይችላል። ድመት ቆሻሻን አትወድ ሆኖም ቁሻሻ ውሃ ውስጥ በድንገት ልትወድቅ ትችላለች። አሳማ ግን ቆሻሻ ውሃ ውስጥ ቢገባ ደስ ይለዋል። ይህ የተፈጥሮአቸው ልዩነት ነው። የእየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነ አዲስ ማንነቱ ንጽህናን የሚወድ እና ኃጢያትን የሚጠላ ነው።
የቀድሞው ሰው/ማንነት ኃጢያት ማድረግን ይፈልጋል። አዲሱ ሰው/ማንነት ኃጢያት ማድረግን ፈጽሞ አይፈልግም። ነገር ግን አዲሱ ሰው ጠንካራ ካልሆነ ልቡን ከስጋው ፈላጎቶች መከላከል ሊያቅተው ይችላል። ይህም የሚሆነው የስጋውን ፍላጎቶች ስለወደደ ሳይሆን ፋላጎቶቹን ለማሸነፍ ጠንካራ ስላልሆነ ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው ምናልባት አዲሱ ሰው ራሱን በእግዚአብሔር ቃል ስላልመገበ ወይም ራሱን በጸሎት ስላላጠነከረ ይሆናል።
ስለዚህ ኃጢያትን ፈልጎ ማድረግ እና ወደ ኃጢያት መውደቅ የተለያዩ ናቸው። ራሳችንን ከመኮነን እንድንጠበቅ የነዚህን ልዩነት ማወቅ አስፈላጊ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፣ "ኃጢአትን የሚያደርግ(ማለት፣ ፈልጎ ኃጢያትን በየጊዜው የሚያደርግ) ከዲያብሎስ ነው" (1ኛ ዮሃንስ 3፡8)። በሌላ በኩል ደግማ እንደዚህ ይላል "ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ (ማለት፣ ኃጢያት ለማደረግ ፈልጎ ሳይሆን በስህተት/በድንገት ለተደረገ ኃጢያት) ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ እየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው" (1ኛ ዮሃንስ 2፡1,2)
በማወቅ እና ባለማወቅ የሚደረግ ኃጢያት
በማንነታችን ውስጥ ሁል ጊዜ ኖሮ ነገር ግን ያላስተዋልነው ኃጢያት እና በስህተት በኃጢያት ስንወድቅ የምናደርገው ኃጢያት ይለያያሉ። እኛ ያልተገነዘብነው ነገር ግን ከኛ የተሻሉ፣ የበሰሉ ክርስቲያኖች እኛ ላይ የሚያዩት ኃጢያት ይኖራል። በዚህ ዓይነት ላላወቅነው ኃጢያት ራሳችንን ማውገዝ አይገባም። የእግዚአብሔር ቃል እንዲይ ይላል፣ "ሕግ እስከ መጣ ድረስ ኃጢአት በዓለም ነበረና ነገር ግን ሕግ በሌለበት ጊዜ ኃጢአት አይቈጠርም" (ሮሜ 5፡13)። (ይህ ማለት ኃጢያት መሆኑን ሳናውቅ የምናደርገውን እግዚአብሔር አይቆጥርብንም)
በብርሃን ስንጓዝ ኃጢያት ከሕይወታችን እየቀንሰ ይሄዳል። እያነሱ ቢሄዱም የማናስተውላቸው ኃጢያቶች ሁልጊዜ በሕይወታችን ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚህ ይላል፤ "ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም" (1ኛ ዮሃንስ 1፡8)። በእኔ ምንም ኃጢያት የለም የሚል ሰው እንደ እየሱስ ፍጹም ነኝ ማለቱ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ግን "እርሱን እንድንመስል እናውቃለን" የሚለው እየሱስ ተመልሶ ሲመጣ እንጂ ከመምጣቱ በፊት አይደለም። (1ኛ ዮሃንስ 3፡2)። ስለዚህ ሙሉ በሙሉ ተቀድሰናል፤ ፍጹም ነን የሚሉ ሁሉ ራሳቸውን እያተለሉ ነው።
ባለማወቅ ከምናደርገው ኃጢያት መንጻት ያስፈልገናል። "የእየሱስ ክርስቶስ ደም (ባለማውቅ ካደረግነው) ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል" (1ኛ ዮሃንስ 1፡7)። ስለዚህ በድፍረት ፍጹም እና ቅዱስ ሆነው እግዚአብሔር ፊት ያለምንም ፍርሃት መቆም እንችላለን። የእየሱስ ደም ኃይል ይህን ያህል ነው። ሃሌ ሉያ!
ምህረት እና ጸጋ
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤"እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ" (ዕብራዊያን 4፡16) ምህረት እና ጸጋ የተለያዩ ናቸው። ምህረት ላለፉት ኃጢያቶቻችን ይቅር ስለመባል ነው። ለወደፊት በሕይወታችን ፈተና ሲገጥመን ደግሞ ጸጋ ያስፈልገናል።
ጸጋ የሚያስፈልገን ስንፈተን እና ልንወድቅ ስንል ነው። ጴጥሮስ ወደ ገሊላ ሃይቅ ውስጥ ሊሰምጥ ሲለ አንዳገኘው ማለት ነው (ማቴዎስ 14፡30)። የዚህን ጊዜ ነው ለጸጋ መጮህ ያለብን። እየሱስ ጴጥሮስን ሊይዘው እጁን እንደዘረጋለት እኛም ከመውደቅ የሚያድነን እና እንድንቆም የሚያስችለን ጸጋ ይሰጠናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ከመውደቅ እንደሚጠብቀን የሚያረጋግጡ ብዙ የሚያስደንቁ መልእክቶች አሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ የሚቀጥሉት ናቸው፤
በመጀመሪያ ላይ ማየት ያለብን እግዚአብሔር ከምንችለው በላይ እንደማንፈተን የገባልንን ቃል ኪዳን ነው።
"ከሚቻላችሁ መጠን በላይ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል" (1ኛ ቆሮንጦስ 10፡13)።
በተጨማሪም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡
ከመሰናከል አድኖአችሁ ከክብሩ ፊት እንከን እንደሌላችሁ አድርጎ ያቆማችኋል (ይሁዳ 24)።
እነዚህ እና ሌሎችም እግዚአብሔር የሰጠን ብዙ ቃል ኪዳኖች ስላሉን ኃጢያትን ማድረግ አይኖርብንም። ከዚህ ቅጥሎ (1ኛ ጴጥሮስ 4፡2) እንደሚለው የምንኖረው የግዚአብሔርን ፈቃድ ለማከናወን ብቻ ነው።
