ወረድ ብሎ እንደምናየው በአጠቃላይ ክርስቲያኖችን በሁለት መክፈል እንችላለን።
1) "የሮማ ካቶሊኮች" እና "ፕሮቴስታንቶች" (በመወለድ ላይ የተመስረተ)።
2) ኤፒስቆፖስ "(የሚስማሙ/conformist) እና "ነፃ ቤተክርስቲያን "(የማይስማሙ/non-conformist) (በቤተክርስቲያን ሥርዓት ላይ የተመሠረተ)።
3) "ዳግም የተወለዱ ክርትስቲያኖች" እና "በስም ብቻ ክርስቲያኖች የሚባሉ" (በልምምድ ላይ የተመሠረተ)።
4) "ወንጌላውያን" እና "ነጻ አሳቢ / ሊበራል" (በአስተምህሮ ላይ የተመስርተ)።
5) "ካሪዝማቲክ እና "ካሪዝማቲክ ያልሆኑ " -("በልሳን በመናገር" ላይ የተመስረተ)።
6) "የሙሉ ሰዓት ክርስቲያን ሠራተኞች" እና "ዓለማዊ ሠራተኞች" - (በሙያ ላይ የተመስረተ)።
ይህን የመሳሰሉ ሌሎች ምድቦችም ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም አንዳቸውም ቢሆኑ ጌታችን ሊፈታው ለመጣው ችግር መፍትሄ የላቸውም።
ብዙዎች "ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን እንደሞተ" ያውቃሉ (1ኛ ቆሮ 15፡3)። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ክርስቶስ የሞተበት ሌላው ምክንያት ለራሳችን ብቻ መኖርን እንድንተው መሆኑን ብዙዎች አይገነዘቡም፤ "... ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ" (2ኛ ቆሮ 5፡15)በመጽሓፍ ቅዱስ አመለካከት መሠረት ክርስቲያኖችን እንደሚከተለው መመደብ እንችላለን፤ "ለራሳቸው የሚኖሩ" እና "ለክርስቶስ የሚኖሩ ፤ ወይም "የራሳቸውን ብቻ የሚሹ" እና "የክርስቶስን ነገር ብቻ የሚሹ" ወይም "ምድራዊ ነገሮችን የሚያስቀድሙ" እና "የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያስቀድሙ"; ወይም "ገንዘብን የሚወዱ" እና "እግዚአብሔርን የሚወዱ". (ኢየሱስ ሁለቱንም መውደድ እንደማይቻል ተናግሯል - ሉቃስ 16: 13)።
ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት አመዳደብ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ሰምቼ አላውቅም። ይህ አመዳደብ የክርስቲያንን ውስጣዊ ሕይወት እና ከእግዚአብሄር ጋር ያለውን የግል አካሄድ ይመለከታል ፣ ቀደም ሲል የተጠቀሱት ግን በውጭ ለሰዎች የሚታየውን አኗኗር የሚመለከቱ ናቸው። ሆኖም ክርስቲያኖች የሚመዘኑት በሁለተኛው መንገድ ነው። ስለዚህ ብቸኛ የሆነው ምድብ ይህ ነው! ይህን በመጠቀም ሌሎች ሊመድቡን አይችሉም። በውስጣችን ምን እንደሚያነሳሳን እና ውስጣዊ ምኞታችን ምን እንደሆነ ከእኛ በቀር ማንም ስለማያውቅ እኛ እራሳችንን መመደብ አለብን። ይህንን ሚስቶቻችንም ላያውቁ ይችላሉ።
ጌታችን በዋነኝነት የመጣው ለሰዎች ትምህርትን ፣ ወይም የቤተ-ክርስቲያን አመሠራረትን ወይም ስዎች በልሳኖች እንዲናገሩ አልፎም የአኗኗር ልምምድ ለመስጠት አይደለም!