የሚያድግ ቅድስና
እየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሂዱና ያዘዝኋችሁንም ትእዛዛት ሁሉ እንዲጠብቁ አሕዛብን አስተምሯቸው አላቸው (ማቴዎስ 28፡20)። ጌታን የሚወድ ሰው መጀመሪያ ላይ በሙሉ ልቡ እነዚህን ትእዛዛት ለማውቅ ይጥራል ከዚያም ትእዛዛቶቹን ለመከተል አጥብቆ ይጥራል (ዮሃንስ 14፡21)።
በቀድሞው ሕግ መሠረት እግዚአብሔር ሕግ እና ትእዛዛትን ለሰው ሰጠ እንጂ እነዚህን ትእዛዛት ለመከተል የሚያስችል ኃይል ግን አልሰጠም። ይህ ከሆነ እግዚአብሔር ለምንድን ነው ሕግን ለሰው የሰጠው? ይህም የሆነበት ምክንያት ሰው በራሱ ጥረት እግዚአብሔር የሚጠብቅበት ደረጃ ላይ ለመድረስ አለመቻሉን ተገንዝቦ አዳኝ እና ረዳት እንደሚያስፈልገው እንዲያውቅ ነው። "እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል" (ገላትያ 3፡24)።
አሁን ግን እግዚአብሔር ከሰው ጋር አዲስ ኪዳን መሥርቷል። በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ትእዛዛትን ብቻ ሳይሆን ለአኗኗራችን ምሳሌ የሆነንን እየሱስ ክርስቶስን ሰጠን። እየሱስ በምድረዊ ኑሮው ጊዜ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ሁሉ መከተል እንዴት እንደሚቻል አሳይቶናል።
በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ሕጎቹን በልቦናችን እንደሚያኖር እና በልባችንም እንደሚጽፍ ተናግሮአል (ዕብራዊያን 8፡10)። ይህንንም የሚያደርገው ውስጣችን በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ነው። መንፈስ ቅዱስ ረዳታችን ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፈቃድ ማሳየት ብቻ ሳይሆን ፈቃዱን የመፈጸም ፍላጎት እንዲኖረን ያስችለናል። በተጨማሪም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስችለንን ጸጋ ይሰጠናል።
ቅዱሶች የሚያደርገን እግዚአብሔር ነው (1ኛ ተሰሎንቄ 5፡23)። ይህን በራሳችን ማድረግ አንችልም። እግዚአብሔር ለሕይወታችን ያለውን ፈቃድ እንድናሟላ ፍላጎትም ሆነ ችሎታን የሚሰጠን እሱ ስለሆነ በእሱ መተማመን አለብን። ሆኖም እኛ ማድረግ ያለብን ራሳችንን ማዳን ነው፤ "በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ" (ፈልጵስዩስ 2፡12,13)። እንደ ሮባት አድርጎ ስላልፈጠረን የሰጠንን በመጠቀም ራሳችንን ለማዳን መትጋት አለብን!
በኃጢያት የተነሳ ከሚመጣው ጥፋተኛነት ያነጻናል። ሆኖም ይህ ትእዛዝ ተሰጥቶናል፤ "በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ" (2ኛ ቆሮንጦስ 7፡1) እርክስና ውስጥ መግባታችን ሲሰማን ይህን ማድረግ አለብን።
ስለዚህ "በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ" (ሮሜ 8፡13) በተጨማሪም የመንፈስን ፍሬዎች ማለትም፤ ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ ገርነት፥ ራስን መግዛት በሕይወታችን የበለጠ ይታያል። እየሱስን ለመምሰል መቀየር ማለት ይህ ነው።
ስለዚህ የመንገዳችን ብርሃን በየጊዜው እየጨመረ ይሄዳል (ምሳሌ 4፡18) ። እግዚአብሔር የሰጠን ታላቅ ቅድስና ይሄ ነው።
አዲስ የተወለደ ልጅ መጀመሪያ ላይ ምግብ እና አየር ያስፈልገዋል። አዲስ ከመንፈስ የተወለደ ሰውም እንደዚሁ ምግብ እና ትንፋሽ ያሰፈልገዋል።
የእግዛብሔር ቃል ምግብ ሲሆን ጸሎት ደግሞ ትንፋሽ ይሆንለታል።
የእግዚአብሔር ቃል - መንፈሳዊ ምግባችን
ሕጻን ልጅ መጀመሪያ ላይ ወተት በመጠጣት ይጀምር እና ትንሽ ከፍ ሲል መደበኛ ምግብ ይበላል። መጽሐፍ ቅዱስ ወተትም መደበኛ ምግብም አለው። ወተት የሚባለው "ስለ ክርስቶስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት" ነው (ዕብራዊያን 6፡1)። ጠንከር ያለው ምግብ ደግሞ "የጽድቅና ቃል" ነው (ዕብራዊያን 5፡13)።
እግዚአብሔር ለሚያሳየን ነገሮች በፍጥነት መታዘዛችን ወይም አለመታዘዛችን ከወተት ወጥተን ወደ መደበኛ ምግብ ለመሻገር የሚፈጅብንን ጊዜ ይወስናል።
የእምነታችን እና የታዛዥነታችን መጠን የመንፈሳዊ እድገታችንን ይወስናል።
እግዚአብሔር በቃሉ ብዙ ተስፋ ስለሰጠን እንተማመንበታለን። መከተል ያለብንን ተእዛዛትም ሰጥቶናል። በየጊዜው የእግዚአብሔርን ቃል አንክረን ብናስብ፤ ብናምነው እና ታዛዦች ብንሆን በእግዚአብሔር ጽኑ መሠረት ስለሚኖረን ያለማቋረጥ ሁልጊዜ እናብባለን። እንዲህ ሲሆን እግዚአብሔር ስለሚባርከን የምንሠራው ሁሉ ይከናወናል (መዝሙረ ዳዊት 1:2 , 3 )
የእግዚአብሔርን ቃል በመመራመር ብቻ ማስተዋል አንችልም። መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ራዕይ ያስፈልገናል። በማቴዎስ 11፡25 ላይ እየሱስ መንፈሳዊ ነገሮች ከጥበበኞች እና ከአስተዋዮች ተሰውረው ለሕጻናት ተገልጠዋል አለ።
ሕጻናቶች ያላቸው ነገር ግን ጥበበኞች እና አስተዋዮች የሌላቸው ነገር ምንድን ነው?
ንጹሕ ልቦና ነው!
እግዚአብሔር ልብን ነው እንጂ አእምሮን አያይም። ትሁት ፤ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ለማያደርጉ እና በቃሉ ለሚንቀጠቀጡ ራዕይ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 66፡2)
እየሱስ የእግዚአብሔርን ቃል ማስተዋል የሚችሉት ፍቃዱን ለመፈጸም የሚፈልጉ ብቻ ናቸው አለ (ዮሃንስ 7፡17)።
የእግዚአብሔር ቃል - የመንፈስ ሰይፍ
ከሰይጣን ጋር ስንዋጋ መሳሪያችን የእግዚአብሔር ቃል ነው።
በእፌሶን 6፡17 ላይ ይህ "የመንፈስንም ሰይፍ" ይባላል።
በረሃ ላይ ሲፈተን እየሱስ ሦስት ጊዜ ይህን መሳሪያ በሚገባ ተጠቅሞ ነበር። ሰይጣን በፈተነው ቁጥር መልስ የመለሰለት "...ተጽፏል... በማለት ነበር (ማቴዎስ 4:4 , 7 , 10 )።
እየሱስ እንደዚህ ነበር ያሸነፈው፤ እኛም እንዲሁ ማሸነፍ እንችላለን።
ሰይጣን ከሳሽ ነው። ክስን እና ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ የእውነት መገለጥን ለይተን ማወቅ አለብን። ስይጣን ሁልጊዜ የሚፈልገው በእሱ ክሶች እንድንቸገር እና ራሳችንን እንድንኮንን ነው። ነገር ግን በልባችን ከመንፈስ ቅዱስ የምናገኘው እውነት ረጋ ያለ እና በተስፋ የተሞላ ነው።
ከሳሻንን ማሸነፍ የምንችለው በዚህ ብቻ ነው፤ "ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት" (ራዕይ 12፤11)። ስላለፈው ኃጢያቶቻችን ሰይጣን ሲከሰን ድል ማድረግ የምንችለው የእየሱስ ደም ሙሉ በሙሉ እንዳነጻን እና አንዳጸደቀን ስንመሰከር ብቻ ነው። እየሱስ የተጠቀመውን መሳሪያ መጠቀም አለብን "...ተጽፏል..."
የእግዚአብሔርን ቃል ለስይጣን መናገር የሰይጣንን ክሶች ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሰይጣን ወደ እምሮአችን የሚያመጣቸው እንደ ተስፋ መቁረጥ፤ ጭንቅት እና እንዲህ አይነት ሌሎችም ፈተናዎችንም ለማሸነፍ ይጠቅማል።
ለዚህ ነው የእግዚአብሔርን ቃል ማዋቅ ጠቃሚ የሚሆነው፤ ማለትም ፈተና ሲገጥመን መንፈስ ቅዱስ ትክክለኛውን የመጽሓፍ ቅዱስ ቃል ወደ አእሞሮአችን ያመጣል። አንክሮ አሰበ።
ስለዚህ በየቀኑ እግዚአብሔር እንዲገልጽልን እየለመንን ቃሉ ላይ አንክሮ ማሰብ እና ቃሉን ማሰላሰል መልካም ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ልባችን ውስጥ ስንደብቅ ኃጢያት እንዳንሠራ ይረዳናል (መዝሙረ ዳዊት 119፡11)።
እግዚአብሔር ለሕይወታችን ያለው ፕላን
እግዚአብሔር ለሕይወታችን እንከን የሌለው ፕላን አለው። በተጨማሪም ይህን ፕላን ማሟላት እንድንችል ሊመራን ይፈልጋል። በምድር ሳለን ትልቅ በረከት ያለው ኑሮ ኖርን ማለት ይህን ፕላን አሟልተን ስንኖር ነው። የሥራ መስክ ወይም የጋብቻ ምርጫን በምናስብበት ጊዜ እግዚአብሔር በእነዚህ ነገሮች ላይ ቀድሞ መንገድ ማዘጋጀቱን ማውቅ አስደሳች ነው! የሱን መንገድ ብንከተል በመንገዳችን ላይ ሰይጣን የጠነሰሰልንን እንቅፋቶች ማስወገድ እንችላለን። በቃሉ ነው እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀልን ፕላን የሚመራን።
"የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ" በሚለው መጽሃፌ በዝርዝር እንደገለጽኩት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማውቅ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው።
ጋብቻን በመንፈሳዊ መንገድ ስለማየት "ፍትወተ ሥጋ፣ ፍቅር እና ጋብቻ - በክርስቲያን አመለካከት" የሚል አርእስት ያለው መጽሓፍ ጸፌአለሁ።
ጸሎት - እግዚአብሔርን ማናገር
ከእዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት፤ በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ እግዚአብሐር የሚለንን እንሰማለን። ከሰማን በኋላ እግዚአብሔርን እናናግራለን።
ጸሎት እግዚአብሔር ይምንፈልገውን እንዲያደርግልን ለመጠየቅ ብቻ አይደለም። የጸሎት ዋነኛ አላማው በሙሽሮች መሃል ያለውን አይነት አንድነት ከእግዚአብሔር ጋር ለመመሥረት ነው።
ሙሽሪት ከሙሽራዋ ጋር እንዴት መነጋገር እንደምትችል የሚወስን ሕግ የለም።
ሆኖም ሥነ ሥርአት እንዲይዝ ጸሎታችን የሚከተሉትን ቢያካትት መልካም ነው፤ ።
1. አባታችንን ስለማንነቱ ማመስገን
2. ስለ ወደቅንባቸው ነገሮች እና ስለሃጢያታችን ንስሓ መግባት
3. ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አቤቱታ ማቅረብ
4. ስለ ሚያስፈልጉን ነገሮች አቤቱታ ማቅረብ
5. ስለ ሌሎች ምልጃ ማድረግ
6. እግዚአብሔር ስላደረጋቸው ነገሮች ማመስገን
7. እግዚአብሔር ለወደፊት ሰለሚያደርጋቸው ነገሮች ማመስገን
እየሱስ ሳትታክቱ ዘወትር ጸልዩ አለ (ሉቃስ 18፡1)።
በየቀኑ ስለሚገጥሙን ትናንሽ ነገሮችም ሳይቀሩ ለእግዚአብሔር መንገር መልከም ልምድ ነው። ይህን ስናደርግ ቀኑን ሙሉ በጸሎት መንፈስ እንውላለን። ስለዚህ እግዚአብሔርን ማናገር ደስታን የሚሰጥ እንጂ የማምለክ ሥርአት አይሆንብንም። ይህን ስናደርግ እግዚአብሔር በሚያስደንቅ መንገድ በልባቸን እንደሚናገረን እናያለን።
የጸሎት ትምርት ቤት ቢኖር ከላይ የተጠቀሰው የመዋለ ህጻናት ትምህርት ደረጃ ነው። በዚህ ማደግ የምንችለው ጠንካራ እምነት ሲኖረን ነው።