ጌታችን የመጣው "ከኃጢአት ሊያድነን" ፤ ከዛፉ ሥር ላይ መጥረቢያውን ሊያደርግ ነው። ስለዚህም የኃጢአት ሥረ መሠረቱ - ራሳችንን ከሁሉም ማስበለጥ ፣ የሚያስደስቱንን ነገሮች ብቻ መሻት እና የግል ፍላጎታችንን ማሳደድ ነው። ጌታ ይህንን "ከሥሩ" ከህይወታችን እንዲነቅለው ካልፈቀድን ፣ ክርስትናችን ለሰዎች በውጭ የሚታይ ብቻ እና ጥልቀት የሌለው ይሆናል። ሰይጣን በትምህርታችን ወይም በልምምዳችን ወይም በቤተክርስቲያናችን አመሠራረት የተነሳ ከሌሎች ክርስቲያኖች የተሻልን ነን ብለን እንድናስብ ያደርገናል!
በራስ ወዳድ እና የግል ምኞታችንን ለማርካት ብቻ ከኖርን ለሎች ነገሮች ላይ ትክክል ብንሆን (ትክክለኛ አስተምህሮ ፣ ትክክለኛ የክርስቲያን ልምምድ እና ትክክለኛ የቤተ ክርስቲያን አመሠራረት ቢኖረንም) ሰይጣን ግድ የለውም (በነገራችን ላይ ይህ "በኃጢአት ውስጥ የመኖር" ሌላው ምልክት ነው!!)። በአሁኑ ጊዜ ሕዝበ-ክርስትና የራሳቸውን በሚፈልጉ እና የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለሟሟላት በሚኖሩ ክርስቲያኖች ተሞልታለች። ብዙዎቹ በአስተምህሮ ልዩነቶች ወይም በአላቸው ልምምዶች ወይም በሚሳተፉበት ቤተ ክርስቲያን የተነሳ እግዚአብሔር ከሌሎች ክርስቲያኖች አብልጦ እንደሚያያቸው የሚያምኑ እና የሚተማመኑ ናቸው። ይህ ሁኔታ ሰይጣን በሕዝበ-ክርስትና ውስጥ ያከናወነውን ታላቅ ሥራ ምን እንደሆነ ያሳያል።በዮሐንስ 6፡38 ላይ ጌታችን ከሰማይ ወደ ምድር የመጣበትን ምክንያት ተናገረ፤
(1) የራሱን ፈቃድ ለመካድ (ይህም ማለት እንደ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ሲመጣ እንደማንኛውም ሰው ያገኘው የግል ፈቃድ) እና
(2) እንደ ማንኛውም ሰው ሁኖ፤ ነገር ግን የእርሱን ፍቃድ ትቶ የአባቱን ፈቃድ ብቻ ማድረግ ነበር። በዚህ ምርጫው የተነሳ ለእኛ ምሳሌ ሆነልን።
ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ሁሉ (ሙሉውን 33 ዓመት ተኩል) የራሱን ፈቃድ ክዶ የአባቱን ፈቃድ ፈጸመ። ተከታዮቹን የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆን ከፈልጉ በተመሳሳይ መንገድ መሄድ እንዳለባቸው በግልፅ ነግሮአቸዋል። በሕይወታችን ውስጥ የኃጢአትን ሥር ("ግላዊ ፈቃዳችንን ማሳደድ") ለመምታት እና ከዚያ ሊያድነን ወደ ምድር መጣ።
በሳይንስ መስክ ስናይ ለሺዎች ዓመታት የሰው ልጅ ምድር የአጽናፈ ዓለማት ማዕከል ናት የሚል የተሳሳተ እምነት ነበረው። ፀሐይ ፣ ጨረቃ እና ኮከቦች በየ 24 ሰዓቱ አንድ ጊዜ በምድር ዙሪያ የሚዞሩ ስለሚመስሉ በሰው እይታ ይህ አምነት ትክክል ይመስል ነበር። ከ 500 ዓመታት በፊት ኮፐርኒከስ ይህን ለዘመናት የነበረውን ታላቅ እምነት ፍጹም ስህተት መሆኑን እና ምድር የሰማይ አጽናፍ ማዕከል መሆን ቀርቶ የፀሃይ ስርዓት እንኳን ማእከል አለመሆኗን አሳየ። ምድር በፀሐይ ክልል ውስጥ እንድትኖር የተፈጠረች መሆኗን አሳየ። ሰው የተሳሳተ ማዕከል እስካለው ድረስ የሳይንስ ስሌቶቹ እና ውጤቶቹ ሁሉ የተሳሳቱ ይሆናሉ - ምክንያቱም ማዕከሉ የተሳሳተ ነውና። ነገር ግን ሰው ትክክለኛውን ማዕከል ካወቀ በኋላ እነዚህ ስሌቶች እና ውጤቶቹ ሁሉ ትክክል ይሆናሉ።
"እግዚአብሔር ላይ ከማተኮር" ይልቅ "በራስ ወዳድነት" የግል ፍላጎታችንን ብቻ የምናሳድድ ከሆነን እኛም የዚህ ተመሳሳይ የተሳሳተ አስተሳሰብ ይኖረናል። ስለሆነም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እና ስለ እግዚአብሔር ፍጹም ፈቃድ የሚኖሩን አስተሳሰቦች (ስሌቶቻችን እና ግንዛቤዎቻችን) በሙሉ የተሳሳቱ ይሆናሉ። ከላይ እንዳየነው ሰዎች ለ5000ሺ ዓመታት ትክክል መስሎአቸው ስህተት አምነው እንደኖሩ ሁሉ እኛም ልክ እንደሆንን መገመት እንችላለን! ንገር ግን እኛም 100% ስህተተኞች እንሆናለን።
ዛሬ በብዙ "ጥሩ ክርስቲያኖች" በሚባሉት መካከል እንኳን ይህን ሁኔታ እናያለን። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሆኖ የተለያዩ ትርጓሜዎች ተሰጥተውን እናያለን - ነገር ግን እያንዳንዳቸው የእነሱን አተረጓጎም ብቻ ትክክል እንደሆነ እና የሌሎችም ሁሉ ስህተት ለመሆኑ እርግጠኞች ሆነው ሌሎቹን "እንደ ተታለሉ" ይቆጥሯቸዋል። ይህም የሚሆንበት ምክንያት የተሳሳተ ማእከል ስላላቸው ነው።
ሰው የተፈጠረው እግዚአብሄርን ማእከል እንዲያደርግ እንጂ የራሱ ማእከል እንዲሆን አይደለም። ስለዚህ ክርስቲያኖች ማእከላቸውን ሲስቱ እንዲሁም "ወንጌላቸው" የተሳሳተ ይሆናል። በመሠረቱ ዛሬ የሚሰበኩት ሁለት ወንጌሎች ብቻ ናቸው - አንደኛው በሰው-ተኮር የሆነ ሲሆን ይሌላኛው ደግሞ እግዚአብሔር ላይ ያተኮረ ነው።
ሰው ላይ ያተኮረው ወንጌል ሰዎች በምድር ሳሉ ምቾት የተሞላ ሕይወት እንዲኖራቸው እግዚአብሔር የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚያደርግላቸው አና በመጨረሻም በሰማይ መቀመጫ እንደሚኖራቸው ይናገራል። በተጨማሪም ኢየሱስ ኃጢአቶቻቸውን ሁሉ ይቅር እንደሚል ፣ በሽታዎቻቸውን ሁሉ እንደሚፈውስ ፣ በቁሳዊ ነገሮች እንደሚባርካቸው እና እንደሚያበለጽጋቸው ፣ ምድራዊ ችግሮቻቸውን ሁሉ እንደሚፈታላቸው፣ ወዘተ 'ያሳያል' ።
እንደዚህ ዓይነት ሰው የሕይወት ማእከሉ ''ራሱ" ስለሆነ በአስተሳሰቡ እግዚአብሔር በእርሱ ዙሪያ ይሽከረከር እና - እንደ አገልጋዩ ሆኖ ለጸሎቱ ሁሉ መልስ ይሰጣል ፤ የሚፈልገውን ሁሉ ያደርግለታል !! እሱ ማድረግ ያለበት ነገር ቢኖር "ማመን" እና "በኢየሱስ ስም እያንዳንዱን ቁሳዊ በረከት መጠየቅ" ነው !!'ንስሓን' ስለማያካትት ይህ ወንጌል የሐሰት ወንጌል ነው። መጥምቁ ዮሐንስ ፣ ኢየሱስ ፣ ጳውሎስ ፣ ጴጥሮስ እና ሁሉም ሐዋርያት በመጀመሪያ ደረጃ የሰበኩት ስለ ንስሓ ነበር። የሚያሳዝነው ነገር ዛሬ ንስሓ ከስብከት ሁሉ መውጣት ነው !!