ያም ሆነ ይህ ጸሎታችን እየቀዘቀዘ ሄዶ ደረቅ እና ባዶ በተለምዶ የመጣ ሰው ሠራሽ ስርአት የሚከተል መሆን በፍጹም የለበትም። ጸሎት ከመተንፈስ ጋር ይመሳሰላል። መተንፈስ ካስቸገረን ይህንን ሁኔታ ያመጣ የሆነ ችግር እንዳለን እንገነዘባለን! ጸሎት ደረቅ እና የሚያስለች እንዲሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም።
ነገር ግን እየተሻሻልን ስንሄድ ጸሎት ከባድ ሥራ መሆኑን እንገነዘባለን። እንድንጸልይበት እግዚአብሔር በልባችን በሚያኖራቸው ትናናሽ ጉዳዮች ላይ ሃላፊነት ወስደን ታማኝነታችንን ስናሳይ፣ የበለጡ ጸሎት የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ይሰጠናል። ይህ ሲሆን እግዚአብሔር ሰዎችን ለመባረክ የሚያደርገው ሥራዎች ተካፋዮች እንሆናለን።
እየሱስ "ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር" ጸለየ (ዕብራዊያን 5፡7)። በጌተሰማኔ አጽንቶ ሲጸልይ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ (ሉቃስ 22፡44)። ጸሎቱ በጣም የጠና ነበር።
እየሱስ አንድ ጊዜ ሌሊቱን ሁሉ ሲጸልይ አደረ (ሉቃስ 6፡12)። በየጊዜው ወደ ምድረ በዳ ብቻውን ሄዶ ይጸልይ ነበር (ሉቃስ 5፡16)። አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ተናገረ "ቱሪስቶች አዲስ ቦታ ሲሄዱ የሚጎበኙ ቦታዎችን ማየት እንደሚፈልጉ ሁሉ እየሱስ ደግሞ በሄደበት ሁሉ ለጸሎት ያሚያመች ጸጥ ያለ ቦታ ይፈልግ ነበር"።
ይህ የእየሱስ ምሳሌ ጸሎት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳየናል። እየሱስ ያን ያህል መጸለይ ካስፈለገው እኛ ደግሞ ከዛ የበለጠ ጸሎት ያስፈልገናል።
የሚያስፈልገውን ዋጋ ከፍላችሁ ስንፍናን አሸንፋችሁ የጸሎት ሰው ለመሆን ወስኑ።
ቀደም ብለን እንዳየነው ተለውጠን እየሱስን እንድንመስል እግዚአብሔር ይፈልጋል። የዚህ አይነት ለውጥ ከሌሎች የእየሱስ ደቀ መዝሙሮች ተነጥለን ለብቻ ስንሆን አይመጣም። መለወጥ የመንችለው ከሌሎች የክርስቶስ ደቀ መዝሙሮች ጋር በአንድነት ስንሆን ብቻ ነው።
እግዚአብሔር የሚፈልገው በእሱ ተማምነን እንድንኖር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር አንድነትን ፈጥረን እንድንኖር ነው። በብሉይ ኪዳን ጊዜ እግዚአብሔር በግለሰቦች ውስጥ ነበር የሠራው - ሙሴ ወይም ኤልያስ ፣ መጥመቁ ዮሓንስ ፣ ወዘተ።
በአዲስ ኪዳን ግን እግዚአብሔር የሚፈልገው ክርስቶስ ራስ የሆነበት በደቀ መዛሙሮች አንድነት የቆመ አካል ነው። 'ቤተ ክርስቲያን' ማለት ይህ ነው፤ የእየሱስ አካል (ኤፌሶን 1:22 , 23 ; 2:14-16)።
ቤተ ክርስቲያን - የክርስቶስ አካል
ቤተ ክርስቲያን የመሰብሰቢያው ሀንጻ ወይም የሃይማኖት ወገን (denomination) አይደለም። ችርች (church) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል 'እክሌሲያ' ከሚለው የግሪክ ቃል የተተረጎመ ነው። እክሌሲያ ማለት ከሌሎች ተለይተው የተጠሩ ሰዎች ስብሰባ ወይም ጉባዔ ማለት ነው። እዚህ ላይ የሚጠቅሰው ከዓለም ወጥተው ከሁሉ ተለይተው ለእግዚአብሔር የተሰጡ ሰዎችን ነው።
በምድር ላይ የእግዚአብሔርን ጥሪ ተከትለው ዓለምን የተዉ እና ኃጢያትን የጠሉ ሁሉ የእየሱስ አካል የሆነውን ቤተ ክርስቲያን ይመሥርታሉ። በየስፍራው እንደነዚህ አይነት አማኞች አንድነትን ፈጥረው ላአካባቢያቸው የዚህ አካል መግለጫ ይሆናሉ።
የመጀመሪያው የክርስቶስ አካል እንደሰው ሆኖ ወደ ምድር ሲመጣ የነበረው አካል ነበር። በዛ ሰውነት እግዚአብሔር ራሱን ለዓለም አሳየ። እየሱስ ሰውነቱን ለእግዚአብሔር ፍጹም አድረጎ ስለሰጠ መጨረሻ ላይ "እኔን ያየ አብን አይቶአል" (ዮሃንስ 14፡9) ማለት ቻለ።
ኡሁን ያለን ጥሪ ለአካባቢያችን እየሱስን በአኗኗራችን ማሳየት ነው። ለብቻው ማንም ሰው እየሱስን ለማሳየት በቂ አይደለም። ስለዚህ እርስ በእርስ መተባበር ያስፈልገናል። ከመሃከላችን የላቀ ነው የምንለው ሰው አለመመጣጠን አለበት። ማንኛችንም ጠንካራ ጎን እንዳለን ሁሉ ደካማ ጎንም አለን። በአንዳንድ ነገሮች ላይ እየሱስን መምሰል ብንችልም በሁሉም ነገሮች ላይ መምሰል አንችልም። በአንድነት ስንሆን ግን የአንደኛችን ደካማ ጎን በሌላው ጠንካራ ጎን ሊሸፈን ይችላል። በመሃላችን ፍቅር እና ታዛዥነት ቢኖር እየሱስን ሙሉ ለሙሉ ለማያምነው ዓለም ማሳያት እንችላለን። እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ያለው ዓላማም ይህ ነው።
አካባቢያችን ያለ ቤተ ክርስቲያን አባል ስለ መሆን
እንደተቀበላችሁ ወዲያውኑ ለእግዚአብሔር ቃል የሚታዘዙ እና የክርስቶስን አርአያነት የሚከተሉ ደቀ መዝሙሮች ፈልጋችሁ ከነሱ ጋር አንድነት መፍጠር ያስፈልጋል።
በክርስትና ውስጥ ብዙ የእምነት ወገኖች (denominations) ስላሉ አዲስ ኪዳን ግራ ልያጋባ ይችላል። በተለያዩ የእምነት አመለካከቶች የተነሳ በብዛት ስለተከፋፈሉ ብዙ ብዙ የእምነት ወገኖች በምድር ላይ እነሱ ብቻ እውነተኛ የእየሱስ ተከታዮች የሆኑ ይመስላቸዋል!!
ከእነዚህ የሃይማኖት ወገኖች ውስጥ ብዙዎቹ የመጽሃፈ ቅዱስ እውቀታቸውን በመሳየት የክርስቶስ አካል ለመሆን ከፈለጋችሁ የነሱ አባል መሆን እንዳለባችሁ ይናገራሉ!
የእምነት አመለካከታቸው እንደነሱ ያልሆኑ እግዚአብሔር ሌሎች ብዙ ልጆች እንዳሉት እነዚህን ሰዎች ማሳመን የሚቻል አይደለም! ይሄ ነው አግባብ የሌለው ጥላቻ ኃይል! ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ከተያዙበት ፈሪሳዊነት አና አምልኮታዊነት ውስጥ እንዳትወሳሰቡ መጠንቀቅ አለባችሁ።
ጌታን ለሚወዱ እና ከልባቸው ለሚከተሉ ሁሉ ልባችሁን ክፍት አድርጉ። ባንድንድ ነገሮች ላይ አመለካከታቸው የተለየ ሊሆን ይችላል። ይህ ሁኔታ ከባድ መሆን የለበትም። እግዚአብሔር በሰጣቸው ብርሃን ይጓዙ እንጂ እግዚአብሔር ለእኛ በሰጠን ብርሃን እንዲጓዙ ማስገደድ አንችልም።
የእግዚአብሔርን ልጆች ሁሉ ስለመቀበል
የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑ ሁሉ ወንድም እና እህቶቻችን መሆን አለባቸው።
እግዚአብሔር የተቀበላቸውን ሁሉ በሙሉ ልባችን መቀበል አለብን (ሮሜ 12፡1 ; 15፡17)። እየሱስ አንድን ሰው ወንድሜ ብሎ መጥራት ካላሳፈረው እኛም ማፈር የለብንም (ዕብራዊያን 2፡11)።
የአማኞች አንድነት ጉዳይ ላይ ሁለት ተቃራኒ የሆኑ የአማኞችን ሁኔታ የሚያሳዩ ሁኔታዎች አሉ። አንደኛው በአንድነታቸው መሃል አለመግባባትን ለማስወገድ ለዕውነት አለመቆም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሁሉም ነገር ላይ አንድ አይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ማስገደድ ነው። ብልህ ከሆናችሁ እነዚህን ሁኔታዎች ታስወግዳላችሁ።
የእግዚአብሔር ሥራ አሠራር ላይ ከማንስማማቸው ሰዎች ጋር አብሮ መሥራት እንደማይቻል ግልጽ ነው። ሆኖም ከእኛ ጋር የአማኞች አንድነት ለመፍጠር የሚሹትን የግድ በእያናዳንዱ ጥቃቅን ነግሮች ሁሉ የኛን አይነት አመለካከት እንዲኖራቸው ማድረግ የለብንም። ከአንድ ሰው ጋር አብሮ መሥራት እና የአማኞች አንድነት መፍጠር የተለያዩ ናቸው።
ቢሆንም በአካባቢያችሁ የመንፈሳዊ ቤት የሚሆናችሁ እና እናንተም ለመሳተፍ የሚስማማችሁን ቤተ ክርስቲያን መፈለግ አለባችሁ።
የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን
አካባቢያችሁ ካሉት ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ በአብዛኛው አዲስ ኪዳንን የሚከተል ፈልጉ። በሂደት አዲስ ኪዳን የበለጠ እየገባችሁ ስትመጡ ይህን ቤተ ክርስቲያን ትታችሁ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የበለጠ ከሚቀራረብ ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን መቀየር ትችላላችሁ።
የዚህ አይነት እድገት የሚኖረው ሰው በመንፈስ እየበሰለ ላለ እና ለሕይወቱ እግዚአብሔር ያዘጋጀለትን ታላቅ ነገር ለማግኘት ለሚሻ ነው። በዚህ ነገር ላይ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁን ታላቅ የሆነውን ትታችሁ በሱ ቦታ ያነሰ ነገር በፍጹም አትቀበሉ። ይህን ካደረጋችሁ በዘላለማዊ ሕይወት ጊዜ ምንም አትቆጩም።
የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ምንም የሃይማኖት ወገን መለያ ስም (denomination) አይኖረውም። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በእየሱስ ስም የተሰበሰቡ የአማኞት አንድነት ነው። እየሱስ በዚህ አይነት ከተሰበስቡት መሃከል ብቻ እንደሚገኝ ተናግሮአል (ማቴዎስ 18፡20)።
የምትሳተፉበት ቤተ ክርስቲያን የእግዚብሔርን ቃል ብቻ የእምነት እና የሕይወት መሠረት አድርገው የሚቀበል መሆን አለበት። ብዙ አምልኮአዊ (cultistic) አካሎች መጽሐፍ ቅዱስን ነው የምንከተለው ብለው ቢሉም መሪዋቻቸው ለሚጽፏቸው ጽሁፎች የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ክብደት ይሰጣሉ። ቀረብ ብላችሁ ስታዩአቸው ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ወደ መሪዋቻቸው አመለካከት እንደሚያዘነብሉ ታያላችሁ። ብዙ መልካም ነገሮች ሊኖሯቸው ይችላል። ነገር ግን እነሱ ጋር ከገባችሁ ብዙም ሳይቆይ ለነሱ አምልኮአዊ (cultistic) አስተሳስብ ተገዢ ትሆናላችሁ።
እግዚአብሔር ቄሶች ስላደረገን በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁላችንም ቄሶች ነን (1ኛ ጴጥሮስ 2፡9)። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማገልገል የሚችሉት የተለዩ ቄሶች ወይም 'መጋቢዎች' (ፓስተሮች) ብቻ ናቸው የሚል ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ፈቃድ ተቃራኒ ነው።
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በሽማግሌዎች (ከአንድ በላይ) እንድትመራ ድንግጓል። እነዚህ ሽማግሌዎች ሙሉ ሥራቸው ይህ መሆን የለበትም (የሃዋሪያት ሥራ 14፡23; ቲቶ 1፡5)
የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን በሚሰባሰቡበት ጊዜ ትኩረት ማግኘት ያለበት ዋናው ቁም ነገር የእግዚአብሔርን ቃል መስበክ ነው። በቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ጊዜ ብስለት እና መንፈሳዊ ስጦታ ያላቸው አማኞች ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል የማካፈል ነጻነት ይኖረቸዋል።