እግዚአብሔር ላይ ያተኮረ ወንጌል ሰው ንስሐ እንዲገባ ጥሪ ያቀርባል። በተጨማሪም "ንስሐ" ማለት ምን እንደሆነ ያስረዳል።
ራስን የሕይወት ማዕከል ማድረግን ፣ የራስን ፈቃድ ማድረግን ፣ ራስ በመረጠው መንገድ መጓዝን ፣ ገንዘብ መውደድን፣ ዓለምን እና በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች መውደድን (ለምሳሌ ለሥጋ ምኞት ፣ ዐይኖች የሚያዩትን መመኘት እና ኩራትን)፣ ወዘተ ሁሉ በመተው፣ ወደ እግዚአብሔር መዞር፣ በሙሉ ልብ እርሱን መውደድ ፣ እሱን የሕይወት ማዕከል ማድረግ እና ከዚያም ፈቃዱን ማድረግ ፣ ወዘተ።
የክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞት በማመን አንድ ሰው ኃጢአቱን ይቅር ሊባል የሚችለው ንስሐ በገባ ጊዜ ብቻ ነው። ይህ ሲሆን በእግዚአብሔር ላይ ያተኮረ፤ እግዚአብሔርን ማእከላዊ ያደረገ ኑሮ መኖር እንዲችል በየቀኑ እራሱን መካድ የሚያስችለውን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ሊቀበል ይችላል። እየሱስ እና ሐዋርያት የሰበኩት ወንጌል ይህ ነው።
ሐሰተኛው ወንጌል በሩን ሰፊ እና መንገዱን ሰፊ ያደርገዋል (ሰው የራስን ማንነት መካድ ወይም ለራሱ ጥቅም መኖርን መተው ወይም የራሱን ጥቅም መፈለግ ማቆም ስለሌለበት አብሮ መጓዝ ቀላል ነው)። በሚሊዮን በሚቆጠሩ እንደዚህ ያለ የሐሰት "ወንጌል" በሚሰበክባቸው ስብሰባዎች ላይ ይሳተፋሉ። ብዙዎች ወደ ሕይወት ይወስደናል ብለው በማሰብ በዚህ በር ገብተው በዚህ መንገድ ይሄዳሉ። ነገር ግን ይህ መንገድ የሚያመራው ወደ ጥፋት ነው። የዚህ ወንጌል ሰባኪዎች ግን በስብሰባዎቻቸው ላይ "እጃቸውን ስለ አውጡና ስለ ክርስቶስ ስለወሰኑ" ብዛት ያላቸው ሰዎች ይደሰታሉ እንዲሁም ሪፖርት ያደርጋሉ!! ነገር ግን ይህ ሁሉ መታለል ነው። ምንም እንኳን አንዳንዶቹ ከቅን ልቦናቸው የተነሳ በዚህ ዐይነት ስብሰባዎች በእውነትም የተለወጡ ቢሆኑም ፣ ብዙዎቹ "ሁለት የገሃነም ልጆች" ይሆናሉ (ማቴ. 23 15) - ስለ ትክክለኛው ሁኔታቸው ተታለዋል።
እውነተኛው ወንጌል ግን በሩን ትንሽ እና መንገዱን ጠባብ ያደርገዋል - አንዳንድ "እጅግ-መንፈሳዊ" ነን ባዮች እንደሚያደርጉት ሳይሆን ኢየሱስ ራሱ ሳያንስ ሳይጠብ በልኩ እንዳደረገው ነው። ይህን ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ የሚያገኙት ጥቂቶች ናቸው። የዚህ ወንጌል ወንጌላውያን ብዙ የሚያወሩት ነገር አይኖራቸውም። እና አኃዛዊ መረጃዎቻቸው አስገራሚ አይደሉም። ነገር ግን ይህ ወንጌል ሰዎችን ወደ ጌታ ኢየሱስ እና ወደ መንግሥተ ሰማያት ይመራቸዋል።
እንዴት እንደምታዳምጡ ተጠንቀቁ ፤ ለሰማው የሚታዘዝ ሁሉ ለእርሱ የበለጠ ብርሃንና ማስተዋል ይሰጠዋል። የሰማውን የማይታዘዝ ግን አለኝ ብሎ የሚገምተውም ብርሃን እና ማስተዋል ይወሰድበታል (ሉቃስ 8፡18)።
የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ፡፡