የሚነገረው ቃል ከመንፈስ ቅዱስ የመነጨ ከሆነ ውጤቱ ለሰዎች እረፍት እና ብርታት ይሆናል። በተጨማሪም በሰዎች ልብ ያለውን ሚስጥር ያጋልጣል። ይህ ሲሆን የሚሰሙ ሁሉ እግዚአብሔር እየተናገረ እንደሆነ ይገነዘባሉ (1ኛ ቆሮንጦስ 14:3 , 24-31 )።
የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ዋነኛው ተግባር ደቀ መዝሙሮችን ማፍራት እና የእየሱስን ተእዛዛት ሙሉ በሙሉ እንዲታዘዙ ማስተማር ነው (ማቴዎስ 28:19 , 20 )። እንዲህ አይነት ቤተ ክርስቲያን ከሌላው የሚለየው ባህሪ በአማኞቹ መሃል ያለው ፍቅር ነው። እየሱስ እንደዚህ አለ "እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ" (ዮሃንስ 13፡35)
የእግዚአብሔር ቃል በኃያልነት የሚነገርበት፤ የእግዚአብሔር ፍቅር የሰፈነበት እና የጌታ መገኘት የሚታይበት አካባቢያችሁ ያለ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሳተፍ አለባችሁ።
የአማኞች አንድነት አስፈላጊነት
የአማኞችን ህብረት ለማጠንከር እና ከሌሎች አማኞች ጋር በፍቅር መኖር ከፈልግን በየቀኑ ምን ያህል ራሳችንን መካድ እንዳለብን እንገነዘባለን።
ሰይጣን ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ልጆች መሃከል መከፋፈልን ይፈጥራል። ጠንካራ ክርስቲያኖች ከሆንን ሁልጊዜ ንቁ ሆነን የዚህን አይነት ክፍፍሎች እንከላከላለን። የእየሱስ አካል ውስጥ የአማኞች አንድነት ሲፈርስ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለእኛም ጎዳት ነው።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነት ሲመሠረት ታላቅ ኃይል ይሆናል። ሰይጣን የሚሸነፈው አንድነት ባለው ቤተ ክርስቲያን ነው።
እየሱስ እንዲይ አለ፣ ሁለት አማኞች ብቻ እንኳን በአንድ መንፈስ ሆነው አንድነት ካላቸው እኔ መሃላቸው ስላለሁ እግዚአብሔር የሚጠይቁትን ያደርጋል። ሁለት ወይም ሶስት አማኞች በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ከተሰበሰቡ የሰይጣንን ሓይል በሰማይም በምድርም ማሰር ስለሚችሉ ሰይጣንን ኃይል ያሳጡታል። ሰዎችንም ከሰይጣን እጅ ነጻ ማውጣት ይችላሉ (ማቴዎስ 18:18-20)።
ለዚህ ነው ሰይጣን በቤት ክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ ግሩፖች እና በሰዎች መሃከል መከፋፈልን የሚፈጥረው። ይህን የሚያደርገው እንድነት ያለው ቤተ ክርስቲያን የሱን መንግሥት እንዳያጠቃ ለመከላከል ነው። የስይጣንን ሴራዎች ችላ ሳንል ሁልጊዜ ንቁ ሆነን መከላከል አለብን።
የእየሱስ እጆች አና እግሮች በአንድነት እና በመተባበር መሥራት ባይችሉ ኖሮ ምድር ላይ በነበረ ጊዜ ሥራው ምን ያህል ውስን ይሆን እንደነበረ አስቡ። የእግዚአብሔርን ክብር ለዓለም ባሳየበት ደረጃ ማሳየት ባልቻለ ነበር። ዛሬ አማኞች ሲከፋፈሉ በመንፈሳዊው አካሉ ወይም የቤተ ክርስቲያን ራስ ሆኖ እየሱስ የሥራዎች ውስንነት ይገጥመዋል።
እኛም ተሸናፊዎች እንሆናለን። ከአንድ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ ሰው ጋር ተቃቅራችሁ ስትለያዩ በዚህ ሰው በኩል ብቻ ከእግዚአብሔር ሊመጣላችሁ የነበረውን ታጣላችሁ። "ከቅዱሳን ሁሉ ጋር" ብቻ ነው የእየሱስን ፍቅር ማወቅ የምንችለው (ኤፌሶን 3:17-19 )።
(ስለ ክርስቲያኖች አንድነት አስፈላጊነት በጥልቅ ለማወቅ "በክርስቶስ አንደ አካል" የሚለውን መጽሃፌን ማንበብ ትችላላችሁ)
በብሉይ ኪዳን ዘመናት ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት እና እግዚአብሔር ወደፊት ስላለው እቅድ ግልጽ የሆነ እውቀት አልነበረም። እነዚህ ሁለት ነገሮችን በተመለከተ እየሱስ በግልጽ አስተሞሮአል። እነዚህን ነገሮች ማወቅ ለእኛም መልካም ነው።
ከሞት በኋላ ያለው ምንድን ነው?
እየሱስ ሞትን ስላሸነፈ የእየሱስ ተከታይ የሆነ ሰው ሞትን አይፈራም። ሞት የተሸነፈ ጠላት ነው። የእየሱስ መሞት የሰይጣንን ኃይል ሰለወሰደበት ሞትን አንፈራም (ዕብራዊያን 2:14 , 15 )። አሁን የሞት ቁልፍ ያለው እየሱስ ዘንድ ነው (ራዕይ 1፡18)። ለተከታዮቹ የሞትን በር የሚከፍተ እየሱስ ብቻ ነው። ሰይጣን ሊነካቸው አይችልም።
አንድ ሰው ሲሞት ምንድን ነው የሚከተለው? ይህን ጥያቄ እየሱስ ስለ ባለ ጸጋው እና ስለ አልዓዛር በመናገር በግልጽ መልሶታል። እዚህ ላይ ወደፊት ሳትቀጥሉ ሉቃስ 16:19-31 ብታነቡ መልካም ነው።
እየሱስ በተናገራቸው ምሳሌዎች ሁሉ የሰዎችን ስም አይጠቅስም። ስለዚህ ይህ ታሪክ ምስሌ አይደለም። ባለ ጸጋው እና አልዓዛር እውነተኛ ሰዎች ነበሩ።
የሞቱ ሰዎች የሚሄዱበት ሁለት ቦታዎች ብቻ እንደሆኑ እየሱስ እዚህ ላይ ገልጿል። አንደኛው መንግሥተ ሰማያት ('የአብረሃም እቅፍ' ወይም 'ገነት') ማለትም የምቾት ቦታ ሲሆን ለላው ደግሞ ሲኦል፣ የስቃይ እና የመከራ ቦታ ነው። አንድ ሰው እንደሞተ ገና አስከሬኑ ሳይቀበር ነፍሱ ከእነዚህ ከሁለቱ ወደ አንዱ ቦታ ትሄዳለች። ምንም እንኳን አካል ባይኖረውም አካባቢው ስላለው ምቾት እና ህመም ንቁ ነው።
ሰው ሶስት ክፍሎች አሉት፣ መንፈስ፣ ነፍስ እና አካል (1ኛ ተሰሎንቄ 5፡23)። በሞት ጊዜ መንፈስ እና ነፍስ ከአካል ተለይተው ወደ መንግሥተ ሰማያት ወይም ወደ ሲኦል ይሄዳሉ።
እየሱስ በመስቀል ላይ ሳለ ባደረገው ጥፋት ለተጸጸተው ሌባ የዚያኑ ቀን በእርሱ ጋር በገነት እንደሚሆን ነገረው። እየሱስ እና የሌባው ነፍሶች ከሥጋቸው እንደተለዩ ወዲያው ወደ ገነት ሄዱ። ከሞተ በኋላ ለሶስት ቀናት 'በምድር ልብ' ውስጥ እንደሚሆን እየሱስ ተናግሮ ነበር (ማቴዎስ 12፡40)። ስለዚህ በዚያን ጊዜ ገነት በምድር ልብ ውስጥ እነደነበረች እንገነዘባለን። ነገር ግን እየሱስ ከሞት ሲነሳ " ከምድር ታችኛ ክፍል....ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ" ( ኤፌሶን 4:8 , 9 )። ገነትን እና ውስጥ ያሉትን ነፍሳት ጭምር ወደ ሶስተኛው ሰማይ ወሰዳቸው።
2ኛ ቆሮንጦስ 12 ቁጥር 2 እና 4 ስናስተያይ አሁን ገነት ሶስተኛው ሰማይ ውስጥ እንደሆነች እናያለን። የእየሱስ ተከታይ የሆነ ሁሉ ሲሞት የሚሄደው ወደዚህ ነው (ፊልጵስዩስ 1፡23)።
የክርስቶስ ተመልሶ መምጣት ምልክቶች
የክርስቶስ መምጫው ሲቀርብ ስለሚሆኑ አንዳንድ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ከነዚህም አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፣
1. ጦርነት፤ ረሃብ እና የመሬት መንቀጥቀጥ (ማቴዎስ 24፡7)። ምንም እንኳን እነዚህ ነገሮች ከበፊትም ቢኖሩ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት (1939 - 1945) ወዲህ ቁጥራቸው በጣም በዝቷል።
2. በአጭር ጊዜ ውስጥ የእውቀት በጣም መጨመር እና የዓለም አቀፍ ጎዞዎች መብዛት (ዳኔኤል 12፡4)። እነዚህ ሁለት ምልክቶች ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ከቀድሞው ጊዜ ይልቅ በብዛት ታይተዋል።
3. ሰዎች ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ (2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡4)። በአሁን ጊዜ ብልግና ዋና የክፋት ባህሪይ ሆኗል። የወሲብ ሥራ ሲኒማ እና ቪዲዮ ቴፖች ብልግናን በማሰራጨት የሰይጣንን ዓላማዎች ያገለግላሉ።
4. ሰዎች ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ ( 2 ጢሞቴዎስ 3:2-4 )።
ዛሬ ዐመጽን በአካባቢያችን - በቤት ውስጥ፤ በትምሕርት ቤቶች፣ በኮሌጆች እና በፋብሪካዎች ውስጥ እናያለን።
5. አማኞች ሃይማኖትን ይክዳሉ (1ኛ ጢሞቴዎስ 4፡1)። አማኞች በተለያዩ አምልኮዎች መስፋፋት የተነሳ ተታልለው ሲወድቁ ዛሬም እናያለን።
6. የእስራኤል ሃገር ሁኖ እንደገና መወለድ (የእስራኤል ምልክት የሆነው የበለስ ዛፍ ሲያቈጠቍጥ) (ሉቃስ 21:29-32 )። ከ70 ዓመተ ምህረት ጀምሮ አይሁዶች በዓለም ዙሪያ ተበትነው ነበር። በዚህ የተነሳ ይህ የበለስ ዛፍ ለ19 ምዕተ ዓመታት ያህል ጠውልጎ ከቆየ በኋላ በግንቦት 1948 እስራኤል እንደገና ተወለደች። ጊዜያቸው ተሟልቶ እስከሚያበቃ ድረስ አይሁድ ያልሆኑ ሃገሮች እየሩሳሌምን እንደሚይዙ እየሱስ ተናግሮ ነበር (ሉቃስ 21:29-32)። ከ20 ምዕተ ዓመታት በኋላ በ1967 በሰኔ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ እስራኤል እየሩሳሌምን ያዘች
ዛሬ በዓለም ውስጥ የሚሆነውን ማየት አስደሳች ነው። ምልክቶቹ ሁሉ የሚያሳዩት የእየሱስን በቅርብ መምጣት ነው።
የመጀመሪያው ትንሳኤ እና የእየሱስ የፍርድ ወንበር
ክርስቶስ ተመልሶ ሲመጣ የእሱ የሆንን ሁሉ በአንድ ጊዜ እንለወጣለን። የማያረጅ እና የማይሞት አዲስ አካል ይሰጠናል (1ኛ ቆሮንጦስ 15:51-53)። አዲሱ አካላችን እየሱስ ከትንሳኤ በኋላ እነደነበረው አካል ነው የሚሆነው (ፊልጲሲዩስ 3:20 , 21 )። በክርስቶስ ሆነው የሞቱ ሁሉ አዲሱን አካላቸውን ለብሰው ከመቃብራቸው ይነሱ እና ካልሞቱት የእየሱስ ተከታዮች ጋር በአንድነት ሆነው በደመና ተነጥቀው እየሱስን በአየር ይቀበላሉ (1ኛ ተሰሎንቄ 4:13-17)።
ከዚያም የክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ለፍርድ (ግምገማ) ቀርበን እያንዳንዳችን በምድር ሳለን በነበረን ታማኝነት መጠን እንሸለማለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ለነበሩት ስለሚሰጠው የጽድቅ አክሊል ይናገራል። ጌታ ስለሚሰጠው ሽልማቶች በዝርዝር 2ኛ ቆሮንጦስ 5፡10; 1ኛ ቆሮንጦስ 3:11-15 & 4:5; 2ኛ ጢሞቴዎስ 4:8 እና 1ኛ ጴጥሮስ 5:4 ማንበብ ትችላላችሁ።
በዚያን ጊዜ "ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ" (ማቴዎስ 19፡30)። በእኛ አስተያየት በምድር ላይ መንፈሳዊ የሚመስሉን ብዙሃን በእግዚአብሔር ፊት ግን ታማኞች እንዳልሆኑ ይታያሉ። ሌሎች ደግሞ እኛ የምናጥላላቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ታማኞች ይባላሉ። በዚያን ጊዜ ምንም ያልታወቀች መበለት በዓለም ከታወቀው ነገር ግን እምነት የሌለው ሰባኪ ትቀድማለች።
በዚያን ቀን ዛሬ በሰዎች ፊት ታላቅ የሚመስሉ ነገሮች፣ ለምሳሌ በሰዎች ዘንድ ዝናን ማግኘት እና ገንዘብ የመሳሰሉት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ምንም ዋጋ እንደሌላቸው እናያለን። ሌሎች ደግሞ ዛሬ ሰዎች የሚያጥላሏቸው ለምሳሌ ትሕትና፣ ራስን ወዳድ አለመሆን፣ የልብ ንጽሕና፣ ምሕረትን ማድረግ እና መልካምነት በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ እንዳላቸው እናያለን።
ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ 'የበጉ ሰርግ' የሚለው ይሆናል - ይህም እየሱስ ክርስቶስ ሙሽራውን የሚያገባበት መንፈሳዊ ሠርግ ነው። የእየሱስ ሙሽራ ለመሆን ታማኝ ሆነው፣ ፍላጎታቸውን ትተው፣ መስቀላቸውን በየቀኑ ተሸክመው እየሱስን ተከትለው በምድር የኖሩ አማኞች ናቸው (ራዕይ 19:8-10)። በዚያን ጊዜ ለጌታችን እና ለጌታችን ወንጌል ብለን የደረሰብን መከራ፣ ስደት፣ ስድብ፣ የሰዎች እኛን አለመረዳት፣ ሞትም ጭምር ቢሆን የከፈልነው ዋጋ ተገቢ እንደሆነ እናያለን።
ሚሊኒየም
ሰላም የሰፈንበት የአንድ ሺ ዓመት መንግሥት ይጀመራል። በዚህ ጊዜ የዔድን ገነትን የሚመስል ሁኔታ በዓለም ይፈጠራል፣ አንበሳው በሰላም ከበግ ጋር ይቀመጣል፣ ልጆች ከማይጎዳቸው ኮብራ ጋር ይጫወታሉ፣ ወዘተ (ኢሳይያስ 11:6-9)።
በዚያን ጊዜ እየሱስ ከእየሩሳሌም በዓለም ላይ ይነግሳል (ዘካርያስ 14:9-21)። በዚህ መንግሥት ጊዜ ሰይጣን ወደ መሬት መምጣት አይችልም። ከአንድ ሺ ዐመት በኋላ ሳይቀየሩ የቀሩትን ለመፈተን ሰይጣን ለጥቂት ጊዜ ይለቀቃል። አሁንም ብዙሃን ሰይጣንን ይከተላሉ። ምንም እንኳን ለአንድ ሺ ዓመት በሰላም ዓለምን ክርስቶስ ቢይስተዳድርም አንዳንዶች የእየሱስን የሰላም መንግሥት ትተው ሰይጣንን መከተል መምረጣቸውን እግዚአብሔር ለሰዎች እና ለመላእክቶች ያሳያል። ይህ ነው የሰው መታውር፣ ክፋት እና ግትርነት። እግዚአብሔር በእነዚህ አመጸኞች ላይ በፍርድ ይመጣል፣ ሰይጣንም ወደ እሳት ባሕር ይጣላል (ከፍተኛ ገሃነም - ራዕይ 20:7-10)።
ሁለተኛው ትንሳኤ እና የመጨረሻው ፍርድ
ያላመኑትን ሁሉ ለመፍረድ እግዚአብሔር በፍርድ ወንበሩ ይሆናል። ይህ ሁለተኛው ተንሳኤ ይሆናል። ሙታን ከመቃብራቸው ይነሳሉ። ያላመኑ ሰዎች ነፍሳቸው ከገሃነም ተመልሰው ምድራዊው አካላቸው ውስጥ ገብተው እግዚአብሔር ፊት ለፍርድ ይቆማሉ። "ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን" ይከፈላሉ (ራዕይ 20፡12)።
ማህደረ ትውስታ በሕይወታችን ሙሉ የነበሩንን አስተሳሰቦች፣ አመለካከቶች፤ ንግግሮች፣ ያደረግናቸው ነገሮች እና የነበሩንን ዓላማዎች በሙሉ በትክክል እንደ ቪዲዮ ይቀርጻል። በዚያን ጊዜ ተደብቆ የቆየውን አኗኗራችንን ዓለም ሁሉ እዲያውቀው እግዚአብሔር የተቀረጸውን ያሳያል። ይህ የሚሆነው እግዚአብሔር ሰዎችን ወደ ዘላለማዊ ፍርድ ሲልክ እሱ ግን ፍጹም ጻዲቅ ስለመሆኑ ነው።
ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ያለተጻፈ ሁሉ ሲያገለግሉት የነበረው ሰይጣን ወዳለበት ወደ እሳት ባሕር ይጣላሉ (ራዕይ 20፡15)።
የጊዜ ፍጻሜ
ከዚህ ቅጥሎ ዘመን ይቆምና ዘላለማዊነት ይጀምራል። ጌታ የዋጃቸው ወንዶች እና ሴቶች ወደ አዲሱ ገነት እና ወደ አዲሱ ምድር ይገባሉ ፣ እየሱስ እና ሙሽራው በክብር ያንጸባርቃሉ (በራዕይ 21 ላይ እንደተጻፈው)።
ሰይጣን እና ያላመኑ ሁሉ ፍጹም ከሆነው ገነት እና ምድር ተባረዋል። በዚያ በተከበረ አጽናፈ ሰማይ ውስጥ ሃጢያት እና ስጋዊ ምኞቶች አይኖሩም። ገነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለዘለዓለም ለመፈጸም በደስታ በመረጡ ሰዎች ይሞላል።
ድል የመጎናጸፍ ጥሪ
ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፤ "ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ (ያሁኑ ሰማይ እና ምድር)፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል" (2ኛ ጴጥሮስ 3:11 , 12 )።
በእነዚህ የመጨረሻ ቅናት የመንፈስ ቅዱስ መልእክት በዚህ ሊጠቃለል ይችላል ፡ "ድልን ተጎናጸፉ" (እነዚህን ጥቅሶች ይመልከቱ ራዕይ 2:7 , 11 , 17 , 26 ; 3:5, 12, 21; 21:7).
የዚህ መጽሐፍ መጀመሪያ የዛሬ ሰባኪዎች ስለማያነሱት፣ ንስሓ መግባት ላይ ትኩረት ሰጥተን ጀመርን።
የመጽሓፉ መጨረሻ ላይ ደግሞ ሌላ የዛሬ ሰባኪዎች ስለማያነሱት፤ ድል መንሳት ላይ ትኩረት እንሰጣለን።
የሰው ዘር ወደ ሃጢያት ከወደቀ ጅምሮ የእግዚአብሔር ለሰው የነበረው ጥሪ ሃጢያትን አሸንፎ በድል ስለመኖር ነው። እግዚአብሔር ቃየንን እንዲህ አለው፣ ኃጢአት በደጅ (በልብህ)ታደባለች፤ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት (ዘፍጥረት 4፡7)። ይህ ጥሪ በመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ ላይም በድጋሚ ተጽፏል።
ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል (ራዕይ 21፡7)።
በኑሮአችን ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ፈጥረን የሱን ሥራ እየሠራን ስንኖር ከምናገኘው ክብር ጋር የሚወዳደር በምድር ላይ አንዳች ነገር የለም። እየሱስ ምድር ላይ በነበረ ጊዜ የኖረው ኑሮ ከማንም ሰው በላይ በጣም ድንቅ፣ በክብር እና በደስታ የተሞላ ነበር። በዚያን ጊዜ በዓለም ዝናን ያተረፈ ወይም ሃብታም አልነበርም። ሆኖም የእግዚአብሔርን ክብር በሕይወቱ አሳየ።
ወንጌል የሚሰጠን የምሥራች ዜና እኛም በሕይወታችን የእግዚአብሔርን ክብር ማሳየት እንደምንችል ነው። ሕይወታችሁን ሁሉ በድል መኖር ትችላላችሁ። እድሜያችሁን ሁሉ በታማኝነት የዘላለም እሴቶች ላይ በማተኮር ኑሩ። አሜን።